Get Mystery Box with random crypto!

ከዛን ቀን በኋላ በአፉ ምንም ባይናገርም አስተያየቱ ተቀየረ። ዓይኖቹን ሳይነቅል ሲያፈጥብኝ ቆዳዬን | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ከዛን ቀን በኋላ በአፉ ምንም ባይናገርም አስተያየቱ ተቀየረ። ዓይኖቹን ሳይነቅል ሲያፈጥብኝ ቆዳዬን ያሳክከኛል። ተስተካክዬ መቆም ያቅተኛል። ከቀናት በኋላ ሆነ ብሎ እዛ ቤት እንድንሄድ አደረገ እና በሴቶቹ ፋንታ ሙሉሰው እንዲመጣ ጠየቀ። ሙሉሰው ከአንድ ጠባቂው ጋር መጥቶ በወዳጅ ሰላምታ ማሽቃበጥ ያበዛበት ዓይነት ሰላም ብሎት ተቀመጠ። ዘለሽ እነቂው እነቂው የሚለኝን ስሜቴን ተቆጣጥሬ ቆምኩ። ሆነ ብሎ እሱ ፈላጭ ቆራጭ መሆኑን ሊያሳያኝ ያደረገው ነገር እንደሆነ ያስታውቅበታል። ቢገጣጠም የማይቀና አማርኛ እያወራ በአይኑ እኔን ያጠናል። ሙሉሰው ወጥቶ ሲሄድ «የዚን ያህል ቀላል ነበር።» ብቻ ብሎ ዝም አለ።

ለሳምንታት በራሴ መንገድ መረጃ ላገኝ ዳከርኩ። ሌላው ቀርቶ ጭፈራ ቤቱ እንኳን ድንገት የሆነ ሰዓት ነው እንጂ የሚመጣው ማንም ሰው የሚመጣበትን ሰዓት አያውቅም። ድንገት እድለኛ ሆኜ እንኳን ባገኘው ጠባቂ አለው!! ከዛ ግን ያ ሰይጣን ሰውዬ ያቀበለኝ ሀሳብ ውስጤ ቀስ በቀስ ማደጉን ያወቅኩት። ባገኘሁት አጋጣሚ ልገድለው አለመፈለጌ ገባኝ!! ቁጭ ብዬ አስቤ አስቤ ማሰሪያዬ <ከነነፍሱ እፈልገዋለሁ! የዛን ቀን አብረውት የነበሩትን ስማቸውን የማላውቃቸውን ጨምሮ መረጃ ይሰጠኛል። እንደውም እሱ መጨረሻ ላይ ነው መሞት ያለበት!> የሚል ሆነ። ሊሆን የማይችል ቅዠት ይመስለኛል ግን ማሰብ ማቆም አቃተኝ። ግን እንዴት? አላውቅም!!!

«እሺ!» አልኩኝ ጠብ የሚል ነገር ከሌለው ብዙ ልፋት በኋላ!! «ነገር ግን በቅድሚያ የማገኘውን ነገር በዝርዝር ማወቅ እፈልጋለሁ!»

ክብሬን ሸጬ በቀል ሸመትኩበት!!! ካሰብኩት በላይ ነገሮች ቀለሉልኝና የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ኖረኝ። እኔ ግን ጎደልኩ!! ለቀናት እራሴው እሺ ብዬ ተስማምቼ የተኛሁ ሳይሆን እንደእናቴ የተደፈርኩ አይነት ስሜት ተሰማኝ። በእንባ የማላጥበው ዓይነት መቆሸሽ ሆነብኝ!! <ጥላቻ ከፍቅር ያይላል> ያለው ይሄን መሰለኝ። የገዛ ሰውነቴ የሆነ ቦታ አስቀምጬው መንቀሳቀስ ብችል አሰኘኝ። ይሄን የውስጤን ጩኸት ላለመስማት በነጋ በጠባ ሴራ መጎንጎን ሆነ ስራዬ!! ከረጠቡ አይቀር መበስበስ ነው በክፋት ተጠመቅኩ። ተንኮል አስራለሁ እፈታለሁ!! ደጋግሜ ረከስኩ!! ደጋግሜ ራሴን ረሳሁ።

ሙሉሰውን እንዲወደኝ አድርጌው አይደለም ያገባሁት!! እጁ ባይያዝበት የመጀመሪያ መግደል የሚፈልገው ሰው እኔ ነኝ!! እንዲያገባኝ አስገድጄው እንጂ!! አብዛኛው ባለስልጣን አንድ የሆነ ድክመት ወይ አንድ የሆነ ቆሻሻ ይኖረዋል። ወይ በሚስቱ ላይ ሲማግጥ ወይ በሃገር ላይ ሲማግጥ ብቻ የሆነ መረጃ ይገኝበታል። ሙሉሰው አስለፋን!! ጭራሽ ምንም ማግኘት ከበደ። በዘመድ አዝማዱ ስም ጭምር የያዛቸው ንብረቶች እና ከሀገር የዘረፋቸው ሀብቶች ማስፈራሪያ ሊሆን ቢችልም በቀላሉ በገንዘብ ሃይል መረጃዎቹን ድራሻቸውን ማስጠፋት ይችላል። የራቁት ጭፈራ ቤቱ ውስጥ በጓሮ ተሹለኩልከው የሚገቡትን ባለስልጣናት በቀላሉ በሴቶቹ ማጥመድ ይቻላል። እሱ ግን ከሴት ጋርም በፍፁም ምንም አይነት ንኪኪ የሌለው ሆኖ ተገኘ። ምናልባት ቤቱ የሱ ስለሆነ ሰራተኞቹ ባሉበት መልከስከስ ስለማይፈልግ ነው ብለን አስበን። (በሃሳቡ ተስማማሁ እንጂ ሀሳቡን የሚያመነጨው አለቃዬ ነው) እቤቱ የምትሰራዋን ሰራተኛ ያዝናት። ጭራሽ እንደውም በበጎ አድራጎት የሚታወቅ ከላዩ ላይ ዝንቡን እሽ ብል ግር ብሎ የሚወጣለት ህዝብ ያሰለፈ ሰው ነው። እጅ ወደመስጠቱ ስንቃረብ ከስንት መላምትና ልፋት በኋላ ማንም ሰውጋ የማይሰማ ማንም ሰው የማይገምተው ብልግና እቤቱ ሸሽጎ እንደሚኖር ደረስንበት። ሊያሳድገው ከገጠር ያመጣው እቤት አብሮት የሚኖር ዘመድ አለው። ደፍሮት አሁንም እያስገደደው ያባልገዋል። ከዚህ ሰውዬጋ መዋል ከጀመርኩ በኋላ ብዙ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ብልግናዎች ሰምቻለሁኮ ይሄ ግን ወደር የማይገኝለት ነበር። ከብዙ ሙከራ በኋላ ብልግናውን ቀረፅነው!! ይሄ ነው እጄ ላይ የጣለው!!

