Get Mystery Box with random crypto!

በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

Logo of telegram channel bewketuseyoum19 — በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ
Logo of telegram channel bewketuseyoum19 — በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ
Channel address: @bewketuseyoum19
Categories: Courses & guides
Language: English
Subscribers: 130.44K
Description from channel

➲የበእውቀቱ ስዩም ፈገግታም እውቀትም የሚሰጡ ወጎች ፣ ግጥምች እና የተለያዩ ፀሀፊዎች የስነጽሑፍ ስራዎች የሚቀርብበት ቻናላችንን ይቀላቀሉ፡፡
@bewketuseyoum19
✥--------------------✥
For your comment,feedback and promotion @Bewketuseyoum2bot
Thank you!

Ratings & Reviews

1.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

0

2 stars

1

1 stars

1


The latest Messages 4

2023-07-01 21:00:46 ሂጂልኝ በክረምት

ሂጂልኝ በክረምት
ንፋስ ሲያንገላታኝ ሲያሰቃየኝ ብርዱ
ልቤን ሲያሸብረው መብረቅ ነጎድጓዱ
እንዳታይኝ ከቶ ራቂኝ ግድ የለም
ወትሮም በጨለማ
መንገዳገድ እንጂ መውደቅ ብርቅ አይደለም

ሂጂልኝ በክረምት
ብቻየን ልጋፈጥ ልቻለው ጭጋጉን
ሰማዩ ሲዳምን ልሩጥ ጥጋጥጉን

ይሄ ገራም አይንሽ
ደግሞ ምን በወጣው ይታዘብ ማጣቴን?
ሂጂልኝ በክረምት
ፍርዱን እኔ ልቻል ልቀበል ቅጣቴን

ይሄ ልስልስ ቆዳሽ
ምን በፈረደበት አብሮኝ ቁር ይሸከም
ግድ የለም ራቂ
ናፍቆት አይገለኝም በትዝታሽ ልክረም

ይሄ ሕያው ጥርስሽ
በየትኛው ዕዳ በርዶት ይንቀጫቀጭ
መንዘፍዘፍ ርቆት
ደራርበሽ ይሙቅሽ እኔ ላንቺ ልቀጭ

ሂጂልኝ በክረምት
ሂጂልኝ በክረምት ባይሆን ነይ በበጋ
እንድትከልይኝ
ክፉ አይን ይበዛል ክፉ ቀን ሲነጋ!

ክረምቱን ብቻየን እጋፈጠዋለሁ
ቁሩን ለብቻየ እንዘፈዘፋለሁ

ሂጂልኝ በክረምት ስለ'ኔ አታስቢ
ይልቅስ በበጋው
ከመስከረም ጋራ ነይ አብረሻት ጥቢ

እድሜ ለጨለማ
እድሜ ለዝናቡ ይሸፋፍኑኛል
ብወድቅም ባለቅስም በጉም ያፍኑኛል

ሂጂልኝ በክረምት
ማንም አይወቅሰኝም ብቸኛ ነው ብሎ
ባይሆን በበጋው ነይ
ጉዴ ሲዘረገፍ
እርቃኔን ሲያቆመኝ ቀኔ ወገግ ብሎ

ሂጂልኝ በክረምት
ሂጂልኝ በክረምት ነይልኝ በበጋ
አፍቃሪ ይበርደዋል
ጀምበር ለብቻዋ ሌትን ስታነጋ

    
          በአቤኒ የተጻፈ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
7.1K viewsAbela, 18:00
Open / Comment
2023-07-01 03:20:06 #ቀድመኸኝ ከሞትክ መልካምነትህን እመሰክራለሁ!!!
"መልካም ሰው ነበረ! "
----------------------------
አርባ አመት ለኖረ
ለአንድ ለክፉ ሰው
ጊዜ ሰው አስትቶት
ዘመን ለወቀሰው
ለዛ ለክፉ ሰው
የአንደበቱ ክፋይ
ምኑ ነች ቀና ቃል
ምኑ ነች አንዲት ቃል
መልካም ሰው መሆንን
በስስ ነፍሱ ያውቃል
ለዛ ነው መሰል በቀኑ ፍፃሜ
የአስቀባሪው ሁሉ
የሀዘንተኛው ሁሉ
"መልካም ሰው ነበረ!"
ይላል ሙሾ ቃሉ።።።
#በልጅ ብዕር Nebiyat Mulat

