Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ፩ 'ልሳልህ?' አልኩት ዝም ብሎ በተቀመጥኩበት ካፌ ወንበር ስቤ ከተቀመጥኩ በኋላ(መቀመጤን | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ክፍል ፩

"ልሳልህ?" አልኩት
ዝም ብሎ በተቀመጥኩበት ካፌ ወንበር ስቤ ከተቀመጥኩ በኋላ(መቀመጤን እስካሁን አላየኝም ነበር ከየት እንደመጣችሁ ራሱ የሚያውቅ አይመስለኝም)
ቀና ብሎ አየኝ ምኔን እንዳየኝ አላውቅም ለመመለስም ላለመመለስም የሚሆን ነገር ያጣ ይመስላል ሁኔታው

"አቤት?"

"አቤት አይባልም እሺ ወይም እንቢ ነው የሚባለው ል ሳ ል ህ ወ ይ?"
ተስተካክሎ ለመቀመጥ ሞከረ ምን እንደሚል እያሰበ ይመስላል
ክብ ፊቴ ላይ አፈጠጠብኝ ለነገሩ እኔን አይቶ ብቻ ምንም አይገባውም ጥልቅ ትመስላለች የሆነች ሊያነቧት ቢጀምሩ የማታልቅ ነገር ይሉኛል ብዙወች የሚያምር እና የማያምር አካሌን ለመቁጠር የሚያስችል ሁኔታ ላይ ያለ አይመስልም። የሴት ውበት ለመለካት ቀርቶ ከሴት ጋር አደለም ከሴት ጋር ከሰው ጋር መነጋገር ራሱ አላሰኘውም።ምን ሊሰራ እዚህ ካፌ እንደገባ እንኳን የሚያውቅ አይመስለኝም ኧረ ምን ያህል እንደቆየ ማወቁንም እንጃ

"ፌቨን እባላለሁ" አልኩት

"እሺ"

"ኧረ እሺ አደለም የሚባለው እኔ ደሞ እገሌ አባላለሁ ነው የሚባለው"

"ምኔን ነው የምትስይው?"

"እ?"

"ማለቴ ለምን ነው የምትስይኝ?"

"አንዳች ነገር ስላየሁብህ"

"ምን ነገር?"

"እሱን እንኳ ከሳልኩህ በኋላ ባሳይህ ነው ደስ የሚለኝ"

አሁን ትንሽ ነቃ ያለ መሰለ

ከካፌው ውስጥ የተከፈተው የኤፍሬም ሙዚቃ ይሰማኛል
"
.
ኮኮብ ተገለጠ ተሸኘ ፀሐይ
ልቤ ረጋ ሳይል አይኔ ሰው ሳያይ
እሷም አልተገኘች ብደክም ብለፋ
ፍቅሬስ አቦል ነበር አጣጪው ባይጠፋ
....." ለኔ እንደሆነ እየተሰማኝ ዘና ለማለት ሞከርኩ።

ከኔ ላይ የሚስብ ነገር? ያውም በአሁኑ ሁኔታየ? እያለ የተገረመ ይመስላል

"ተቀመጭ" አለኝ

ሳቅኩ ከልቤ ሳቄ አልሞቀውም አልበረደውም እንዲሁ ነው ስስቅ አልሳብኩትምም አልደበርኩትምም

"ከተቀመጥኩ እኮ ቆየሁ ባይሆን አንተ ተቀመጥ"

"ምነው የኔስ መቀመጥ አይታይሽም?"

"መስሎህ ነው እንጂ አየር ላይ ነህ አልተቀመጥክም በሀሳብ ሩቅ ሄደሀል ከቅድም ጀምሮ የተቀመጥክ መስሎሀል እንጂ አልተቀመጥክም ያለህ መስሎሀል እንጂ የለህም" ይሄን እያልኩት አንዲት ጠይም ልጅ እግር አስተናጋጅ ማኪያቶ ይዛ መጣችና ከፊት ለፊቴ አስቀመጠችልኝ ፈገግ ብየ አመሰገንኩና ማማሰል ጀመርኩ(መቼ አዝዛ ነው? እያለ የተገረመ ይመስላል) ይሄኔ ነበር እሱ ያዘዘው ሻይ እንኳ መጥቶ መቀዝቀዙን ያየው

እንዲህ ሲሆን የመጀመሪያው አይመስለኝም። እዚህ 4ኪሎ ቅድስተ ማሪያም አካባቢ ካለው ካፌ በመስኮቱ አሻግሮ አንዳች ነገር ላይ ያፈጠጠ ይመስላል ወጪውንም ወራጁንም ታክሲውንም ሁሉንም ያያል። ግን ደግሞ በዛውም ልክ ማንንም እያየ አይደለምደ ቅርብ ይመስላል እንጂ ሩ ቅ ነው ሩቅ ነው ቢሉትም ግን እሱ እዚሁ ነው እዚህም ነው እዛም ነው ግን እዚህም የለም እዛም የለም እንዲህ ያረገዋል መሰለኝ አንዳንዴ

አንዴ ፉት ካልኩለት በኋላ እኔም በሀሳብ ሄድኩ የተከፈተው ሙዚቃ ወደማለቁ ነበር። አብሬ እየዘፈንኩ ነው ለማለት በሚመስል መልኩ ከንፈሬ ይንቀሳቀሳል
"
..
መሸ ደህና እደሩ ናፍቆት ነው ልማዴ
መቼም መተው መርሳት እያውቅበት ሆዴ
ለታቦት ይሳላል የተጨነቀ ሰው
ማን አለኝ እንዳንቺ ነፍሴን የወረሰው
..."

"እኔ እምልህ ለምነህ ታውቃለህ?"

"ማንን?"

"ማንንም ሊሆን ይችላል ፈጣሪህን ወላጆችህን ጓደኞችህን የማታውቀውን ሰው ወይም ራስህን?"

"ራስህን?"

"አወ ራስህን"

"ራሴን ደሞ ምን ብየ ነው የምለምነው?"

"እስኪ ብሮ 15 ብር አበድረኝ ብለህ ልበልህ?" ብየ ፈገግ አልኩ
ፈገግ አለልኝ(ያለ መሰለኝ)

"ለምሳሌ የሆነ ባህሪን እንዲተውልህ የወደድካትን ልጅ እንዲያናግርልህ ይቅርታ እንዲጠይቅ ወይም ሲጠየቅ ይቅር እንዲል አለ አደል ለምነኸው አታውቅም?"

"እኔ እንጃ"

"እንዴት እኔንጃ"

"ማነሽ?"

"ማለት?"

"ማለትማ አንቺ ማነሽ እንዴት ከመሬት ተነስተሽ ስለይቅርታ ልታወሪኝ ቻልሽ? እንተዋወቃለን? ማነው የላከሽ ምንድን ነሽ? ማነሽ?".....

...ይቀጥላል...

በአቤኒ የተፃፈ


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19