. አልሻረም እያልኩኝ መገፋት የጫረው የልቤ ላይ ቁስል አሁን ላይ ተገኘሁ ወፍራም ፍቅርን ችየ በ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

.

አልሻረም እያልኩኝ
መገፋት የጫረው የልቤ ላይ ቁስል
አሁን ላይ ተገኘሁ
ወፍራም ፍቅርን ችየ በስስ ቀለም ስስል

ትናንት ደህና ነበርኩ
ቅድም ደህና ነበርኩ አሁን ግን አመመኝ
በምን ይባበላል እንዲህ ያል ገጠመኝ

'የወንድ ልጅ ነገር'
ይለኛል የሰማ መገልበጤ ገርሞት
ባያውቅ ነው እንጂ
እንኳን ሽንፈት ቀርቶ ይረሳ አይደለ ሞት

ሰለቸኝ እስኪሉ አልቅሼ እንዳልማልኩኝ
እርሜ ነው ከእንግዲህ በቃኝ እንዳላልኩኝ
ባ'ንድ ቀን ሽንፈቴ አመት እንዳላፈርኩ
ያንን ሁሉ ትቼ አይገርምም? አፈቀርኩ

የዘመን መርሳትን
የአመት መግፋትን የሽውታ ናፍቆት እያፈራረሰው
በቃኝ ቆረጠልኝ
ወጣልኝ እያለ እንዴት ይኖራል ሰው

ከፍቅር ሲጥለኝ ራሴን ታዘብኩት
አመሌ ሲረታኝ በቃሌ መዘንኩት
የሰው ልጅ መብሰክሰክ
አንዲት ስንዝርን ለውጥ በራሱ አያመጣም
ሁለት እግር ይዞም ሁለት ዛፍ አይወጣም

ከረሱ መርሳት ነው ካፈቀሩ ማፍቀር
ፍቅር በጊዜ ቤት ላይገኝ በቀመር
በቃኝ ካሉም በቃኝ ትዝታን መሸከም
ልቁም ካሉም መቆም ከፍቅር ጋር መክረም

እንዳዲስ እንግዳ
ፍቅር ፍቅር ብሎ በመውደድ ከሚያስረኝ
ትናንቴን የሚያውቀው
ይሄ አብሮአደግ ልቤ ምናለ ቢመክረኝ

ጭራሽ ከሱ ብሶ...
በግጥሞቼ መስመር
የእሷን ስም አስፍቆ ያንቺን አስከተተኝ
ከእንግዲ አልሞክርም
ያልኩትን ሀሳቤን መውደድሽ አሳተኝ

ባ'ንድ ቀን ሽንፈቴ አመት እንዳላፈርኩ
ያንን ሁሉ ትቼ አይገርምም? አፈቀርኩ

ያውም አንቺን


በአቤኒ የተጻፈ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19