Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ፪ ...'ማነሽ?' 'ማለት?' 'ማለትማ አንቺ ማነሽ እንዴት ከመሬት ተነስተሽ ስለ ይ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ክፍል ፪

..."ማነሽ?"

"ማለት?"

"ማለትማ አንቺ ማነሽ እንዴት ከመሬት ተነስተሽ ስለ ይቅርታ ልታወሪኝ ቻልሽ? እንተዋወቃለን? ማነው የላከሽ ምንድን ነሽ? ማነሽ?"

"ፌቨን እባላለሁ አልኩህኮ ሠዓሊ ነኝ ወይም ለመሆን እየሞከርኩ ነው ቢባል ይሻላል። ከቀናት በኋላ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ለምናቀርበው የሥዕል አውደርእይ ስለአንዳንድ ነገሮች እንድንነጋገር ተቀጣጥረን ነው እዚህ የመጣሁት ቅድም እዛጋ ሆኜ ሳይህ በሀሳብ ጭልጥ ብለህ ነበር እናም የሚያዋራህ የሚያጫውትህ የሚያስፈልግህ መሰለኝና መጣሁ። ደፈረችኝ እንደማትል ተስፋ አረጋለሁ ሳዋራህ መለስ ካለልህ ብየ ነው"

ተረጋጋ
"አመሠግናለሁ"

እስካሁን ልብ አላለውም እንጂ መፅሀፍ ይዣለሁ። አየው አንድ እጄን መፅሀፉ ላይ ጣል ስላደረኩት ርዕሱን ለይቶ ማየት አልቻለም

"መፅሀፍ ታነቢያለሽ? አለኝ በአገጬ ወደያዝኩት መፅሀፍ እየጠቆመ

"እንደዛ ነገር በአብዛኛው የውጭ መፅሀፍት ነው የማነበው አልፎ አልፎ ደግሞ የሀገር ውስጥ ግን ብዙም አይመቹኝም የእዚህ ሀገሮቹ"

"ለምን?"

"ሻይህን ሞቅ ያርጉልህ" አልኩና ዞር ብየ የቅድሟን ጠይም አስተናጋጅ ጠራኋትና "ሻዩን አሙቀሽ አምጭለት" ብየ ሰጠኋት

"ኧረ ምን አይነቷ አይን አውጣ ናት! እያልክ ነው አይደል?"

"ኧረ በፍፁም..."
አሁን የበለጠ ለጨዋታ ነቃ እያለ ነው ከደቂቃወች በፊት ድብትብት ብሎ የነበረው ሰው እንዲህ ለወሬ ለጨዋታ መመቻቸቱ እኔን ራሱ ገርሞኛል

"ምን ነበር ያልከኝ?"

"ለምን የሀገር ውስጥ መፅሀፍት አልተመቹሽም?"

"ተመሳሳይ ናቸው የሚናገሩት አዲስ ነገር ብዙም የለም። አብዛኞቹ ወቃሽ ናቸው በተለይ የኛን ትውልድ እነሱ ብቻ አዋቂ፤ እነሱ ብቻ አሳቢ ሆነው መታየት ይፈልጋሉ። መንቀፍ መዝለፍ ማጥላላት ይወዳሉ። ደሞኮ እንዲህ እያጥላሉህም አያነብም እያሉ መልሰው ሊወቅሱህ ይፈልጋሉ። ግን ይሄን ስልህ ሁሉን በድፍን አደለም አንዳንዴ ሰወች ሲጠቁሙኝ ወይም ራሴ ሲመቸኝ አነባለሁ"

"የያዝሽው መፅሀፍ አዲስ ነው?"

"ይሄ አዎ ወር አካባቢ ቢሆነው ነው "

እጄን አነሳሁት ለእሱ ተዘቅዝቆ ቢቀመጥም ርዕሱን ግን ማየት ይችላል 'ሽርፍራፊ ሳቆች' ይላል የበለጠ ነቃ ሲል ታወቀኝ

"አንብበኸዋል?"

"አ.. አይ አላነበብኩትም ማነው የፃፈው ታዋቂ ነው?"

"ታዋቂ ያልሆነ ማን አለ ብለህ ነው? ጥያቄህ ከብዙ ሰው አፍ ላይ በመዋል ከሆነ ግን አይመስለኝም ለምሳሌ እኔ ከዚህ በፊት አላውቀውም 'አሮን እጅጉ' ይባላል ታውቀዋለህ?"

"አይ አልመሰለኝም እና ወደሽዋል አሁን እኔ ላንብበው ብልሽ ትጋብዥኛለሽ?"

