Get Mystery Box with random crypto!

አስጨርሱኝ (በእውቀቱ ስዩም) አብቹ ወደ ስልጣን በመጣ ሰሞን ለቀቅ ያረግሁትን ሙገሳ ብጤ፥ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

አስጨርሱኝ
(በእውቀቱ ስዩም)

አብቹ ወደ ስልጣን በመጣ ሰሞን ለቀቅ ያረግሁትን ሙገሳ ብጤ፥ ከማህደሬ ፈልፍላችሁ በማውጣት “ ሙድ “ ለመያዝ የምትሞክሩ ሰዎች፥ ዲያብሎስ በብርድ ቀን፥ ቆለጣችሁን በጋመ ወረንጦ ይያዝላችሁ ከማለት ውጭ ክፉ አይወጣኝም!

በጊዜው ከነበረው የማሽቃበጥ ፏፏቴ አንጻር ሲታይኮ የኔ ግሳጼ ነው ማለት ይቻላል: በጊዜው ማሽቃበጡን ከፊት ሆነው ሲመሩት ከነበሩት አርቲስቶች አንዱ በቅርቡ “ ይሄ ስሙን ልጠራው የማልፈልገው ሰውየ” ሲል ሰማሁት፤ ለሽንገላ የፈጠነ ለርግማንም የሚቀድመው የለም፤ እኛ ግን ዛሬም በሚሆነው አዝነን፥ ሂስ ስናቀርብ “ ክቡር ጠቅላይ ምኒስትር “ የሚል ማእረጋቸውን አንነሳቸውም ::

ብቻ የሆነውን ሁሉ ሳስበው የልጅነቴን አንድ ገጠመኝ ያስታውሰኛል :: በብላቴናነት ዘመኔ ፥ የሰፈራችን ኗሪዎች ፥ የገና በአል መዋጮ ሰብስበው ፥ ፍሪዳ ጥለው ይቀራመታሉ፤ የተረፈው ተደግሶ ከተበላ ከተጠጣ በሁዋላ፥ ታዳሚዎች ስእለት ማቅረብ ይጀምራሉ::

መጀመርያ የበውቄ አባት ጋሽ ስዩም ተነሱ: :

“በሚቀጥለው አመት ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ ከፍሪዳው በፊት እምንቃመሳት አንድ ጠቦት ፍየል አስገባለሁ”

እልልልል!

ጨብጨብ

ቀጥለው የመዋእለ ህጻናት መምህርት ወይዘሮ እታገኝ ተነሱና “በሚቀጥለው አመት ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ፥ አንድ ጥዋ የስጋ ማባያ ድቁስ አቀርባለሁ”

አነስ ያለ ፥ የተድበሰበሰ ጭብጨባ ተሰማ::

በማስከተል፥ የሰፈሩ ጋሪ ነጂ ጋሽ በላይ ብድግ አለና ለሁለት ደቂቃ ሳይናገር ዝም ብሎ ተገተረ፤ ከዝያ ከእንቅልፉ እንደመባነን አለና” በሚቀጥለው አመት ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ …ደስ ይለኛል “ አለና ተቀመጠ::

እድምተኛው አጉረመረመ::

መጨረሻ ወይዘሮ ማሚት ተነሱ፤ ሻሻቸውን ነጠላቸውን አስተካከሉ፤ ጠላ የረጠበውን ያፋቸውን ጠርዝ ጠራረጉ ፤

“ በሚቀጥለው አመት ፤ ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ፥ አንድ ጋን ጠጅ ...”

እድርተኛው አላስጨረሳቸውም ፤ እስከ ሰላሌ የሚሰማ ጭብጨባ ወረደ! ደን ጠባቂው አቶ ቢረሳውማ ነሽጦት ብድግ አለና ፥ ከ”ነጻ ርምጃ ወዲህ “ ተተኩሶ የማያውቀውን አብራራው ጠመንጃውን ወደ ሰማይ ደግኖ ሁለት ጥይት ለቀቀ! በጭብጨባው እና በተኩሱ መሀል ወይዘሮ ማሚት “ አስጨርሱኛ ! “ ሲሉ እሰማለሁ::

ጭብጨባው በረድ ሲል ፥ የባሩዱ መአዛ ገልል ሲል ፥ ማሚት እንዲህ አሉ፤

“ በሚቀጥለው አመት ቢያደርሰን ቢያደርሳችሁ አንድ ጋን ጠጅ የሚያስንቅ ፤ ማንቆርቆርያ ሙሉ ጠላ አቀርባለሁ”: :


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19