Get Mystery Box with random crypto!

«በህይወት አለሽ? በህይወት እያለሽ ነው ልታዪኝ ያልፈለግሽው? ምን ሆነሽ እንደሆነ ብቻ ንገሪኝ? | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

«በህይወት አለሽ? በህይወት እያለሽ ነው ልታዪኝ ያልፈለግሽው? ምን ሆነሽ እንደሆነ ብቻ ንገሪኝ? ደህና ሆነሽ ነው?» እያለች ማልቀስ ጀመረች። በጥይት መመታቴን ነገርኳት። መርሳቴን ግን ዘለልኩት። ደግሞ ወቀሳዋን ትታ ለእኔ ማዘን ጀመረች። ዞር ብላ ጎንጥን በ<ማንነው ?> አይነት ምልክት ሰጠችኝ። አጠያየቋ እንደምነግራት እርግጠኛ የሆነ ነው። የቀረቤታዋ ልክ ብዙ ነገር የምናወራ ሰዎች እንደነበርን ያስታውቃል።

«ጎንጥ ዘበኛዬ ነበር።» አልኳት። ለምን <ነበር> እንዳልኳት አላውቅም!
«ጎንጥ ጎንጤ? ጎንጤ ጥጋቡ? » ብላ ጮኸች። ስለጎንጥ የምታውቀው ምን እንደሆነ ባላውቅም የግርምት አጯጯኋ ስለዘበኝነቱ ብቻ እንዳልነገርኳት ያስታውቃል። ለአንድ አፍታ ሁሉንም ዝርግፍ አድርጌ ነግሬያት የምታውቀውን ብትነግረኝ ተመኘሁ።

«ኪዳንን ይዘውታል! ቪዲዮዎቹን ካልሰጠኋቸው እንደሚገድሉት ነግረውኛል።» አልኳት የማወራው ነገር አዲሷ እንደማይሆን እርግጠኛ ሆኜ።

«ኪዳን ምን ሊሰራ መጥቶ አገኙት? ሺት!! እርግጠኛ ነሽ? እኚህ አጋሰሶች!! የፈራሽው አልቀረም!! » ብላ በድንጋጤ እና በንዴት መሃል ዝም አለች።
«አዎ በቪዲዮ አይቼዋለሁ። አውርቼዋለሁም። ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ?» አልኳት ሌላ ፍንጭ ከሰጠችኝ ብዬ
«መቼም አትሰጫቸውማ? ሌላ መላ መቼም አይጠፋሽምኣ? »
«በኪዳን ነፍስ ቁማር መጫወትም አልችልም!»
«እየቀለድኩ ነው በይኝ!! ጥይቱ የዋህ አድርጎሻል ልበል? ወይስ ሚሞርሽንም ነው ያጠበልሽ?» ያለችው ለአባባል ነበር እኔ ግን አዎ ብያት ሁሉንም ብትነግረኝ ፈለግኩ። የጎንጥን ማስጠንቀቂያ ችላ ማለትም ከበደኝ። እራሱን ሳላምነው ቃሉን ለምን እንደማምን ምክንያት የለኝም። ግን መጠንቀቅ አይከፋም። እሷ ቀጠል አድርጋ

«ከዚህ በፊት ከእጃቸው ፈልቅቀሽ ወስደሽዋል። አሁንም ተረጋግተሽ አስቢ እና መላ አታጪም!!»
«ተረጋግቼ የማስብበት ጊዜ የለኝም!! የሰጡኝ ሰዓት ሊያልቅ ሶስት ሰዓት ነው የቀረው!» ስላት የሆነ ግራ ያጋባኋት አይነት በጥያቄ አስተዋለችኝ። አለባበሴን ጭምር በዓይኗ ለቀመች እና
«ምንድነው እሱ? ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ መልፈስፈስ ያወቅሽበት? የሆነማ ልክ ያልሆነ ነገር አለ። ደግሞ ልስጣቸውም ብትይ ሴትየዋን በ3 ሰዓታት ውስጥ አጊንተሽ አንደኛውን ኮፒ ልትቀበያት አትችዪም!! ነው ወይስ ኦልረዲ አጊንተሻታል?»