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
8.1K viewsAbela, 00:20
Open / Comment
2023-06-30 13:10:05 (እድሌነች እታለሜ )
ታደሰ ደምሴ

በማለዳ
ገና ሳይረፍድ...
እንዳየኋት
እንዳወቅኋት
ፈገግታዋን "ለጉድ!" ብየ በሰመመን ወድጄላት
"ታዴ!" ብላ ስትጠራኝ መላ አካሌ ደንግጦላት


ውብ አይኖቿን ስርቅ አርጋ ከወደኔ ስትሾፈኝ
ነዳይ ልቤ ሲበጣጠስ፣
እየከዳ ሲያስቸግረኝ

ያዳምን ዘንግ ተመርኩዤ ሴትነቷን ስመረምር
ስብዕናዋን አውቅ ብየ ከቁናየ ስሰፋፍር
ደግሞ አንዳንዴ...
ሰምና ወርቅ ስትሆንብኝ ላመሰጥር ስውተረተር
ዳርቻዋን እያጣሁት ላይሆንልኝ ስቸጋገር
ወንድነቴ ያናቀፈኝ፣
ጣዕምናዋ የጠለፈኝ፣
ገና በፊት ጠዋት ነበር!
ገና በፊት...
ገና ጠዋት!!!

ገና በፊት...
ገና ጠዋት...
በግልብ አቅሜ በስንኩሉ ፣
መልመድ እንጂ መለየትን ከተራራ በሚያከብደው
እግሬም ቢሆን እንደመዝለቅ ፣መመለስን ለማይደፍረው
ስላመዳት ስትሞቀኝ
ስቃለዳት ስጣፍጠኝ

አወቅኋት ስል ስትሰፋ ፣
የእንቁነቷን መዳረሻ በኔ ብርታት ላልወስነው
ያኔ ነበር...
ቀሪ እጣየ ምርጫ ነስቶ እድል ሆኖ የተጻፈው!

እድሌ ነች እታለሜ...
በምድር ላይ ትክ የሌላት ከመለኮት የተቀባች
የኔ ምስራቅ ውብ ተስፋየ፣ መፈጠሬን ያስወደደች!

እድሌነች እታለሜ ቀልቤን በአውዷ ያጠመቀች
እድሌነች እታለሜ ቀልቤን በአውዷ ያቆረበች
ከማንምጋር ደሜ ላይሞቅ ለሷ ብቻ ያመነነች!

እድሌነች እታለሜ...
ከሷ ስሆን የሚያምርብኝ ውድ ጌጤ ሽልማቴ!
አብራኝ ካለች የምደፍር ኩራትና በረከቴ!

እድሌነች እታለሜ...
ውብ ጠረኗ ድግፍ አርጎ ከግም ሽታ የከለለኝ
ተሰውራኝ ሳለቃቅስ ፣
ልጽናናበት ተቀንፎ የተቸረኝ!

እድሌነች እታለሜ...

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
8.9K viewsAbela, 10:10
Open / Comment
2023-06-29 17:35:59 ሰሞንኛ!
(በእውቀቱ ስዩም)

በቀደም የአባቶች ቀን ሲከበር ከሰባት አመት በፊት “ ለአባቴ “ ጽፌ በማለዳ ድባብ ውስጥ የታተመ ውዳሴ ግጥም እዚህ ግድም ሲዘዋወር ዋለ፤ በረከት ገበሬዋ የተባለች የተሳካላት ሴት ግጥሙን አነብንባ ለቀቀችው፤ በረከትን በስኬትዋ የሚቀኑባት፥ ወይም በግላቸው ምክንያት የጠመዷት ሰዎች ከግጥሙ ውስጥ አንዲት ቃል መዝዘው ዘመቱባት ፤ በረከት በምትችለው አስረድታለች፤ አሁን የኔ የባለቤቱ ተራ ነው፤

