Get Mystery Box with random crypto!

የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ (ሜሪ ፈለቀ) ክፍል 16 | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........


(ሜሪ ፈለቀ)

ክፍል 16

«ብዙውን አላውቅም። እየሆነ ስላለው ነገር ምንም እውቀት እንደሌለሽ ያወቁ ሰዓት ግን እንደሚገድሉሽ በአስር ጣቴ ፈርማለሁ። ስራ አቀለልሽላቸው!! አንቺም ከእነርሱ እኩል የሚፈልጉትን ማስረጃ የት እንዳለ የማታውቂ ፣ ገና እያፈላለግሽ እንደሆነ ልቦናቸው ካወቀ ምን ትሰሪላቸዋለሽ?»

«እኮ ያ ማለት ጠላታቸው አይደለሁም እኔን የሚያሳድዱበት ወንድሜንም የሚያፍኑበት ምክንያት የላቸውም!»

«አንችዬ ጅልም ነሽሳ? ያስታወስሽ ማግስት እንደገና ራስምታታቸው እንደምትሆኚ እያወቁ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ! ብለው እንዲሸኙሽ ነው የምታስቢ?»

«አንተስ የሆነ ቀን ማን እንደሆንክ እንደማስታውስ ግን በሀሳብህ ሽው ብሎ ያውቃል??»

«አይከፋኝም ዓለሜ!! ያኔ ከምታውቂኝ በላይ አሁን ነውስ ምታውቂኝ !!» አለ ዘወር ብሎ አይቶኝ መልሶ «ያለፈውን ብነግርሽ ታምኚኝ ይመስልሻል?»

«ስላልነገርከኝም እያመንኩህ አይደለም። ቢያንስ አውቄው ራሴ ልወስን!! ካልሆነ ግን እንድች ብዬ እግሬን ካንተጋ የትም አላነሳም!»

«አራት አስርት ዓመት እዝህች ምድር ባጀሁኮ!! ምኑን አውግቼሽ ምኑን ትቼው እዘልቀዋለሁ? የትየለሌ ነው!!» አለ በንግግሩ ብዙዙዙ እያስመሰለው።

«እኔ የ40 ዓመት ታሪክህ ምን ያደርግልኛል? እኔ ደጅ ያደረሰህን ታሪክ ነው የምፈልገው። አንድ ዓመት ያከረመህንም!!» በረዥሙ ተነፈሰ። ሁል ጊዜ እንደሚያደርገው። ሊነግረኝ ነው ብዬ ስጠብቅ አጀማመሩን አርዝሞ የቆመ ጆሮዬን ኩም እንደሚያደርገው

«አንዱ ከሌላው ይተሳሰራል። ሁሉን ካልነገርኩሽ ቁንፅል ነው የሚሆን። እንደው በጥቅሉ ደጅሽ ያመጣኝ እንዳልኩት ሰው ነው። ደጅሽ ያቆየኝ አንድ እለት የዋልሽልኝ ውለታ ነው!» ብሎ የማንነቱን እንቆቅልሽ ሁሉ የፈታልኝ ይመስል ጭጭ አለ። ተናደድኩ።

«ኸረ? ውለታ? እያዋረድኩህ እንኳን ደጄ የነበርከው ለአንድ እለት ውለታ ነው? ትንሽ እንኳን የሚመስል ነገር ብታወራ ምን አለበት? ማስታወስ እንጂ ያቃተኝ ጡጦ የሚጠባ ህፃን እኮ አይደለሁም!!»

