Get Mystery Box with random crypto!

የክልል መለያ ከተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተመራ! የሚኒ | YeneTube

የክልል መለያ ከተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተመራ!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የክልል መለያ በተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ መራ፡፡ምክር ቤቱ የተወያየበት ረቂቅ አዋጅ ከተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመርያና መመዝገቢያ አዋጅ ጋር በአባሪነት ተያይዞ ያለውን ሰንጠረዥ ይሽራል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ የሚሻረው ሰንጠረዥ የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶችን በዝርዝር የደነገገ ሲሆን፣ እንደ ተሸከርካሪዎቹ አገልግሎት የሚኖራቸውን ቀለምና መለያ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰንጠረዡ እንደ አአ፣ ኦሮ፣ አማ፣ ደሕ እና ሌሎች አሥራ ሁለት የክልልና ከተማ አስተዳደሮችን የሚወክሉ ምህፃረ ቃሎችን ዘርዝሮ፣ ተሽከርካሪዎቹ እንደ ተመዘገቡበት ክልል ወይም የከተማ አስተዳደር ሰሌዳቸው እንዲሠፍር ያዛል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሁን ያዘጋጀው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፣ ይኼንን አሠራር በማስቀረት ወጥነት ያለው ብሔራዊ የተሽከርካሪ ሰሌዳ አሠራር ለመዘርጋት አልሟል፡፡በሚኒስቴሩ የሕግ አማካሪ አቶ አበጀ ማሞ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለተወካዮች ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ የክልል መለያ የያዙ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ተግባራዊ የሚሆኑት አዲስ ብሔራዊ ሰሌዳ ይፋ እስኪደረግ ብቻ ነው፡፡

እንደ አማካሪው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የፈረመችው እ.ኤ.አ. የ1968 ‹‹የቬዬና የመንገድ ትራፊክ ኮንቬንሽን››፣ ፈራሚ አገሮች ብሔራዊ ደረጃን የያዘ መለያ በአገሮች ውስጥ ለሚገኙ ተሽከርካሪዎች እንዲሰጡ ያዛል፡፡ ይሁንና የተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመርያና መመዝገቢያ አዋጅ ላይ የተቀመጠው አሠራር ክልሎች የየራሳቸውን መለያ የያዘ ሰሌዳ እንዲሰጡ እንጂ፣ ወጥነት ያለው አገር አቀፍ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ተግባራዊ እንዲደረግ አይፈቅድም፡፡ ‹‹ተሽከርካሪ ዓለም አቀፍ ቁስ ነው፣ አንድ መኪና ከዚህ ተነስቶ ኬንያም ሆነ ሱዳን ሲሄድ የአገሮቹ መንግሥት ግራ ሊጋቡ አይገባም፤›› ያሉት አቶ አበጀ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረገው የሰሌዳ ዓይነት የሚገልጸው ተሽከርካሪነታቸውን ብቻ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

https://www.ethiopianreporter.com/article/24452

Via Reporter
@YeneTube @FikerAssefa