ለዘመናት የናፈቅኩት ቀን ተከሰተ እና ፊት ለፊት ተገናኘን። ውርደቱ እጄ ላይ እንዳለ ስነግረው ፊቱን ማየት ለቀናት ሲያቅበጠብጠኝ ነበር። እዛው የራቁት ጭፈራ ቤቱ ከአለቃዬ ጋር ሄደን እሱ ሲመጣ እንዲጎበኘው መልዕክት አስቀመጠ። እዚህ ጋር የማይገባኝ አለቃዬ በእኔ በቀል የሚሰክረው ጉዱ ነበር። ልክ መጥቶ እንደተቀመጠ።

«ሜላት እባላለሁ! ወይም ደግሞ አባቴ ባወጣልኝ ስም አምሳል!» አልኩት እና የአባቴን ማንነት ቀዬዬን እና የዛን ቀን ተፈጥሮ የነበረውን ሳላዛንፍ ነገርኩት። ምንም ታክል የፀፀት ስሜት ሽው ባላለው አነጋገር

«ጦርነት ነው የገጠምነው!! ልንስማችሁ አልነበረም የመጣነው!! እንኳን አንቺ ማን እንደሆንሽ አባትሽንም አላስታውሰውም!» ሲለኝ እሱን ለመበቀል የሄድኩት መንገድ ልክ ነው ብዬ አመንኩ። ቪዲዮውን ላኩለት እና ምንም ከማሰቡ በፊት አንድ ቅጂ አለቃዬ ጋር ፣ ሌላ ቅጂ ተቀባብሎ ሌላ ሰው ጋር መኖሩን ነገርኩት!! አንድ ነገር ሊያደርገኝ ቢያስብ መረጃውን ከመውጣት እንደማያግደው ሲያውቅ ተሰበሰበ።

«እሺ ምንድነው የምትፈልጊው? ምን ያህል?» ብሎ ራሴን የሸጥኩበትን በቀሌን በገንዘብ ተመነብኝ

«ገንዘብ አይደለም የምፈልገው!! እንድታገባኝ ነው የምፈልገው!!» ስለው በቁሙ ቃዠ።

«ቀልድ ነው የያዝሽው? ጤነኛ ነሽ?» ሲል አለቃዬ በወልካፋ አማርኛ ቅልብ አድርጎ
«ውነቷን ነው! ቀልድ የለም!» አለው።
«ምን አስበሽ ነው?»

«አታስብ ጠዋት ከእንቅልፋችን አንድ ላይ ተነስተን ፣ ደህና አደርሽ ፣ ደህና አደርክ የምንባባል፣ ቁርስ አንድ ላይ የምንበላ ሰዎች አንሆንም!! አንድ ቤትም አንኖርም! ሚዲያዎች የሚዘግቡት ሰርግ ደግሰህ እንጋባለን!! አብረን አንኖርም እንጂ የትም ቦታ ስትሄድ እጄን እጅህ ውስጥ ሻጥ አድርገህ ትሄዳለህ!! ከዛ የቀረውን እያኖርን እንመካከራለን!! ውሳኔህን እንድታሳውኝ 2 ቀን እሰጥሃለሁ። ያው አማራጭ የምትለውን በሙሉ አይተህ እንደማያዋጣ ትደርስበታለህ!!» ተወራጭቶ ወጣ!! እንደምገምተው አማራጭ ሊሆን ይችላል ብሎ የሚያስበውን ሁሉ አስቧል። ጉዱን ለማንም እንደማያዋየው ግልፅ ነው!!

ቪዲዮው ቢወጣ በመድፈር ወንጀል ብቻ አይደለም የሚከሰሰው በፍቅር ከፍ አድርጎ የሰቀለው ራሱ ህዝብ በድንጋይ ወግሮ እንደሚገድለው ያውቃል። ሰው ገደለ፣ ሀገር ከዳ ፣ ሰረቀ …… ምንም ቢባል ኸረ ምንም ጥፋት ቢሆን ይታለፍለታል። ይሄን ግን አያልፉለትም።
በሁለተኛው ቀን መስማማቱን ላከብኝ!! በአደባባይ ሀገር ጉድ ያሰኘ ሰርግ ደግሶ አገባኝ!! ኪዳን ዩንቨርስቲ ገብቶ ነበር። ማንን እንደማገባ ሲያውቅ ለብዙ ሳምንታት አኩርፎኝ ነበር።