«ሴትየዋን?» ካልኩ በኋላ ሳላስበው « የአቅሜን እሞክራለኋ» አልኳት መልሼ!! መልስ የሰጠችኝ መሰለኝ። ለሰዎቹ የሰጡኝን የጊዜ ገደብ ማራዘሚያ ምክንያት!! የምጠይቃት ብዙ ቢኖርም!! በምን መንገድ እን,ደምጠይቃት ካለማወቄ የእሱን እንቢታ ጥሶ ሌላኛው ጠባቂ እመቤትን እንዲጠራልኝ ያስገደደው ልጅ እግር ጠባቂ ሰዓታችን ማለቁን ከግልምጫ ጋር ይነግረኛል። ለእመቤት መልሼ እንደምመጣ ነግሬያት። ወደከተማ መመለስ ጀመርን።

«ሴትየዋ ያለችሽ ማን ትሆን?» ሲለኝ ያወራነውን ሁሉ እንደለቀመ ገባኝ።
«አላውቅም! መርሳትሽን አትንገሪያት አላልክም? ማናት ብዬ እንዴት መጠየቅ እችላለሁ? ሁሉን ነገር ታውቅ የለ? ይሄ እንዴት አመለጠህ?» ብዬ ጮህኩበት

«ታዲያ ምን የሚያስቆጣ ተናገርሁ? ቃሌን ያለማመንና ሴትዮይቱን ማመንምኮ ያንቺ ድርሻ ነበር።» አለ ተረጋግቶ።

«ለማንኛውም እቤት ንዳኝ!! ተረጋግቼ የማስብበት ሰዓት እፈልጋለሁ።» አልኩኝ። ከዛ ማውራት የእሱ ተራ ዝም ማለት የእኔ ተራ ሆነ።

« አሁን እኔና አንቺ አንባጓሮ የምንፈጥርበት ሰዓት አይደለም! በአንድነት መላ ብንዘይድ አይበጅም? ከሰውየው ጠባቂዎች አንዱ ወዳጄ ነው። ኪዳን ያለበትን አድራሻ ማግኘት ከቻልን መልዕክት አኑሬለታለሁ። እስታሁን የምትመጪበትን አድራሻ አልላኩም? መላክ ነበረባቸው!! ትክክለኛ አድራሻውን እንደማይልኩልሽ ግልጥ ነው። ከሆነ ቦታ ይቀጥሩሽና ነው በራሳቸው መኪና የሚወስዱሽ!! እርግጥ አድራሻውን ከደረስንበት እነርሱ የቀጠሩሽ ቦታ ሲመጡ እኛ ቀድመናቸው ቦታው እንደርስ ነበር ….. » እሱ እቅዱን ከጅምር እስከ ፍፃሜ ሲነግረኝ እኔ ደግሞ የራሴን እቅድ ከጅምር እስከ ፍፃሜ የሌለው አቅዳለሁ። እቤት እንደደረስን እዛ መሳቢያ ውስጥ ያለውን ሽጉጥ እወስዳለሁ። ምን እንደማደርግበት የማውቀው የለኝም። በሆነ መላ ከጎንጥ እሰወራለሁ። የቀጠሩኝ ቦታ ብቻዬን እሄዳለሁ። የሚወስዱኝ ቦታ ስደርስ (ኪዳን ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ) ሁሉንም ኮፒ ለማግኘት በቂ ጊዜ ስላልነበረኝ ተጨማሪ አንድ ቀን እንዲሰጡኝ እጠይቃለሁ። የሚፈልጉት ቪዲዮ የዚን ያህል አንገብጋቢ ከሆነ አይገድሉኝም። የጠየቅኩትን ጊዜ ይሰጡኛል። በተቃራኒው ሊሆን እንደሚችል ሳስብ ልቤ ይደልቃል:: ትልቁ ፍላጎቴ ግን ለትንሽ ደቂቃ ከወንድሜ ጋር እንዲተውኝ ማድረግ ነው። ብቸኛ ላምነው የምችለው እና ሊያውቅ የሚችል ሰው እሱ ነው። ይሄ ጎንጥ እንዳለው የጅል እቅድ ሊሆን ይችላል። እጄን አጣጥፌ እየጠረጠርኩት ያለሁትን ጎንጥን ከመከተል ውጪ ሌላ የተሻለ እቅድ ግን የለም። ያን ደግሞ አላደርግም!!

