Get Mystery Box with random crypto!

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸው | YeneTube

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ አየር ኃይላችን የታጠቀው መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት "የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው" ሲል የሚያቀርበውን ውንጀላ ከእውነት የራቀ ነው ብለውታል።

በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ደማቅ መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በመመከት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እውቅናና ሽልማት መበርከቱ ይታወሳል።

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አቢይ አህመድ የላቀ አመራርነት ላስመዘገቡ የጦር መኮንኖች የ'አድዋ ጀግና ሜዳይ' የሸለሙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አንዱ ናቸው፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ ከጦር መኮንንነት በተጨማሪ ምርጥ አብራሪ መሆናቸውም በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ይህም አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በብቃት በመመከት ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲያበረክት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ከየትኛውም ወገን የሚቃጣን ጥቃት ለመመከትና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

አየር ኃይሉ ሕዝባዊ መሰረት ያለውና በጠንካራ ስነ ምግባር የተገነባ በመሆኑ የትኛውም አይነት ኦፕሬሽኖች ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

የአየር ኃይሉ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያን በሚመጥንና ኢትዮጵያዊያንን በሚመስል መልኩ የተገነባ እንዳልነበረ፤ በአንድ አካባቢ ሰዎች ታጥሮ ለአንድ ፓርቲ ህልውና ሲሰራ እንደቆየም አንስተዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ለታላቅ አገር የሚመጥንና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሆነ ተቋም መገንባት መቻሉን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

@YeneTube @FikerAssefa