ላባቴ የጻፍኩት ግጥም ላይ “ሉሲፈር “ እሚል ቃል ተጠቅሚያለሁ፤ ትርጉሙ አሻሚ ለሆን እንደሚችል በመገመት በግርጌ ማስታወሻ ላይ ቃሉን የተጠቀምኩበትን አግባብ ማስቀመጥ አልረሳሁም፤

ሉሲፈር የሚለው ቃል መሰረቱ ሮማይስጥ ወይም ላቲን ነው ፤ የንጋት ኮከብ ወይም ያጥቢያ ኮከብ “ በሚል ይተረጎማል፤ ቬነስ የተባለቸው አንጸባራቂ ፕላኔት በዚህ ስም ስትጠራ ቆይታለች፤ በዚህ ረገድ፥ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ትንቢተ ኢሳያስ የባቢሎን ንጉስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤
“ አንተ የንጋት ልጅ ፤ አጥቢያ ኮከብ ሆይ! እንዴት ከሰማይ ወደቅህ ! አህዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ እንዴት እስከምድር ድረስ ተቆረጥህ “
እያለ ይቀጥላል፤

አማርኛው የንጋት ልጅ ወይም ያጥቢያ ኮከብ እሚለውን የላቲኑ ትርጉም ሉሲፈር ይለዋል፤ የባቢሎኑ ንጉስ በቅጽል ስሙ “ ያጥቢያ ኮኮብ ወይም የንጋት ልጅ “ ተብሎ ይጠራ ነበር ፤ ባገራችንም ነገስታት “ ጸሀዩ ንጉስ “ ተብለው ይሞገሱ ነበር ፤ ለእቴጌ ምንትዋብ በነገሱ ጊዜ “ አሁን ወጣች ጀንበር ፤ ተሸሽጋ ነበር “ ተብሎ ተዘፍኗል ፤ ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልክቱ ኢየሱስን ለመግለጽ ይሄንን ቃል ተጠቅሟል “ ምድርም እስኪጠባ ድረስ ፥ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ ፥ሰው በጨለማ የሚያበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህንን ቃል እየተጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ” (ምእራፍ 1፤ 19)

በሌላ በኩል፥ የካቶሊክ የስነመለኮት እና ባለቅኔዎች በሁዋለኛው ዘመን ኢሳያስ ስለ ባቢሎን ንጉስ የተናገረውን በመተርጎም ሉሲፈር የሰይጣን የቀድሞ ስም ነው የሚል ትረካ አስተዋውቀዋል፤ በርግጥ፥ ማርቲን ሉተርን ጨምሮ ታላላቅ የፕሮቴስታን አባቶች ይህንን ትርጓሜ አልተቀበሉትም፤ እኔ ባህላዊ እውቀቴን ባገኘሁበት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ፥ የክፋት አውራ እንደሆነ እሚታመነው ፍጡር፤ ልዩልዩ ስሞች ይሰጡታል፤ ካልተሳሳትኩ ሄዋንን ያሳታት ሰይጣን” ተመን “ ይባላል፤ መጽሀፈ ሄኖክ የልዩልዩ አጋንንትን ስሞችን ሲዘረዝር ሉሲፈር እሚል አልጠቀሰም፤ ሰይጣን፤ ሳጥናኤል፤ ቢልዘቡል፤ ጸላኤ ሰናይ፥ እሚል አውቃለሁ፤

እኔ ገጣሚ ስለሆንኩ እያንዳንዷን ቃልና ዘይቤ በጥንቃቄ ለመምረጥ እሞክራለሁ፤ “ላባቴ” በተሰኘው ግጥሜ ላይ “ሉሲፈር “እሚለው ቃል “የንጋት ኮከብ “ የሚለውን እንዲገልጽ ተጠቅሜበታለሁ፤ ባንጻሩ ስለ ክፋት (evil) መጻፍ በፈለግሁበት ጊዜ ‘ሰይጣን” እና “ዲያብሎስ “የሚሉ ቃላትን ተገልግየባቸዋለሁ ፤ ለዚህ ማሳያ እዚያው የማለዳ ድባብ ውስጥ “ አባ ይፍቱኝ “ እሚለውን ግጥሜን እጠቅሳለሁ፥