እቤት እንደደረስን ተናኜ የማያቆም ጥያቄ እና ወሬ ታከታትላለች። እንደማልሰማት እንኳን የምታስተውልበት ፋታ አትወስድም። ጎንጥ ከገባ ጀምሮ በሩ ላይ እንደተገተረ ነው። ጮክ ብዬ ጎንጥ እንዲሰማ

« አንድ ላይ የምንበላው እራት አሰናጂ!! ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም! እራት አንድ ላይ እንቋደስ!» አልኩኝ ለእሷ ግራ እንደሚያጋባት ሳልረዳ

«ምነው እትይ የት ልትሄጅ ነው?»
«የትም አልሄድ! ያልኩሽን ዝም ብለሽ አድርጊ!» አልኳት። ቅር እያላት ገባች። ለመሄድ የሚያስፈልገኝን ነገር ካሰናዳሁ በኋላ ጥርጣሬውን ለመቀነስ ልብሴን አልቀየርኩትም። እራት ሶስታችንም ቀርበን እየበላን። አስተያየቱ እንዳላመነኝ፣ ነገረ ስራዬ እንዳላማረው ያስታውቃል።

«አድራሻውን ልከውልኛል።» አልኩት
«የት ነውስ?» አለ ቀና ብሎ ስልኬን እንድሰጠው መሰለኝ እጁን እየዘረጋ። ስልኬን የለበስኩት ሹራብ ኪስ ውስጥ የከተትኩት ለራሴ እቅድ እንዲመቸኝ በመሆኑ እጁን ችላ ብዬ

«እንዳልከው ነው። ቀበና የሚባል ሰፈር የሆነ ካፌ ፊትለፊት ነው። ስልኬ መኝታ ቤት ነው አሳይሃለሁ። ከዛ ነው ከእነርሱ ጋር ሊወስዱኝ ያሰቡት! ምንድነው የምናደርገው? ወዳጅህ እስከአሁን አልመለሰልህም?።» አልኩት። ይመነኝ አይመነኝ ባላውቅም በእርሱ እቅድ እየተመራሁ እንደሆነ እንዲመስል ጣርኩ። አስተያየቱ ያመነኝ አይመስልም። ከጎሮሮዬ አልወርድ ያለውን እህል እንደምንም ካጋመስኩ በኋላ

« …… በልተሽ ስትጨርሺ እዚህ ላይ አንድ ስኒ ቡና ብታጠጪኝ ደግሞ?» አልኳት ተናኜን። ልትነሳ ሲዳዳት ተረጋግታ እንድትጨርስ ነግሪያት ወደጓዳ እጄን እንደሚታጠብ ሰው ገባሁ። እጅ መታጠቢያውን ውሃ ክፍት አድርጌ አስቀድሜ ክፍቱን በተውኳቸው በሮች የምፈልገውን ይዤ በጓዳ ወጣሁ። መጣ አልመጣ አድብቼ እየተርበተበትኩ የአጥሩን በር ከፍቼ ስወጣ ከኋላዬ የሚያባርረኝ ያለ ነበር የሚመስለው አሯሯጤ። የቤቴ በር ከአይኔ እስኪሰወር እሮጥኩ። ያገኘሁትን ታክሲ አስቁሜ ወደተላከልኝ አድራሻ እየሄድኩ።

«ማን ስለሆነ ነው ቆይ እንዲህ የምደበቀው? ያውም በገዛ ቤቴ?» እላለሁ በልቤ!!

.......... ይቀጥላል........

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19