🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ቀጣዩን የሶማሊያ ምርጫ በሚመለከት በተከፋፈሉት የፖለቲካ መሪዎች መካከል የተደረገው አስቸኳይ ውይይ | DW Amharic

ቀጣዩን የሶማሊያ ምርጫ በሚመለከት በተከፋፈሉት የፖለቲካ መሪዎች መካከል የተደረገው አስቸኳይ ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አስታወቁ። ሚኒስትር ኦስማን አቡካር ዱቤ ዓርብ ማምሻውን ሞቃድሾ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ « መንግሥት በአከራካሪ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር እና እልባት ለመስጠት ሀሳብ ያቀረበ ቢሆንም አንዳንድ ማስተዋል የተሳናቸው ወንድሞቻችን ግን ጉዳዮቹን ለመፍታት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል» ብለዋል።
በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥታት መካከል በምርጫ ሂደት ላይ ለቀናት የተደረገው ድርድር እልባት ሳያገኝ ትናንት መጠናቀቁ ምናልባትም ለፊታችን ሰኞ በተቆረጠው ቀነ ገደብ መሠረት ሶማሊያ ውስጥ አዲስ ፕሬዝደንት መምረጥ አይቻል ይሆናል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ እና የሶማሊያ አምስት የክልል አመራሮች እ.ጎ.አ. መስከረም 17 ቀን በ 2020 መገባደጃ እና በ 2021 መጀመሪያ ላይ መንገድ የሚከፍት የፓርላማ እና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከስምምነት ደርሰው ነበር። ይሁንና ይበልጥ በቅፅል ስማቸው ፋርማጆ በመባል በሚታወቁት ፕሬዚዳንት እና በአንዳንድ የክልል ተቀናቃኞች መካከል አለመግባባቶች እየተባባሱ በመምጣታቸው ይህ ስምምነት ሊፈርስ ችሏል። ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ቦታ የሚፈልጉት ፋርማጆ ዛሬ ሌላ ስብሰባ በፓርላማ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።