“ አባ ይፍቱኝ
ሰይጣን ብሎ ነገር ፥ የተጭበረበረ
ዋዛ ነው ቧልት ነው ፥ ብየ አስብ ነበረ
ይሄው እውነት ሆኖ ዋዛና ተረቱ
ዲያብሎስን አየሁት፤በሸሚዝ ዘንጦ
እልፍ ግዳይ ጥሎ፥ ቸብቸቦ ጨብጦ”

(የማለዳ ድባብ ፥ ገጽ 75)

ዛሬ ዛሬ፥ ሚድያ ከፍተው ከሞላ ጎደል ለአገሪቱ በጎ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን ስም በማጥፋትና ባልዋሉበት በመወንጀል የሚተዳደሩ ሰዎች አሉ፤ የግል ውድቀታቸውን ፤ ክፋታቸውን በሀየማኖት እና በሀገር ፍቅር ካባ ስለሚሸፍኑት የሚያዳምጣቸውና የሚከተላቸው አላጡም ፤ “ ዲያብሎስን አየነው በሸሚዝ ዘንጦ” እሚለው ሀረግ ደና አድርጎ ይገልጻቸዋል፤ የሚባንንባቸው ትውልድ እስኪመጣ ድረስ በቅደስና ስም ክፋትን እየነገዱ ይቆያሉ::


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
10.0K viewsAbela, 14:35
Open / Comment
2023-06-29 09:40:06 #ኑሮና_ትግሉ
.
.
.
ድካም ከነልጅህ መዛልና ወዳጅህ፣
መጠማት ቁርጥማት፤
ህመም ገላዬ ሁን ሀዘን ሆይ እቀፈኝ፣
ማጣት አዝለኸኝ ዙር መታረዝ ግረፈኝ።
ወንድ ሀሞቴ ፍሰስ፣
ቀና እስክትል ድረስ።
ሲሻህ ገደል ግባ!!  "የለውም" ሁን ወኔ፣
ለማሸንፍ ሲቃን የማልቀበለው ማነኝና እኔ ?

በል ቶሎ በል ድካም፤
በል ቶሎ በል ህመም፤
በማጣት ፍላፃህ ስስ ልቤን ተርትረው፣
በሀዘን ኩታህ ስፌት አካሌን መትረው።
እንዲቆረቁረው፤
እንዲሸነቁረው ነፍሴ እክል ይግጠመው፣
ሽንፈት ያየ ሰው ነው፤
ደክሞት ያመጣውን ድል የሚያጣጥመው።

ብርታት የእናት አባት፤
ሽንፈት ውርስ አይደለም፤
ጀግና መሆን የዘር የሚያገኙት በደም፣
ወይም ወጥተው መቅረት፤
የነፍስ እጣ አይደለም ሲታገሉ መውደም።
እናም እላለሁ........
ሞት ከነወንድሙ ሊወስድ እስትንፋስህ፣
የመቃብር ደጃፍ እስኪያውክ መንፈስህ።
መናኛ በርህን፤
እስኪቆረቁረው ቆሞህ ከመጠብቅ፣
ደጁ ድረስ ሄደህ አንገቱን ነው ማነቅ።
መጋልና መብረድ፤
መውጣትና መውረድ፤
አጥንት ቢያሳሳም መንታም ቢሆን መልኩ፣
ሞት የናቀ 'ለት ነው፤
የወንድ ልጅ መብቃት ጀግና የመሆን ልኩ።

