Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ፭ '....መፈቀር ሁሉም ሊያገኘው የማይችል ፀጋ ነው' 'ደስ ይላል የምር በእናትህ ቀ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ክፍል ፭

"....መፈቀር ሁሉም ሊያገኘው የማይችል ፀጋ ነው"

"ደስ ይላል የምር በእናትህ ቀጥል"

"እስኪ የምንኖርበትን ምክንያት ከማየት እንጀምር ለምንድን ነው?ለማን ነው? የምንኖረው ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ምንድን ነው? ለሆነ ሰው አይደል? ለምንወደው፣ለምናስብለት፣ለምናፈቅረው፣ የኛ መኖር ግድ ለሚሰጠው ፣ ለሚያስደስተው ፣ለሚፈልገን ፣ለምናስፈልገው... መውደድ በቃ ራስሽን አሳልፈሽ ለወደድሽው ሰው መስጠት ነው ብየ አስባለሁ በነገራችን ላይ ራስን አሳልፎ መስጠት ስልሽ መሞት ማለቴ አደለም ዋጋ እንደምትሰጭው ማሳየት ማለት ነው በተለያየ መንገድ ለምሳሌ ብዙ ጊዜሽን ከዛ ሰው ጋር ማሳለፍ።መቼም ከማትፈልጊው ሰው ጋር አንድ ደቂቃ እንኳ ብትሆን ማሳለፉ ይከብድሻል ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ የፈለግሽውን ያህል ጊዜ አብረሻቸው ብታሳልፊ እንኳ ውስጥሽን የሚሰማሽ አንዳች ደስ የሚል ስሜት አለ። እሱን ስሜት ነው ለእኔ መውደድ የምለው ፍቅር ሲሆን ግን መስዋዕትነቱም ስሜቱም የበለጠ ከፍ ይላል አለ አደል በጣም በጣም መውደድሽ ይበዛና ስስት ያስጀምርሻል ሌላ ባላየው ትያለሽ ፤ ከሌላ ጋር ባያወራ ትመኛለሽ፤ከሌላ ጋር ባይሳሳቅ ባይጫወት ትመኛለሽ ፤ ብቻሽን ከዚህ ሰው ጋር ብትጠፊ ከዚች አለም ላይ አንድም የሚጎልብሽ ነገር እንደሌለ ይሰማሻል፤የሁሉ ነገርሽ መለኪያ እሱ ይሆናል።ፍቅር ውስጥ ሁሉም ነገሮች ከተፈቃሪው በታች ይሆናሉ። ሀገር ከእሱ አንፃር ተራ አፈር ትሆንብሻለች፤ ቤተሰቦችሽ ከእሱ አንፃር ምንም ስሜት የማይሰጡ የግለሰቦች ጥርቅም ይሆኑብሻል ፤ ምግብ እና እንቅልፍ ላንቺ ቅንጦት ይመስሉሻል ፤ ጎደለኝ የምትይውን ነገር ሁሉ በዚህ ሰው ትደፍኝዋለሽና። ፍቅር ሙሉነት ነው! በተፋቀሩ ሰወች መሀል ክፍት ቦታ አይኖርም።ፍቅር የማያልፈው መሰናክል፣ የማይዘለው ዝላይ፣ የማይስተው ጦር አይኖርም። ጣፋጭ ነው! ይስባል፣ ያጓጓል ግን ደግሞ በዛውም ልክ ያማል የፍቅር ህመም ግን ከሌሎቹ የሚለየው ህመሙ ራሱ መፈቀሩ ነው። መናፈቁ ህመም ፣ ተቃጥሮ መጠበቁ ህመም ፣ ቻው ተባብሎ መለያየቱ ህመም ህመም ህመም ህመም... ግን ያለእነዚህ ህመሞች ፍቅር ምንም ነው ምንም! የምታፈቅሪውን ሰው ስትናፍቂው ነው የበለጠ ምን ያህል እንደምትወጂው የሚገባሽ ከዛ በኋላ ህልምሽን ማጋራት ትጀምሪያለሽ ምንም የምትሰስችው ነገር አይኖርሽም ለዛ ሰው። ጊዜሽን ገንዘብሽን ሀሳብሽን ፍቅርሽን አካልሽን ምንም ነገርሽን ከዛ ሰው መደበቅ አይሆንልሽም ያ ተፈቃሪ እጅ ወደላይ አስብሎሻልና ምንምሽን ከዛ ቁጥጥር ማራቅ አትችይም እጅ ወደላይ የተባልሽበት መሳሪያው ፍቅር ስለሆነ..."

