Get Mystery Box with random crypto!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና የሱዳኑ ጄኔራል መሀመድ ዳጋሎ ተወያዩ! የሱዳን ሉኣላዊ የሽግግር ምክር | YeneTube

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና የሱዳኑ ጄኔራል መሀመድ ዳጋሎ ተወያዩ!

የሱዳን ሉኣላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄመቲ) በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸው ተገለፀ፡፡

ሌተናል ጄኔራሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የአገር መከላከያ ሚኒስትሩን አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አግኝተዋል፡፡

የሱዳን የዜና ኤጀንሲ (ሱና) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ሌተናል ጄኔራሉ በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነትና የጋራ ጥቅሞች (ፍላጎቶች) ዙሪያ መወያየታቸውን ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብና ከድንበር ጉዳይ ጋር የተያያዘ ከፍ ያለ የጋራ አጀንዳ እንዳላቸው የሚታወቅ ነው፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤት ምሽቱን በተደረገው ውይይታቸው የሁለቱን አገራት ወንድማማች ሕዝቦች ፍላጎት ለማሳካትና ለማላቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል ተብሏል፡፡

ሌተናል ጄኔራሉ ‹‹አዲስ አበባን በመጎብኘቴ እና የዚህችን ውብ አገር መሪዎች በወንድማማችነት መንፈስ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ጥልቀት እና ጥንካሬ ያረጋግጣል›› ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡

የጦር መኮንኑ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር ‹‹በሱዳን አስጨናቂ ሁኔታዎች ዙሪያ›› ትናንት በአዲስ አበባ መወያየታቸው ኮሚሽነሩ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

Via Walta
@YeneTube @FikerAssefa