እውነት ነው፤
እርግጥ ነው፤
እንደ ጋቢ ካፖርት ሀዘን የደረበ፣
ጥም መቁረጫ ያጣ አንጀቱ የተራበ።
እንኳንና "መሆን" ለጠፋው "ምናልባት"።
የሴት ልጅ ፈገግታ ምኑም ነው ደምግባት፣
ቀይ እንጆሪ ከንፈር አያይም ዳሌ ባት።

እውነት ነው ሀቅ ነው፤
መኖር ለታከተው ቀን ለሸረከተው።
አለም ለናቀው ሰው ግራ ለተጋባ፣
ናፍቆት እንጦሮጦስ ፍቅር ገደል ይግባ።
ዘላለም ነኝ አትበይ፤
ሁሌም አለሁ አትበይ፤
ቆመሽ አታስቁሚው ሂጂ አንቺም ወዳሻሽ፣
አሁን የጨበጥሽው፤
ማለዳሽን እንጂ አታውቂውም ማምሻሽ።
      " ሰምተሻል አንቺን ነው !!!"
.
.
ሀዘን ሆይ ክፉ ነህ !
ማጣት ክፉ ጠላት፣
ማርያምን አውሬ ነህ ገዳይ ነህ መጠማት።
ከ'ኔ ራቅ መባተል!!!!
መገፋት መግተልተል።
መንዘፍዘፍ ደክሞኛል፣
እስኪያቅተኝ ድረስ እራሴን አሞኛል።
የደከመ አታውቅም ?
የከፋው አታውቅም ?
የአምና ቀኔ በቃህ ዛሬን ልኑርበት፣
አይችሉት የቻለን ጥርሴም ልሳቅበት።
ብዬ ብለምንህ፤
ብዬ ባስለምንህ፤
ክፉ አይደለህ ድካም አይተህ መች ልታልፈኝ፣
ሩቅ ተጓዥ ነኝና፤
መሸሸጊያ አላጣም ይልቅ ና እና እቀፈኝ።
.
.
.
"እኔ ትግል ላይ ነኝ እርሶም መልካም ትግል ይሁንልዎ!!"


    ዓቢይ ( @abiye12 )

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
9.1K viewsAbela, 06:40
Open / Comment
2023-06-28 17:45:48 :      ማን ነሽ??


በምን አፈር ቀምሞ ሰራሽ
                 ነፍስሽን እንደምን ለካው?
ምሳሌ ከየት አገኘ
               ምን ሲያረግ ይሄን አሰበው?

እኔማ ለራሴ ገዢ
             እል ነበር ሁሉን አውቃለሁ
አዋቂ ጥበበኛ ሰው
            ጀግና ነኝ አንቺን እስካየሁ

ወጣሁኝ ሰልፍ ወደአምላኬ
ስሰፍረው ቢያንስ ልኬ
አንተ ጌታ ሸክላ ሰሪ
            የሷን ፈጥረህ ጌጥ ያረከው
ምነው የኔን
ምነው ልቤን ጀበና አርገህ ከእሳት ጣድከው

ሙግት ያዝኩኝ ከጌታየ ከፈጣሪሽ
ከላይ ነኝ ስል ቢያሳንሰኝ ደጉ ሰሪሽ

እንቆቅልሽ ሆነሽ መጣሽ
በምን አቅሜ ችየ ልርታሽ
እንዳልመልስ ጥበብ አነሰኝ
ሀገር አልሰጥ እትብቴ ያዘኝ

በጥያቄ አጥረሽብኝ
      በየት በኩል ልግባ ቅጥርሽ
በጥበቡ ፈትነሽኝ
       እንዴት ብየ ልቁም ስርሽ

አልከትሽ ነገር ውጬ ሆዴ
በምን ችሎ ሊያቅፍሽ ክንዴ

አልደርብሽ እንደሸማ
ወይ አልረሳሽ እንዳልሰማ

እንዳልስምሽ ከንፈርሽ እሳት
እንዳልተውሽ ቀልቤን ነሳት

ማን ነኝ? ብለሽ ጠይቀሽኝ
               ማን ነሽ ብየ ልመልስሽ?
እኔ እንደሆንኩ ጥበብ የለኝ
                ጥበበኛው እሱ ይሁንሽ!

