Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ፫ ....'3 ያጎደልሽበት ልትለኝ ነው አ?' 'እንደዛ ነገር' ከበፊቱ የበለጠ ነቃ እያለ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ክፍል ፫

...."3 ያጎደልሽበት ልትለኝ ነው አ?"
"እንደዛ ነገር"
ከበፊቱ የበለጠ ነቃ እያለ ነው።

ለረጅም ጊዜ ያህል የምንተዋወቅ እየመሰልን ነው ካፌው ውስጥ የተከፈተውን ሙዚቃ በግማሽ ልቤ ሰማሁት መልኩን እንጂ ስሙን የማላውቀው ዘፋኝ እየዘፈነ ነበር
"...
ሊሆን የማይችል ድንገት የሆነ ድንገት ይሆናል
ጨበጥኩት ያሉት ከጉም ይበናል ከጉም ይበናል
የገባኝ እንዳልገባኝ እንዳልገባኝ
ያልገባኝ እንደገባኝ ገና አሁን ገባኝ
...."

ሙሉ ሀሳቤን ሰብስቦ ሊያዳምጠኝ ተሰናዳ ትንሽ አሰብ አርጌ

"እ..." ብየ ልቀጥል ስል ስልኬ ጠራ አነሳሁት

"ወየ ሜሪየ አወ እዛው ነኝ የምርሽን ነው? እና ዛሬ መገናኘታችን አያስፈልግም በይኛ አይ ብዙም አልደበረኝም ከሰው ጋር ነበርኩ እሺ በቃ ቻው ስመጣ እናወራለን ዝርዝሩን"

ስልኩን ከዘጋሁ በኋላ
"የመጣሁበት ቀጠሮ ተሰረዘ በቃ ልሂድ"
ውስጡን ክፍት እንዳለው አንዳች ነገሬ ሹክ አለኝ።

"ወዴት"

"ወደ ካዛንችስ"

"ቢያንስ የጀመርሽልኝን ሳትጨርሺ"
"እንዴ እሱንማ እጨርስልሀለሁ ባይሆን የማኪያቶ ትችለኛለህ"

"እሱ እንደፀባይሽ ነው" አለኝና ፈገግ አልኩ(አሁን የምሩን ነው ታውቆኛል ፈገግ እንዳለ)

"እሺ ምን ላይ ነበርን?"

"ከመፅሀፉ ያልተመቸሽን ልትነግሪኝ ነበር"

"ርዕሱ"

"ርዕሱ?" አለኝ ገርሞት

"አወ ምነው? ገረመህ? ርዕሱ ያላግባብ በዝቷል ብየ አስባለው ለኔ ርዕሱ ከውስጡ ሀሳብ በላይ ይጮሃል በዛ ላይ ውስጥ ያለውን ታሪክ በደንብ የገለፀልኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ብቻ አልሳበኝም የሽፋን ስዕሉም በቂ ሆኖ አልታየኝም በእርግጥ እዚም እዛም የወዳደቁ ጥርሶች አሉ እና ደሞ መልኳ በደንብ የማትለይ የደበዘዘች ግን ጎልታ እንድትታይ የተፈለገች ሴት እኔ ግን ከዚህም በላይ መሆን ይችል ነበር ብየ አስባለሁ ሌላው ደሞ ሴትን የሳለበት መንገድ አልተመቸኝም"

"ቢብራራ"

"ምን መሰለህ ብዙ ጊዜ እኔ ያጋጠሙኝ ፅሁፎች ላይ ሴቶችን ጅል ፣ በጣም ሞኝ በቀላሉ የሚታለሉ ያረጓቸዋል ያውም በወንድ 'ሞኝ ሴት ከብልጥ ወንድ የተሻለ ብልህ ናት' ሲባል አልሰማህም?" መለስ ያለ ፈገግታ አሳየኝና አንገቱን በአወንታ ነቀነቀልኝ(የሆነች 'ተንኮለኛ' ፈገግታም አሳየኝ)

"..ወይ ደግሞ በጣም በተቃራኒው በጣም ሲበዛ ብልጥ ነገረኛ ተንኮለኛ ያረጓቸዋል ትንሽ ይበዛል ባይ ነኝ እና መፅሀፉ ላይ ካሉት ባህሪያት ሁለቱ ሴቶች ያላግባብ ተጋነውብኛል አንዷ ያለአግባብ ጎላችብኝ አንዷ ደሞ ያላግባብ አነሰችብኝ"

"ግንኮ ሴቶች በጋራ እንዲህ ተብሎ የሚጠራ ባህሪ ቢኖራቸውም የተለየ የራሳቸው የሆነ ድምቀት ሊኖራቸው ይችላል።ምንአልባት እንደነዛ አይነት ሴቶችን ማለት ፈልጎ ከሆነስ"

"Of course ይችላል ግን በመፅሀፉ መሰረት ለነዛ ባህሪያት ያንን መብት የሚሰጥ Background ማለቴ የጀርባ ታሪክ አላገኘሁም።"

ፋታ ከወሰድኩ በኋላ
"እና ደግሞ አድራሻውን አላስቀመጠም ምንአልባት የሰው አስተያየት መስማት የማይወድ ግትር ይሆን? ብያለሁ ጉራ ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም አለኝ እንዳልኩህ ለመጨረስ ጥቂት ገፆች ይቀሩኛል በአጨራረሱ ያሳፍረኛል ብየ አልጠብቅም ባጭሩ ብታነበው አትጎዳም " አልኩት እነረ ንግግሬን ስትጨርስ ሙዚቃውም ወደማለቁ ነበር
"...የገባኝ እንዳልገባኝ እንዳልገባኝ
ያልገባኝ እንደገባኝ አሁን ገባኝ
እንዳልጠግነው
ሰዓቱ ረፍዷል ሰዓቱ ረፍዷል
የሆነው ሁሉ
እንዳይሆን ሆኗል እንዳይሆን ሆኗል
የገባኝ እንዳልገባኝ እንዳልገባኝ
ያልገባኝ እንደገባኝ አሁን ገባኝ..."

