Get Mystery Box with random crypto!

. እስኪ እንደምን ልሁንልሽ? ከመላዕክት ጋር ልሳቅ? ከሰይጣን ጋር ልልከፍ? | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

. እስኪ እንደምን ልሁንልሽ?

ከመላዕክት ጋር ልሳቅ?
ከሰይጣን ጋር ልልከፍ?
ከፀሀይ ጋር ሙግት ልያዝ?
በጨረቃ ውበት ልክነፍ?

እስኪ እንደምን ልሁንልሽ?

ልቆጣልሽ? ልሳቅልሽ ወይ ልከፋ?
ሌባ ልሁን ወይስ መንኩሼልሽ ቆቤን ልድፋ?

ደሞ እንደምን ልሁንልሽ?

ልሂድ?
ልሩጥ? ልቁምልሽ?
ዛሬ ሌሊት
ምን አይነት ህልም ላልምልሽ?

የኔ ነገ እንዲጥምሽ ባንቺ ነገም እንድትወጂኝ
ከተስማማሽ ስጪኝ ጤና ካሰኘሽም አሳብጂኝ

በቃል በኩል እኔ አልዋሽም ስሜቴን ነው የምፅፈው
ስሜቴንም አምነዋለሁ አንችኑ ነው የሚወደው

ለምን ትናንት አላውቅሽም የሚል ፀፀት አይነካኝም
ደሞስ ነገ አጣት ይሆን የሚል ጭንቀት አያውቀኝም

ኋላና ፊት አልገድብም ቅፅበት ላይ ነው የማቆምሽ
.....አሁን ላይ ነው የምወድሽ

እላለሁ እላለሁ

አልረታም ያለኝ ቃሌ አሁን ታጠፈ
ወትሮም ቀልብ የለውም ባንቺ የተለከፈ

እላለሁ እላለሁ

በየትኛው ጥበብ ይሄን አደረግሽኝ
በአይንሽ አባብለሽ እጄን የማረክሽኝ

እላለሁ እላለሁ

አንቺን ይንሳኝ እያልኩ ስናገር ይሰማል
አይደነቁብኝ ይሄ ምን ይገርማል
የአፍቃሪ ወጉ ነው በፍቅሩ ስም መማል

እላለሁ እላለሁ

ካላደረሰልኝ ካልቆረጠ በቀር ያለኝን ፍቅር ጥም
ለምን እፅፋለሁ? ምን ሊረባኝ ግጥም

ስላንቺ ለመጻፍ የዘረጋሁትን ወረቀት አጥፌ
አሁኔን ላጣጥም ልውደድሽ አርፌ

ዝግ ባለው ቀኔ 'ፍቅርየ' እያልኩሽ
እሰየው እሰየው እሰየው ወደድኩሽ

ስወድሽኮ!!!


በአቤኒ የተጻፈ


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19