            ማነሽ?


            በአቤኒ የተፃፈ


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
9.0K viewsAbela, 14:45
Open / Comment
2023-06-28 15:25:08 እንኳን ከግንባር ላይ፣
ነፍጥ አንግቶ አይተውት
እንኳን ቃታ ስቦ  ፣
     ብትሩን ቀምሰውት
ድሮም "ፋኖ" ሲባል ፣
     ስሙ አለው ማዕበል
የመንጋን ግሪሳ ፣
   እልፍ ያስበረግጋል

ፋኖ ፋኖ
(ታደሰ ደምሴ)

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
8.3K viewsAbela, 12:25
Open / Comment
2023-06-28 12:30:35 ለወደድናት ሁሉ "አንቺዬ" እያልን ዜማ ሲሸበረቅ
ለናፈቅናት ሁሉ "ናፈቅሽኝ" እያልን ቅኔ ሲነፈረቅ
አመታት ነጎዱ ለሴት ብቻ ሲፃፍ
ልቦና ለነሱን ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ

ያለንን ክህሎት ለ አንቺዬ ሰጠን ብንፈራገጥም
ሴት ብቻ አይደለችም የፅሁፍ ውሃ ጥም
          ምን ነበረ ግጥም???

ዮኒ
     ኣታን @yonatoz

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
8.2K viewsAbela, 09:30
Open / Comment
2023-06-28 09:25:06 #እምቢ_ባይ_ልሳን

የአመታት ስቃዬን አብሮኝ የኖረውን
የሚረዳኝ ጠፍቶ መፍትሄ ያጣውን
ጨክኜ ብነግራት ድብቁ ስሜቴን
በአንዲት ቁንፁል ቃል ናደችው ህይወቴን
እወድሻለሁ ብዬ ቃላት ሳዥጎደጉድ
አልወድህም ብላ አደረገችኝ ጉድ
:
ሂድልኝ ከዚህ ጥፋ ከፊቴ
ላይህ አልሻም አትድረስ ቤቴ
ብላ በዚች ቃል ክምሩ ፍቅሬን
አጠለሸችው ናደችው ክብሬን
የትኛው በደሌ የትኛው ጥፋቴ
ያለ ፍርደ ሸንጎ እንዲህ መቀጣቴ
:
እንዲያውም ልንገርሽ
ፍትህ አልባ ሰው ነሽ
.
በጠጣሩ ቃልሽ መጎዳት ባልሻም
እቀበለዋለሁ እውነቱን አልሸሽም
ምን ይደረጋል አንዴ ፈርደሻል
በኔ ከባድ ህመም መወሰን ቀሎሻል
:
አይባልም እንጂ.......
ስቃዬ ደርሶብሽ በራስሽ ፍረጂ
የሚረዳሽ ጠፍቶ በናፍቆት ንደጂ
ግን ይሁን እንደፈለግሽ...
ባፈቀረ ልቤ መልሼ አልርገምሽ
.
ካልወደድሺኝ አታስቢ
እንድትወጂኝ ብዬ እኔ አልወደድኩሽም
ጠልተሽኛል ብዬ ፍፁም አልረሳሽም
ግን እስከዚያው.....
ደንዳናው ልብሽን ፍቅር እስኪገዛው
እኔም የልቤን ወላፈን አፍኜ ልያዘው
.
ግን ግን እንዳትረሺ...
ትዝ ባልኩሽ ቁጥር ይህንን አስታውሺ
ይህ ደብዛዛ ፍቅሬ አንድ ቀን ከገባሽ
በልቤ ሰገነት ሁልጊዜም ቦታ አለሽ
ዛሬም ትላንትና ነገም ትኖሪያለሽ
{MU_EID}


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19
8.3K viewsAbela, 06:25
Open / Comment
2023-06-28 08:12:06
እንኳን ለ 1444ኛው የ ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ !

@bewketuseyoum19
7.1K viewsAbela, 05:12
Open / Comment