Get Mystery Box with random crypto!

​​ሰው የስርዓት ውጤት ነው፡፡ የሚያስበው በስርዓት ነው፡፡ ማንም ዝም ብሎ አያስብም፤ ዝም ብሎ ያ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

​​ሰው የስርዓት ውጤት ነው፡፡ የሚያስበው በስርዓት ነው፡፡ ማንም ዝም ብሎ አያስብም፤ ዝም ብሎ ያስብ ዘንድ የተፈጠረ የለም፡፡ ሰው ለማሰቡ ሰበብ አለው፤ ለሃሳቡ ምክንያት አለው፡፡ ምክንያቱና ስርዓቱ ያመጣው ነው፡፡ ለማሰቡ መነሻ ሃሳብ ያስፈልገዋል፡፡ ከሰማው፣ ካየው፣ ከዳሰሰው፣ ከቀመሰው፣ ካሸተተው፣ ከነፍሱ ጥሪ፣ ከመንፈሱ ግፊት ተነስቶ ነው የሚያስበው፡፡ በል በል የሚለው ስሜት አለ፡፡ ያስብ ዘንድ የሚገፋፋው ውስጣዊ ግፊት አለ፡፡ እንዲያስብ የሚያደርገው ከአዕምሮው ጋር የተዋሃደ የሚንጠው ሃይል አለ፡፡ የሚከውነው በስርዓት ነው፡፡ ስርዓት ከልባችን ጋር ተጋምዷል፡፡ አፈጣጠራችን ራሱ ስርዓት አለው፡፡ መላው አካላችን በስርዓት ነው የሚሰራው፡፡ የልባችን አመታት፣ የኩላሊታችን አሰራር፣ የአዕምሯችን መዋቅር፣ የዲኤንኤያችን ድርድሮሽ፣ መላ አካላችን በስርዓት ነው የታነፀው፡፡ ሰው ከስርዓት ውጪ መሆን አይችልም፡፡ ሰማይና ምድሩ፣ ፀሐይና ጨረቃው፣ ባህርና የብሱ፣ ነፋሳቱና ዝናቡ፣ ወጀቡና ሞገዱ፣ የዓየር ንብረቱ ሁሉ በስርዓት ነው ስራውን የሚሰራው፡፡

ፍቅር ስርዓት አለው፡፡ ጠብም ስርዓት አለው፡፡ ሰው በሚያጋጨው ነው ከሌላ ሰው ጋር የሚጣላው፡፡ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ ካልበደለው ሰው ጋር የሚጣላ ሰው ስርዓት የሌለው ነው፡፡ ሰው ፍቅር ይዞኛል ብሎ በየሜዳው ፍቅሩን አይገልጽም፡፡ ቦታና ጊዜ ይመርጣል፡፡ ሰው ያለቦታውና ያለጊዜው ያለስርዓት ምንም ነገር ሲያደርግ አያምርበትም፡፡ አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ የሚለቀልቀው እኮ አሳሳም ስርዓት ስላለው ነው፡፡ ትዳር ስርዓት አለው፣ አበላል ስርዓት አለው፣ አነጋገር ስርዓት አለው፣ አለባበስ ስርዓት አለው፣ አኗኗር ስርዓት አለው፡፡ ስርዓት የሌለው ምንም ነገር አይገኝም፡፡ አሟሟትም ቢሆን ሰርዓት አለው፡፡ ሰው በየሜዳው እየተገደለ፣ በየጢሻው እየሞተ በቡልዶዘር በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ሬሳው ተሰብስቦ ሲቀበር ማየት ልብን የሚያደማውና ቅስም የሚሰብረው አሟሟትም ስርዓት ስላለው ነው፡፡ አዎ ሰው በህግና ስርዓት ካልተመራ አውሬ ነው የሚሆነው፡፡

ሰው ተፈጥሯዊ ስርዓቱን መለወጥ ባይችልም ዓለማዊውን ስርዓት ያሻሽላል፡፡ ጎጂ የሆነውን በጠቃሚ ስርዓት መተካት አዕምሮ ላለው ሕዝብ ዋና ተግባር ነው፡፡ አድሏዊና ዘረኛ የሆነውን የመንግስትን ስርዓት ሁሉን አካታችና በእኩልነት ወደሚያገለግል ፍትሐዊ ስርዓት መቀየር ከሰለጠነ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ነው፡፡ ያለመልካም ስርዓት መኖር አይቻልም፡፡ ስርዓት ከሌለ ሰላም የለም፤ ብዙ ነገሮች ይመሰቃቀላሉ፣ ጉልበተኞች ይፋንናሉ፣ ባለመሳሪያዎች ሁሉን ለእኔ ይላሉ፡፡

ከተፈጥሯዊው ስርዓት መቃረን ከራስ መጣላት ነው፡፡ ዓለሙ የጫነብሽን ያረጀ አስተሳሰብ አስወግደሽ በአዲስ ሃሳብ ትተኪያለሽ ማለት በዘመናዊነት ስም ከስርዓት ነጻ ትሆኚያለሽ ማለት አይደለም፡፡ ሳይንስ የሚለፋው ስርዓት ለማፍረስ ሳይሆን ጥቃቅን ችግሮቻችንን ለመፍታትና ያልተደረሰባቸውን የሰው ልጅና የተፈጥሮን ስርዓት ለመረዳት ነው፡፡ የተፈጥሮ ስርዓቱን ልጣስ ቢል ግን አይችልም፡፡ ከስርዓቱ አፈነግጣለሁ ብትዪ ከተፈጥሮሽ ነው የምትጋጪው፡፡ አንቺነትሽን በስርዓት ካልመራሽ፣ አኗኗርሽ ስርዓት ከሌለው፣ ሴትነትሽን በስርዓት ካልያዝሺው ገላሽም ይረክሳል፣ ሰውነትሽም ይቆሽሻል፡፡ በኮስሞቲክ ብቻ ሳይሆን በስርዓትም ራስን መጠበቅ ታላቅ ብልህነት ነው!

ዘመናዊነት ሥርዓትን ማሻሻል እንጂ ከሥርዓት ነፃ መሆን አይደለም!

#ሞጋቿነኝ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19