"እስኪ እንደውም በዛው ስለ ፍቅር ሕይወትህ አጫውተኝ ነግረኸኝ አታውቅምኮ" ሁኔታው ቅይርይር አለ ደህና የነበረው ፊቱ ባንዴው ጠወለገ
"ይቅርታ ማንሳት የማትፈልገውን ጉዳይ አነሳሁ መሰለኝ"

"አይ ችግር የለውም"

"እና ትነግረኛለህ?"

"ስለ ምኑ?"

"ስለ ፍቅር ሕ..."

"የለኝም"

"ስለበፊቷምኮ ሊሆን ይችላል..." ጮክ ብሎ አቋረጠኝና
"የበፊቷ አደለችም። የበፊቷ ፣ የድሮዋ ሲሉብኝ አልወድም" ደነገጥኩ ለረጅም ደቂቃ ዝም ተባባልን ምን ብየ ጨዋታ መቀየር እንዳለብኝ እያሰብኩ እያለ መናገር ጀመረ...

"ከልጅነታችን ጀምሮ በሚያስብል መልኩ አብረን ነው ያደግነው።ሁሌም ትምህርት ቤት የምሄደውም የምመለሰውም ከእሷ ጋር ነበር ቤቷ አስገብቻት ነበር መንገዴን የምቀጥለው ቤታቸውም ቢሆን ለኔ እንግዳየ አልነበረም ገብቼ እጫወት ነበር ወላጆቿም ቢሆኑ ይወዱኝ ነበር ለረጅም አመት እንደ እህቴ ነበረ የማያት 9ኛ ክፍል አካባቢ ስንደርስ ግን የተለየ ስሜት ይሰማኝ ጀመር በእህትነት አይን ብቻ ማየትን አልችል አልኩ። ይባስ ብሎ ደግሞ እሷ ላይ ሙሉ ውበትን ደፋባት።አይኗን ማየት ከእሳት በላይ የሚያቃጥል ጨረር ሆኖ ልቤን ያርደው ጀመር። ከጎኗ ሆኜ እያደገች፣እያማረች፣ እየተዋበች ፣እየፈካች ስትሄድ መታዘብ ሆነ ስራየ።ሙቀቷ አቃጠለኝ አሳሳችኝ! ሳሳሁላት። ከአይኔ እንዳትጠፋ መጠንቀቅ አበዛሁ ጎኔ ካልሆነች እየናፈቀችኝ ተቸገርኩ። ለረጅም ጊዜ የእህትነት ነው እያልኩ ራሴን ላታልለው ብሞክርም ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ። እንደፈለግኩ አወራትና አጫውታት የነበርኩት ልጅ አይኗን ሳይ ማፈር ጀመርኩ። ብቻየን መብሰልሰሌ ባሰና ዝምታ አበዛሁ።አንድ ቀን ግን ወሰንኩ። የተሰማኝን ልተነፍስላት ፤ ወደድኩሽ ልላት ፤ ልጽፍላት። ሁለት ሶስቴ ማሰብ ሳያስፈልገኝ በጥንቃቄ ባንዴው ፃፍኩት ነገር ግን ሌላ ስጋት ደርሶ ተደቀነብኝ ስነግራት አልፈልግም ፤ ከዚ በኋላ አታውቀኝም አላውቅህም ብትለኝስ አይኗን ሳላይ መዋሉን እንዴት እችለዋለሁ?እንዲሁ ፀጥ ብየ ከጎኗ ሆኜ ድምፄን አጥፍቼ ባፈቅራት ይሻላል የሚለው ሙግት አስቸገረኝ። ነገር ግን እኔ አፍኜው በጭንቀት ከምፈነዳ የመጣው ይምጣ ብየ ልገላገለው ወሰንኩ ከዛ በማግስቱ...." አለና አየር ወሰደ ታሪኩን ሲናገር ፊቱ ላይ በግልፅ የሚነበቡ ስሜቶች ይፈራረቃሉ ሁኔታው አጠገቡ ላለሁት ለእኔ ሳይሆን ለአምላኩ ወይም ለራሱ የሚተርክ ይመስላል

