Get Mystery Box with random crypto!

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ዓሳ የማርባት ሥራ ተፈቀደ! በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የዓሳ | YeneTube

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ዓሳ የማርባት ሥራ ተፈቀደ!

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የዓሳ ማርባት ሥራ መፈቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የዓሳ ሀብት ልማት ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር ማክሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ምክክር ያደረገ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ያላት ቢሆንም በተገቢው መንገድ ያልተያዘና ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድብን ሳይጨምር በተደረጉ ጥናቶች ኢትዮጵያ በዓመት 94,500 ቶን ዓሳ የማምረት አቅም እንዳላት፣ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አስቻለው ላቀው (ዶ/ር) ገልጸዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት እየተመረተ የሚገኘው በዓመት ከ60 ሺሕ ቶን ያልበለጠ ዓሳ መሆኑን አክለዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 200 ያህል የዓሳ ዝርያዎች መኖራቸውንና 40 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ ዝርያዎች አሁን ባለው ገበያ ተፈላጊ ናቸው ብለዋል። ነገር ግን ዓመታዊ ምርቱ በቂ ባለመሆኑ የአንድ ሰው ዓመታዊ የዓሳ ፍጆታ ግማሽ ኪሎ ግራም በታች መሆኑን ጠቁመው፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአንድ ሰው ዓመታዊ የዓሳ ፍጆታ እስከ 12 ኪሎ ግራም መድረሱን ተናግረዋል። በመሆኑም ያሉትን ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ የውኃ ሀብቶች በመጠቀም የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ አክለዋል።

Via Reporter
@YeneTube @FikerAssefa