Get Mystery Box with random crypto!

የዘላለም እናት በእናትነት አንጀት በአባታዊ ወኔ፣ አቅፋ አሳድጋኝ እኔን በወገኔ፣ የወላድ ማህጸን | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

የዘላለም እናት
በእናትነት አንጀት በአባታዊ ወኔ፣
አቅፋ አሳድጋኝ እኔን በወገኔ፣
የወላድ ማህጸን እንስፍስፍ ሲያደርጋት፣
ፍቅሯ ከልክ ሲያልፍ እናት ነሽ ስላልናት፣
የደጉ ቀን እናት የከፋ ለት አባት፣
ሀገሬ እንዲህ ናት፣

በስም አባት ብቻ ልጇን ያልተጋራች፣
እኔ ላሳድገው ሲሏት ያልተስማማች፣
አሁን ላይ ጐርምሶ ከቤት ልውጣ እንዳለው፣
ሰፈር ሲበጠብጥ ያላሰደገ አባት ከየት ነው ሚመጣው፣
ባላዋቂ ብዕር ማገር ሲነቀንቅ፣
የት ያለው አባት ነው ምሰሶ እሚያጠብቅ፣
ጠግቦ ልውጣ ብሎን ለያዥ ካስቸገርን፣
በምን ቀሚሷ ነው እሷ ምሸሽገን፣
ቀሚሷን ለመያዝ የተሽቀዳደመው፣
ሸማዋን ቀዳዶ ሌጣዋን ካስቀረው፣
እናቴ ምን ታድርግ በምኗ ትያዘው፣

ፍሬዎቿ እሾህ ሆነን ከበቀልን፣
እሽ በምን እዳ መጣ ትሰብስበን፣
እንደው በየት ቦታ እረ በየት ሀገር፣
ልጅ እናትን እንጂ እናት ልጅን አጦር፣
በማረፊያዋ ወቅት ባክኚልን ካልናት፣
ውለታዋን ሽረን ካልን አባት አባት፣
ጀግና እናት መሆኗን የረሳነው መስሏት፣
እንደ ዘመዶቿ እሷም አንሳ ጎብጣ፣
ለማደጎ እንዳይሆን ነገም የእኛ እጣ።

ትዕይንት አባተ

ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19