🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

የሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ/ም የዓለም ዜና በድምጽ ርዕሶቹ ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በሁለት | DW Amharic

የሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ/ም የዓለም ዜና በድምጽ
ርዕሶቹ
ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በሁለት ተከታታይ ቀናት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ ፤ ሌላ አንድ ሰው አቆሰሉ። በተመሳሳይ የታጣቂዎች ጥቃት በኦሮሚያ ክልል የአደአ በርጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና በደምቢዲሎ ዩኒቨርሲቲ አንድ የጤና ባለሙያ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱባቸው ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም WFP በኢትዮጵያ ያቀርብ የነበረውን የተወሰነ የምግብ እርዳታ ሊያቆም እንደሚችል አስታወቀ። ውሳኔው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ የምግብ እጥረት እንዳያጋልጥ አስግቷል።


በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ የባህር ዳርቻ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ጽንፈኛው አልሸባብ ትናንት አርብ ምሽት ባደረሰው ጥቃት 9 ሰዎች ተገደሉ። ከሞቱት ስድስቱ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ተብሏል ።

ዩክሬን ባለፉት ጥቂት ቀናት በምስራቃዊ ባክህሙት የጦር ግንባር ከሩስያ አንጻር አንድ እርምጃ ወደፊት ያራመደ ድል መቀዳጀታቸውን የወታደራዊ ቃል አቃባዩ ዛሬ ተናገሩ። በባክህሙት አቅራቢያ የኪዬቭ የድል ዜና ሲሰማ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ በፓሪስ የዳይመንድ ሊግ የ300 ሜትር የመሰናክል ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ አሸነፈ።

ዜናውን በዝርዝር

ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በሁለት ተከታታይ ቀናት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ ፤ ሌላ አንድ ሰው አቆሰሉ። ጥቃት አድራሾቹ ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ ከአካባቢው ለቀው መሄዳቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
"በሶስት አቅጣጫ ነው ወደ አጋምሳ መጥተው ተኩስ የከፈቱት፡፡ ሶስት ሰዎች ህይወት አልፈዋል፡፡ አንድ በእርሻ ማሳ ላይ የነበሩ አቶ ዱባለ ተገኘ የተባሉ ነዋሪም ትናንት በእነዚህ ታጣቂዎች ህይወታቸው አልፈዋል፡፡ ሚግር በሚባል ጎጃም መስመርና ሀሮ በሚባሉ ቦታዎችን የሚመጡት፡፡ ከአጋምሳ ተፈናቅለን ከዚህ በፊት የሆሮ ጉዱሩ ዞን ከተማ ሻምቡ ከተማ ላይ ነበርን፡፡ "
ካላፈው ሐሙስ ጀምሮ ከጎጃም ቡሬ ተሻግረው የመጡ የተባሉ ታጣቂዎች አጋምሳ በተሰኘች ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት ካደረሱት ሰብአዊ ጉዳት በተጨማሪ 30 ያህል ከብቶችን ዘርፈው መውሰዳቸውን ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬለ ነግረዋል።
«ወደ 30 ከብቶችን በትናንትው ዕለት ወስደዋል፡፡ አንድ ሰው የአካል ጉዳት አድርሰዋል ሌሎች ደግሞ ሸሽተው ነው ያመለጡት፡፡ ሰው ወጥተው መግባት አልቻለም፣ማረስ አልተቻለም፡፡ በርካታ ሰዎችም ለረሀብም እየተጋለጠ ነው፡፡»
የአሶሳው ወኪላችን ነጋሳ ደሳለኝ የአሙሩ ወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረታ አልተሳካም። በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በተለያየ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ባደረሷቸው ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በተመሳሳይ የታጣቂዎች ጥቃት በኦሮሚያ ክልል የአደአ በርጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና በደምቢዲሎ ዩኒቨርሲቲ አንድ የጤና ባለሙያ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱባቸው ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል። የአደዓ በርጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አብዲሳ ቀነኒ ከትናንት በስትያ ሐሙስ ምሽት በመኖሪያ ቤታቸው በደረሰባቸው ጥቃት መገደላቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሚኒኬሽን በፌስ ቡክ ገጹ አጋርቷል። በተመሳሳይ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የጤና ባለሞያ የነበሩት ገመቹ ጀቤሳ የተባሉ ግለሰብ ትናንት ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ/ም በጉዞ ላይ እያሉ መገደላቸው ተነግሯል። ዩኒቨርሲቲው በፌስ ቡክ ገጹ «ድንገት በደረሰባቸው አደጋ » ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል። ግለሰቡ በአምቡላንስ በመጓዝ ላይ እያሉ ድንገተኛ ጥቃት ሳይሰነዘርባቸው እንዳልቀረ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም WFP በኢትዮጵያ ያቀርብ የነበረውን የተወሰነ የምግብ እርዳታ ሊያቆም እንደሚችል አስታወቀ። ውሳኔው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ የምግብ እጥረት እንዳያጋልጥ አስግቷል።
ድርጅቱ ከውሳኔው የደረሰው የአሜሪካው ዓለማቀፍ የረድኤት ድርጅት ዩ ኤስ ኤ ይድ ለረድኤት የተላከ ምግብ ከታለመለት ዓላማ ውጭ መዋሉን በማረጋገጥ እርዳታ ማቅረብ ማቆሙን ተከትሎ መሆኑን ትናንት ዐርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። የረድኤት ድርጅቶቹ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራዩ ጦርነት ለከፋረሃብ የተጋለጡትን እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል አስከፊ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት እርዳታ ጠባቂ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግ የሰብአዊ ረድኤት ሲያቀርቡ እንደነበር የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ዩኤስኤአይዲ እና የኢትዮጵያ መንግስት “የምግብ ዕርዳታ ዝርፊያን በተመለከተ የወጡትን መረጃዎች በተመለከተ ተከሰቱ የተባሉትን ችግሮች ” ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ባለፈው ሀሙስ አስታውቀው ነበር። የዓለም የምግብ ፕሮግራም በመግለጫው የምናቀርበው ዕርዳታ «ለሚገባቸው የማይደርስ» ከሆነ በፍጥነት ለማቋረጥ እንገደዳለን ብሏል።

በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ የባህር ዳርቻ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ጽንፈኛው አልሸባብ ትናንት አርብ ምሽት ባደረሰው ጥቃት 9 ሰዎች ተገደሉ። ከሞቱት ስድስቱ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ተብሏል ። በጥቃቱ ሌሎች 10 ሰዎች ቆስለዋል። ፖሊስ ከጽንፈኞቹ ጋር ምሽት እስከ ንጋት ከዘለቀ የተኩስ ልውውጥ በኋላ በታጣቂዎቹ ዕገታ ስር የነበሩ ከ80 በላይ ሰዎችን በሕይወት ማስመለጡን ገልጿል። ለጥቃቱ አልሸባብ ወዲያው ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስታውቋል። ፐርል ቢች የተባለው ሆቴል እና በአብዛኛው በመንግስት ባለስልጣናት የሚዘወተረው የባህር ዳርቻው ሆቴል ውስጥ በርካታ ሰዎች ታግተው እንደነበር የአይን ምስክሮች ጠቅሶ አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። አልሸባብ ባለፈው ሁለት ሳምንት ውስጥ በአፍሪቃ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ ጥቃት አድርሶ ብርቱ ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል። በጥቃቱ 54 የዩጋንዳ ወታደሮች ሲገደሉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በሰፈሩበት የጦር ሰፈር ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዲፒኤ ዘግቧል። በጥቃቱ ሁለት የአልሸባብ አጥፍቶ ጠፊዎች በጦር ሠፈሩ ላይ ባደረሱት ጥቃት «በርካታ ቁጥር» ያላቸው ሲቪሎችም ጭምር መገደላቸውን አመልክቷል።

ዩክሬን ባለፉት ጥቂት ቀናት በምስራቃዊ ባክህሙት የጦር ግንባር ከሩስያ አንጻር አንድ እርምጃ ወደፊት ያራመደ ድል መቀዳጀታቸውን የወታደራዊ ቃል አቃባዩ ዛሬ ተናገሩ። በባክህሙት አቅራቢያ የኪዬቭ የድል ዜና ሲሰማ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል። ዩክሬን በመልሶ ማጥቃት 1,400 ሜትሮች የሚረዝሙ የተለያዩ ክፍሎችን ከሩስያውያን እጅ ማስለቀቅ መቻላቸውን የምስራቅ ጦር ቃል አቃባዩ ሴሬይ ቼሬቫቲ ተናግረዋል። ከመልሶ ማጥቃቱ በኋላ ሩስያውያን «ተመሳሳይ ጥቃት ሞክረው አልተሳካላቸውም» በማለት ቃል አቃባዩ አክለዋል ። ነገር ግን የዩካሬን በሜትሮች የሚቆጠር የቦታ ስፋትን ከሩስያውያን እጅ ማስለቀቅ ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አለመቻሉን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል። ሩስያ ለረዥም ጊዜ ከቆየ እና ከብርቱ የደም አፋሳሽ ውግያ በኋላ ባክህሙትን ባለፈው ወር ነበር በቁጥጥሯ ስር ማዋሏን ይፋ ያደረገችው ።