Get Mystery Box with random crypto!

እረፍቴ እረፍቴ ሆይ ወዴት አለሽ? በታሪክ ጉም በጭለማ ስፈልግሽ፣ በዕድሜ መንገድ ጎዳናው ላይ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

እረፍቴ

እረፍቴ ሆይ ወዴት አለሽ?
በታሪክ ጉም በጭለማ ስፈልግሽ፣
በዕድሜ መንገድ ጎዳናው ላይ ሳባርርሽ፣
በዘመን ሸለቆ ልክ እንደወንዝ ስፈስ፣
መሻት ሞልቶኝ አንችን ሳስስ...

ጊዜ ክንፍ አውጥቶ 'ንደ ንስር በረረ
ሄዋን በለስ በላች፥አዳም ተባረረ፤
መስዋዕቱ በልጦ፥ አቤል ተወደደ፤
ግድያን በመፍጠር፥ቃየል ተሰደደ፤
ኖህም ጀልባ ሰራ፥ከጥፋት ተረፈ፤
አብርሃም ተጠራ፥በይስሓቅ አረፈ፤

ሰላሜ ሆይ አንቺን እያሳደድኩ...
በዘመን ሸለቆ ልክ እንደወንዝ ስፈስ
መሻት ሞልቶኝ አንችን ሳስስ...
ያዕቆብ  ተሰደደ፤አምላክን ታገለ፤
ሲባረክም አድሮ፥እስራኤል ተባለ፤
ዮሴፍ ተወለደ፥አድጎም ሕልም አለመ፤
የአቤል እጣ ደርሶት፥ከጉድጓድ ተጣለ፤
ሙሴ አንቺን ፈለገ፥ከተራራ ወጣ፤
እግዜርን ሲገድር፥ፈርዖን ተቀጣ፤
ዳዊት ተመረጠ፥ዘይቱን ተቀባ፤
በጠጠር ተጥሎ፥ጎልያድ መሬት ገባ፤
ዳንኤል ታሰረ፥ላንበሶች ተሰጠ፤
ዮናስ በማበዩ፥ለሦስት ቀን ተዋጠ፤

እረፍቴ ሆይ አንቺን ሳስስ ስፈልግሽ፣
በታሪክ ውስጥ እያሳደድኩ ስከተልሽ፣
ትንቢቶች ተናግረው፥ትንቢቶች አለፉ፤
መንደሮች ተወልደው፥ከተማ ሆነው ሰፉ፤
እረፍቴ ሆይ አንቺን ሳስስ፣
በዘመን ሸለቆ ልክ እንደወንዝ ስፈስ...
ጡንቻ አጥንቴ ላፍታ ሳይደክም፣
ትከሻዬ ሳይጎብጥ፥ቁመናየ ሳይጠም፣
የረገጥሽውን እየረገጥኩ፥ በየሄድሽበት ስከተልሽ፤
በታሪክ ውስጥ እያሳደድኩ፥ ለዘመናት የፈለግኩሽ፤
ቀራንዮ መስቀሉ ስር፥ተቀምጠሽ አገኘሁሽ።
  
                       ~ተፃፈ በኤሮስ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19