«ምንአለበት? የሰው ልጅ ለአንዲት ቀን በደል እድሜውን ሙሉ ቂም ይዞ ይኖር የለ? ለአንዲት ቀን በደል ለዓመታት በቀል ሲጎነጎን ይከርም የለ? ምናለበት ለአንዲት ቀን ደግነት ብዙ ዓመት ደግ ቢሆን?» ዋናውን ርዕስ እየሸሸ መሆኑ ገብቶኛል። ስልኬ ላይ መልዕክት ገባ።

«ምሽት 2 ሰዓት ላይ ፒክ የሚያደርጉሽ ሰዎች በዚህ አድራሻ ይጠብቁሻል። ሰው አይደለም የሰው ጥላ ቢከተልሽ ያልኩሽን አትርሺ!! የምልክልሽን ስጦታ!!» ይላል። ምን እንደሆነ እንድነግረው ዘወር ብሎ እያየ ይጠብቃል።

«እናቴ ናት!! በአጎቴ ስልክ ደህና መግባታችንን ለማወቅ ነው መልእክት የላከችው።» አልኩት።

ለመጀመሪያ ጊዜ ዋሸሁት! ለመጀመሪያ ጊዜ ደበቅኩት። ግን ልክ ያደረግኩ መሰለኝ አልከፋኝም!! አዲስ አበባ ገብተን ለምናልባቱ የተሻለ ፍንጭ ካገኘን ቃሊቲ እየሄድን ነው። በልቤ ወስኜ ጨርሻለሁ። ከቃሊቲ መልስ ፣ መልስ ባገኝም ባላገኝም ጎንጥን የሆነ ቦታ አመልጠዋለሁ። ለሽንቴ እንኳን ስወርድ ልጠፋበት እንደምችል ጠርጥሮ መሰለኝ በቆቅ አይኖቹ ይከተለኛል። እንዴት እንደማመልጠው አላውቅም። ግን ከእርሱ ጋር የሚቀጥለውን እርምጃ አልራመድም። አሁን ላይ ማንን እና ምን እንደማምን ግራ ገባኝ። ለምኜዋለሁኮ ስላለፈው ህይወቴ የሚያውቀውን እንዲነግረኝ። ምንም እንደማያውቅ ሲነግረኝ አምኜው ምንም ሳልደብቀው በእሱ ላይ ዘጭ ብዬ እምነቴን ስጥልበት ትንሽ እንኳን አይከብደውም? የምሸሸው ምን እንደሆነ እንኳን ሳላውቅ በፍርሃት ነፍሴ ሲርድ እና ስፈራ አላሳዝነውም? እርሱን ከምንም በላይ አምኜኮ ለሳምንታት እጁን ይዤ እንቅልፌን ተኝቻለሁ። ምን ይሆን ያስብ የነበረው? በልቡ <አይ ሞኞ> ብሎኝ ይሆን?

«እመቤት በአንድ ወቅት ከእነርሱ ወገን የነበረች ጋዜጠኛ መሆኗን ሰምቻለሁ። ወዳጃምነታችሁ እምንድረስ እንደነበር የማውቀው ባይኖረኝም ለጊዜው መዘንጋትሽን ግልፅልፅ አድርገሽ ባትነግሪያት እመክርሻለሁ።» አለኝ ልንቃረብ ገደማ። አስቤ የነበረው ሁሉንም ነግሪያት የምታውቀውን መጠየቅ ስለነበር ካልጠየቅኳት የመሄዴ ትርጉም ራሱ ምን እንደሆነ ግራ ገባኝ። ቢሆንም ሄድን!!


በሩ ላይ ስንደርስ የሆነ ልጅ እግር ጠባቂ «ይሄ ባሻሽ ሰዓት እየመጣሽ እገሌን ጥሩልኝ የምትዪበት የጎረቤትሽ ቤት መሰለሽ እንዴ? እስረኛ መጠየቂያ ቀንና ሰዓት አለውኮ!!» ብሎ ፊቱን ወደ ውስጥ መለሰ
«እናውቃለን! እንደው የሞት ሽረት ጉዳይ ገጥሞን ነው! እንደው ለ2 ደቂቃ!» አለ ጎንጥ
«አትሰማኝም እንዴ ሰውየው? ስራዬን ልስራበት ከዚህ ራቁ!! እንደውም እዚህ አቅራቢያም መቆም አይቻልም ዞር በሉ ብያለሁ።» ብሎ አምባረቀ። ምንም ተስፋ እንደሌለው ሲገባኝ

