🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

​​የውብ ተሰጥኦ ዳር (በእውቀቱ ስዩም) የሳምንቱ ትልቅ ክስተት፥ የታላቂቱ የረቂቅ ሙዚቃ ደራሲ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

​​የውብ ተሰጥኦ ዳር
(በእውቀቱ ስዩም)

የሳምንቱ ትልቅ ክስተት፥ የታላቂቱ የረቂቅ ሙዚቃ ደራሲ እማሆይ ጽጌ ገብሩ እረፍት ነው፤ ታታሪ አድናቂዋ እንደመሆኔ መጠን መሰናበቻ ጥቂት ሀሳብ ባልጽፍ ህሊና ይወቅሰኛል! የፒያኖው ሽቦ ይወጋኛል::

ከእማሆይ ጽጌ በፊት የውብዳር ነበረች፤ አባትየው ከንቲባ ገብሩ እናቲቱ በየነች ኤሌምቱ ይባላሉ::

የውብዳር በሁለት መንገድ እድለኛ ናት፤ ባንድ በኩል እጅግ የላቀ ተሰጥኦ ይዞ መወለድ መታደል ነው፤ ከገዥው መደብ መወለድ ደግሞ ሌላ መታደል፤ የውብዳር ስዊዘርላንድ አዳሪ ትምህርት ቤት የመሄድ እድል ያገኘችው አባትየው ባለማእረግ በመሆናቸው ነው፤ በጊዜው ከመፍጨት ከመውቀጥ ውጭ ሌላ የህይወት አማራጭ የማይቀርብላቸው ብዙ ሴቶች መኖራቸውን እናስብ::

የውብዳር ስዊዘርላንድ በነበረችበት ጊዜ፥ ከዘመናዊ የአውሮፓ ሙዚቃ ፈሊጥ ጋራ ተዋወቀች፤ ባገራችን ለአመት በአል ለልጅ የሚሰጠው ትልቁ ስጦታ ድፎ ዳቦ ነው፤ የውብዳር ግን ለክሪስማስ የፈረንጅ ማሲንቆ( ቫዮሊን ) ተሸለመች፤ እንደሚጠበቀው ባይተዋርነት ይሰማት ነበር፤ በጊዜው የነበራትን ስሜት በማስታወሻዋ እንዲህ ገልጻዋለች፤
“ በጊዜው ከስነፍጥረት ጋር ወዳጅነት ነበረኝ ! አበቦችን እንደ ውብ ልእልቶች ፥ ዛፎች ዘበኞቻቸው፥ ነፋስ ፈጣን መልእክተኛ ፥ ጸሀይ ደግሞ የአለም ንጉስ ሆኖ ይታየኝ ነበር”
የማስታወሻው ፍሬ ሀሳብ የውብዳር የነበረችበትን የብቸኝነት ጥልቅት ያሳያል፤ በሌላ በኩል ረቂቁን ወደ ግዙፍ የመቀየር ተሰጥአዋ ይታያል::

የውብዳር ወጣትነት ህይወት ውስጥ ያለው አንድ ቁልፍ ቃል ቢኖር “ ማምለጥ” የሚባል ቃል ይመስለኛል፤ ባይተዋርነት ይከብዳታል፤ ያም ሆኖ ባገር ቤት መቀመጥ የምትወድ ሴት አልነበረችም፤ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ውስጥ የነበራትን ስራ ለቀቀችና ወደ ካይሮ ሄደች፤ እዚያ እያለች ሮማንቲክ ልቦለዶችን ማንበብ ብቸኝነቷን ለማምለጥ ተጣጣረች፤ ግን በልቦለዶቹ ውስጥ የምታገኛቸው መራር ታሪኮች ፍቅርና ሰውን እን እንድትጠላ አደረጋት፤ ከካይሮ መልስ የእንግሊዝ የትምህርት እድል አገኘች፤ የትምህርት ምኒስትሩ አቶ ሳህሌ ጸዳሉ፤ ከአባትየው ጋራ ተጠማምደደው ስለነበር እድሉን አጨናገፉባት:: በዛሬ አነጋገር “ዲፕሬሽን “ የተባለ ቀውስ ውስጥ ሰተት ብላ ገባች :: “ ዲፕሬሽን “ በዘመኑ አማርኛ “ድብርት” ተብሎ ሲገለጽ አያለሁ፤ ግን ከዚያም የከፋ ነው፤ ችግሩ ከጥንት ጀምሮ ይታወቅ እንደነበር ፍንጭ የሚሰጡን ታሪካዊ መዝገቦች እናገኛለን፤ ለምሳሌ፤ የዋድለው ደብተራ አሰጋኸኝ ስለአጼ ቴዎድሮስ የመጨረሻ ሚስት ፥ እቴጌ ጥሩነሽ ህመምና ሞት ሲጽፍ ‘ሕመማቸው የሀዘን ህማም ነው “ ይላል፤ በርግጥም፥ ዲፕሬሽን እስከሞት የሚያደርስ ህመም ነው፤ የውብዳር እንደ እቴጌ ጥሩነሽን አዋክቦ ከወሰደው ሞት የታደጋት ፥ “ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው ‘ ብላ ታምናለች::

በመጨረሻ ከአዲስ አበባ ወደ ግሼን- ከግሼን ወደ ኢየሩሳሌም ከየውብዳር ወደ እማሆይ ጽጌ መነነች::

ዘጠና ዘጠኝ አመት ለጥቂት ሰዎች ብቻ እሚደርሱበት እድሜ ነው፤ አባትየው ከንቲባ ገብረእግዚአብሄር ደስታም ፥ በአምስት ነገስታት ዘመናት ውስጥ ኖረው፤ በዘጠና አራት አመታቸው ነው የሞቱት፤ ረጅም እድሜና ታላቅ ስራ የቤተሰቡ ነው !

ብዙ ጊዜ የአውሮጳ ታላላቅ ረቂቅ ሙዚቀኞችን ሙዚቃ ለማጣጣም ያደረኩት ጥረት በቅሬታ ተጠናቋል:: የእነ ቬትሆቨኝ ሙዚቃ ጆሮየ ላይ ነጥሮ ተመልሷል፤ እኔ ረቂቅ ሙዚቃ ለማጣጣም አልተፈጠርኩም ከማለት ያዳኑኝ የእማሆይ ጽጌ ዜማዎች ናቸው! በብቸኝነት ውስጥ የተወለዱ ዜማዎቿ ብዙ ጊዜ ከብቸነት ገላግለውኛል!

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19