ተነሳሁ

"ወዴት ነው?"

"በቃ እንውጣ ማለቴ ልውጣ ይቅርታ ግን ከረበሽኩህ ችግር አለብኝ ሰው ከቀረብኩ እንዲሁ ነኝ የሆነ ርዕስ ካነሳህልኝ የማውቀው ከሆነ መሽቶ እስኪነጋ ላወራህ እችል ይሆናል። እንዲህ ስልህ ግን መስማት አልወድም ማለቴ አደለም እንደውም ከመናገር ማዳመጥን አስቀድማለሁ ሳይህ የሚያዋራህ ሰው የሚያስፈልግህ መስሎ ስለተሰማኝ ነበር የቀረብኩ አሁን ግን ልሄድ ነው ግን በጣም ይቅርታ እንደዛ ያስከፋህን ነገር ሳልጠይህ ልሄድ ነው"

"ልሄድ ነው? ሥዕሉስ?"

"እሱማ.." ብየ ሳቅ አልኩና አንዲት ግማሽ ሉክ ወረቀት ከመፅሀፉ ውስጥ አውጥቼ አቀበልኩት አየው ሩቅ የሚመሰጥ የሚመስል ከፊቱ ሻይ የቀረበለት ሰው ነው እሱ ራሱ ነው ሩቅ ተቀምጣ የሳለችኝ መሆኑ ነው? አለ ለራሱ

"እውነት ለመናገር ስልኬ ላይ ካሉት አብዛኞቹ ፎቶወች ይሄ ያምራል" አለኝ ሳቅኩለት

"ስንት ልክፈል?"

"እስከ ታክሲ ሸኘኝ"

"አልተወደደም?" በድጋሚ ሳቅኩለት (ሳቄ ግን ቀስ በቀስ ሞቀው ልበል?)

"እሺ ወዴት ነሽ? ኦ ለካ ካዛንችስ ብለሽኛል"

"አንተ ወዴት ነህ? "

"እኔ እንኳ እዚሁ 5 ኪሎ ነኝ በእግሬ ዎክ እያረኩ ነው የምሄደው"

ከፈለና ወጣን ትንሽ ወደታች ወረድን እና መንገዱን ተሻገርን

"ለማንኛውም መፅሀፉን ላውስህና አንብበው" ያቺን 'ተንኮለኛ' ፈገግታውን ፈገግ አለ

"እንዴ አንቺ ሳትጨርሽው?"

"ችግር የለውም ከጓደኛየ ተቀብየ እጨርሰዋለሁ እዚህ ካፌ ቁጭ ብየ አነበዋለሁ ብየ አስቤ ነበር እድሜ ላንተ ስታስለፈልፈኝ ዋልክ"

'ካዛንችስ 2 ሰው የሞላ 2 ሰው 2 ሰው የሞላ' የሚል ታክሲ ላይ ደረስን ረጅም ጊዜ እንደምንተዋወቅ ሁሉ ቻው ማለቱ ከፋኝ። ቻው ብየው ገባሁ በመጨረሻው ወንበር መስኮቱ ላይ ነበርና የተቀመጥኩት መስኮቱን ከፍቼ

"እኔ እምልህ..."
የጎደሉት ሰወች ገብተው ነበርና ሹፌሩ ሞተሩን ሲያስነሳ በወጣው ድምፅ ምክንያት ጥያቄየን አልሰማኝም መሰል ጠጋ ብሎ

"ምን አልሽኝ?"

"ስምህን? ስምህንኮ አልነገርከኝም"

ያቺን 'ተንኮለኛ' ፈገግታውን ካስቀደመ በኋላ
"አሮን"
"እ?"
"አሮን አሮን እጅጉ እባላለሁ" ፊቴ ላይ የመደነቅ ይሁን የመደንገጥ የመናደድ ይሁን የማፈር ስሜት እንዳስተናገድኩ የመታዘብ እድልን ሳይሰጠው ታክሲው መንቀሳቀስ ጀመረ።

ዞር ብየ ሳየው ቀስ እያለ ወደ 5 ኪሎ ማዝገም ጀምሯል።ነገሮችን እያስታወስኩ ሳቅ ሳቅ እያለኝ ነበር። ታክሲው ውስጥ የተከፈተው ሙዚቃ ተሰማኝ
"...ስቄ እሸኝሻለሁ....
ስቄ እሸኝሻለው ባዝንም የይስሙላ
ቀድመሽኝ መጥተሽ ከሄድሽ ወደ ሌላ..."

ቲሽ! ምን አይነቷ ነኝ ስልክ ቁጥሬን ሳልሰጠው



...ይቀጥላል...
በአቤኒ የተፃፈ


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19