"እውነት ለመናገር መፅሀፍ መጋበዝ አልወድም ያ ሰው ምን ልታስተምረኝ ፈልጋ ነው? እያለ ሳይሆን ነፃ ሆኖ እንዲያነብ ነው የምፈልገው ስለመፅሀፉ ግን በእርግጥ ለመጨረስ ጥቂት ገፆች ቢቀሩኝም እንዲሁ 7 ከ 10 እሰጠዋለሁ"

"ለምን 3 ቀነስሽበት?"

ፈገግ አልኩ
እሱም አለ(ወይም ያለ መሰለኝ እርግጠኛ አደለሁም)

ሻዩ ሞቅ ብሎ መጣ አማሰለውናና አንዴ ፉት ብሎ አስቀመጠው

"ምነው?"

"አይ ከሰጠሁት 7 ይልቅ የተቀነሸችው የጎደለችው 3 ማየትህ ገርሞኝ ነው።እኛ ሰወች ከሰፊው ነጠላ ይልቅ መሀል ላይ ያለች ጥቁር ነጥብ ሀሳባችንን ትወስደናለች አ?"

"እሺ ይቅርታ ለምን 7 ሰጠሽው?"

"ጎበዝ እንደዛ ነው የሚባለው
ይሄውልህ አንዳንዶቹን እንደኔ ዕይታ ላስቀምጥልህ ግን ስታነብ የሚጫንህ ይሆን እንደሆን ልተወው"

"አይ ግድ የለም ቀጥይ"

የቀረችኝን ማኪያቶ ጨለጥኳትና ቀጠልኩ "አንደኛ ታሪኩ! ታሪኩን ከመፃፉ በፊት በደንብ ገብቶታል አውቆታል ስንቶቹ መሰሉህ አሪፍ ታሪክ አንስተው ግን ሳይገባቸው ለመናገር ይቸኩሉ እና የሚያበለሻሹት ፤ የልብህን አላደርስ የሚሉት እዚህ መፅሀፍ ላይ ግን ያ ችግር የለበትም። ሁለተኛ ገፀባህሪያቱ የቀረቡሀት መንገድ! ያለስራ የገባ አይድም ገፀባህሪ አላገኘሁም በዛ ላይ ቅርብ ናቸው የምትዳስሳቸው የምታዋራቸው ያህል ይሰማሀል ሶስተኛ እና በጣም የወደድኩለት ደግሞ አይጫንህም ሊያሳምንህ ሊያስገድድህ እኔ ያየሁትን እይ እኔ የሰማሁትን ስማ ሊልህ አይሞክርም። በቃ እየነገረህ ነው አለ አይደል መፃፍ የፈለገውን ነው የጻፈው እየተነፈሰበት ነው። እየተናገረ ግን አስገድዶ አይደለም የሚነግርህ ይሄን ባወቁልኝ ወይም ይሄን ባመኑልኝ ሳይል እንዲሁ ነው የፃፈው አራተኛ ነፃ ነው አይገድብህም። እንደፈለክ እንድታስብ ይተውሀል አንድን ሀሳብ አንስቶ መንገዱን አሳይቶህ ሸኝቶህ ይመለሳል እንጂ እስከመጨረሻው ወስዶ አይዘጋብህም እና እከሌን ጥፋተኛ ነው ወይም ልክ ነው ብሎም አይደመድምብህም ፍርዱ የራስህ ነው። አምስተኛ አነጋገሩ እና ቋንቋው ይገርማል ቀላል ይመስላል ግን በሳል ነው ሌላው ደግሞ ገና ለገና ወረቀቱን አገኘሁ ብሎ ያንንም ያንንም አልፃፈበትም መናገር የፈለገውን ውስጡ የተሰማውን ብቻ ነው የፃፈው ድንገት ታሪኩ ቁርጥ ቢልብህ መናገር የፈለገውን ጨርሷል ማለት ነው። አሉልህ እንጂ አንዳንዶቹ ገና ለገና አገኘን ብለው ወረቀቱ የጠላት ይመስል ማህበራዊውን ነክተው ሳይጨርሱ እዛው ላይ ኢኮኖሚስት ይሆኑልሀል የኢኮኖሚውን ጉዳይ ዳር ሳያደርሱ ደግሞ የጋብቻ አማካሪ ይሆናሉ አሮን ግን የተነሳበትን አላማ ብቻ ነው የፃፈው። ለራሱ ነፃ ሆኖ ለሌላውም ነፃነት የሚሰጥ ሰው ደስ ይለኛል" ብየ ፀጥ አልኩ

"ይሄን ያህል ከወደድሽው ታዲያ ምን አሳንሶ ነው..."

"3 ያጎደልሽበት ልትለኝ ነው አ"

"እንደዛ ነገር"

ከበፊቱ የበለጠ ነቃ እያለ ነው።....

....ይቀጥላል....

በአቤኒ የተፃፈ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19