"..ከዛ በማግስቱ በቦርሳዋ ኪስ ላስቀምጥላት ወስኜ የፃፍኩትን በጥንቃቄ አጥፌ አዘጋጀሁና የእረፍት ሰአትን መጠባበቅ ጀመርኩ። ልክ እረፍት ስንወጣ አብሬአት ትንሽ ቆየሁና 'ቆይ መጣሁ' ብያት ወደክፍል ተመለስኩ የቦርሳዋን ትንሹን ክፍል ከፍቼ የጻፍኩትን ላስቀምጥ ስል በተመሳሳይ መልኩ የታጠፈ ወረቀት ተቀምጦ አገኘሁ። እጢየ ዱብ አለ አልቅስ አልቅስ አሰኘኝ የተቀደምኩ እንደሆነ ተሰማኝ ቦርሳዋን እንደነበረ ዘግቼ ምንም እንዳልተፈጠረ ልመለስ ስል ደግሞ አንዳች የልቤ ክፍል 'ቦርሳው ውስጥ ያለው ወረቀት እንደታጠፈ ነው ስለዚህ አላነበበችውም ማለት ነው እሱን አውጣና ያንተን አስቀምጠው' አለኝ ይሄኛው ሀሳቤም አሸነፈና ቦርሳዋ ውስጥ ያገኘሁትን ወረቀት አውጥቼ በኪሴ ይዤ የኔን ወረቀት ቦርሳዋ ውስጥ አርጌ እየሮጥኩ ወደእሷ ተመለስኩ። እስካሁን ስሟን አልነገርኩሽም አይደል ሪታ! ሪታ ትባላለች አይ እሷ! ቆንጆ ነበረች ቆንጆ የሚለው ከበቃት ክብ ፊቷ ላይ ፈጣሪ ጥበቤን አዩልኝ እያለ ያስቀመጣቸው የሚመስሉ አይኖቿ፣ ከንፈሯ ፣ ቀጥ ያለው አፍንጫዋ ብቻ ምን ልበልሽ በቃ ልቅም ያለች ቆንጆ። እና የዛን ቀን ያንን ወረቀት በእጄ ካስገባሁ በኋላ ቀኑን ሙሉ ሳስበው የነበረው ቤት ገብቼ ማን አባቱ ሊነጥቀኝ እንደነበረ አውቄ ለዚህ ሀሳቡ እንዴት አርጌ ልኩን እንደማሳየው ነበር። የቀኑ ትምህርት ሲያልቅ እንደተለመደው ቤት ካደረስኳት በኋላ ወደቤቴ ሮጥኩ። ወረቀቱን ለማየት ቸኩያለሁ ምኝታ ቤቴ ገብቼ ቦርሳየን ወዲያ ወርውሬ ልብሴን እንኳን ሳልቀይር ወረቀቱን አውጥቼ ማንበብ ጀመርኩ።ልክ ከፍቼ ማንበብ ስጀምር ፈፅሞ ያልጠበቅኩት ነገር ተፈጠረ የራሴን ያህል የማውቀው የእጅ ፅሁፍ የራሴን ያህል የማውቀው የፊደል አጣጣል ከአይኔ ገጠመ። ልቤ ምቷ ሲፈጥን ይታወቀኛል ላምን አልቻልኩም...."


...ይቀጥላል...

በአቤኒ የተጻፈ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19