«እሺ የእስረኛ መጠየቂያ ቀን መቼ ነው?» አልኩ። ይሄኔ ሌላኛው በእድሜ በሰል ያለ ጠባቂ «ምንድነው? » እያለ ብቅ አለ። ልጅ እግሩ ምንም የሚለንን የማንሰማ መሆናችንን እያብራራለት ሰውየው እኔን በትኩረት ካየ በኋላ

«አጅሪት? መቼም ካንቺ ውጪ እዚህ በር ላይ ሁከት የሚፈጥር የለም!! ስትጠፊኮ ሌላ ቦታ ሸቤ ገብታ ነው ወይም ከባርች ጋር ተጣልታ! ብለን አስይዘን ነበር። ኸረ ለውጥ ቁርጠቴ በቀሚስ?» አለኝ። አወራሩ የእስር ቤት ጠባቂ ሳይሆን የሆነ የወዳጅነት ነው። ልጅ እግሩ ጠባቂ ግራ ገብቶት ያየዋል። « ከባርች ጋር ተጣልታችሁ ነው መምጣት ያቆምሽው??» ካለኝ በኋላ ወደልጅ እግሩ ጠባቂ ዞሮ « …. ቁርጠቴ የሴቶቹ ካቦ ነበረች እዚህ እያለች።» ሲል ልጅ እግሩ የሆነ ነገር እንደማስታወስ ብሎ ከላይ እስከታች ካየኝ በኋላ « ቁርጠቴ ማለት እሷ ናት? የሰማሁትን አትመስልም!» አለ

« ምን እንታዘዝ ታዲያ? መጠየቂያ ቀን አለመሆኑን ታውቂያለሽ መቼም!!» አለ በሰል ያለው ጠባቂ ወደ እኔ እየተጠጋ
«ብያለሁ አልሰማ ብለውኝ ነው። እመቤት የምትባል ነው የሚሉት?» አለ ልጅ እግሩ እኔ ሰውየው የሚጠራቸው ቅፅል ስሞች የማን እንደሆኑ ሳላውቅ ያለቦታው ሰክቼ ስህተት እንዳልሰራ ስደነባበር። ንግግሩ ያለመፍቀድ ዓይነት አይደለም። የመፍቀድም አይነት አይደለም። ግራ የገባ ነገር አለው። ይሄኔ ጎንጥ ጠጋ ብሎ እየጨበጠው

«እግዜር ይስጥልን ጌታዬ!! የሞት ሽረት ጉዳይ ባይሆን ካለቀኑ መጥተን ባላስቸገርን!!» አለው። ሰውየው ሳቅ ብሎ የጨበጠበት እጁን ከልጅ እግሩ ጠባቂ ደበቅ አድርጎ ገለጠው። ገንዘብ ነው ያቀበለው። ገንዘብ መፈለጉ እንዴት ገባው? ቆይ እሱ የማያውቀው ነገር ምንድነው? ሰውየው ዞር ብሎ ለልጅ እግሩ እመቤት ያለችበትን ምድብ ይመስለኛል የሆነ ቁጥር ነግሮት እንዲጠራ አዘዘው። ልጁ እየተነጫነጨ የተባለውን አደረገ። ምን መጠየቅ እንዳለብኝ እና እንደሌለብኝ መወሰን አቃተኝ። እንደማላስታውሳትስ መንገር አለብኝ? እሷስ የእኔ ወዳጅ ናት ወይስ እንደጎንጥ ማንነቷን የደበቀችኝ ሴት? የስራውን ይስጠው እንኳን ጠርጥርትያት ብሎ ሹክ ብሎኝ እንዲሁም ጥላዬን የምጠራጠር ጠርጣራ አድርጎኛል:: ስትደርስ ለቅሶ እና ሳቅ የተደባለቀው ነገር ሆነች። በእኔ ተመሳሳይ እድሜ የምትገኝ ዓይነት ሴት ናት። ጎንጥ ጆሮውን ቢተክል የምናወራውን ሊሰማ በሚችልበት ርቀት ቆሟል።