Get Mystery Box with random crypto!

ያሉባልታ እና የፍቅር ፀብ ድሮ ገና ድሮ ሰማዩ ከተራራ በላይ ሳይወጣ የሰው ልጅ ከጭቃና ከእሳት | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ያሉባልታ እና የፍቅር ፀብ

ድሮ ገና ድሮ ሰማዩ ከተራራ በላይ ሳይወጣ
የሰው ልጅ ከጭቃና ከእሳት በእስትንፋስ ሳይመጣ
አእዋፍ ዜማን ሳይቀምሩ
እንስሳት በሜዳው ሳይሰርሩ
በውሀ ጉልበት ወንዞች ሳይሰሩ
                     ሀይቆች ሳይፈጠሩ
ወርቅ የተላበሰ ብርሃናማው ፍቅር
በጨቅላዋ አለም ላይ ብቻውን ይኖር ነበር አሉ
አይሉት የለ...

አንበሳ ሚዳቋን ሳይበላ
ብርታት ባፈር ውስጥ ሳይተላ
ቃየል ወንድሙን ሳይጠላ
የደም ገመድ ክረቱ ሳይላላ
ኤሎሂም በሉ ውጡልኝ ሳይል
መለዐክ  ጌታ ሆኖ በሲዖል ሳይሸልል
ከዛ ሁሉ በፊት ዘመናት ሳያልፉ
የዕጣ ፈንታ እህቶች ጥልፋቸውን ሳይጠልፉ
በጨለማው መሀል ያው ፍቅር ነበረ
የህይወትን ሰዓት ሀ ብሎ የጀመረ
እያሉ ያወራሉ ወሬው እንደሆን አያልቅ...

አዬ...
ፍቅርስ አለፈበት ገና ድሮ ቀረ
መውደድ ይሉት ፈሊጥ ጊዜ አልፎት በረረ
ማስመሰል ተክቶት መሬት ውሎ አደረ
ይበሉ ግድ የለም
ውዴ የኛን ኑሮ ተናጋሪ አልኖረም

የዘንድሮ ፍቅር...
ልክ እንደ ሸረሪት ግጣሙን ይበላል
እንደ ንጋት ጤዛ
ጠዋት አለሁ ብሎ ከሰዓት ይተናል
እየተባባሉ በየቡናው ይጠጡት
በየዕቁብ በየዕድር ተሰብሰበው ያውጉት
ጠበል ጠዲቅ አርገው በዝክር ይቋደሱት
ያውሩት ይለፍፉት እኔ ግድ የለኝም
ፍቅር ታማሁ ብሎ አንቺን አልነሳኝም

                       ኤሮስ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19