Get Mystery Box with random crypto!

«ከሰዎች ይደበቃሉ፡፡ ከአላህ ግን መደበቅ አይቻላቸውም፡፡» . ኡስታዝ አህመዲን ጀበል . አማኞ | AS-HABULE YEMINE (የቀኝ ጓዶች) ማህደር

«ከሰዎች ይደበቃሉ፡፡ ከአላህ ግን መደበቅ አይቻላቸውም፡፡»
.
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል
.
አማኞች በምንም ምክንያት ለእኩያን ወግነው ሊሟገቱላቸው እንደማይገባ አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን በግልፅ ተናግሯል። ለፖለቲካ አሰላለፍ፥ለብሄር ወገንተኝነት፥ ለጥቅማቸው ወይም ሌላ ምክንያት በዚህ ዓለም ሳሉ ለእኩያን ቢከራከሩላቸውና ጥብቅና ቢቆሙላቸው እነኝህ ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ቅንጣት በማይፈይዱበት በእለተ ትንሳኤስ አላህ ፊት ማን ይሟገትላቸዋል? ሁላችንም በጥሞና ቀጣዩን የቁርአን አንቀጽ እንመልከት።አላህ እንዲህ ይላል፦

“ለነዚያ ነፍቦቻቸውን ለሚያታልሉት (ጥብቅና በመቆም) አትሟገት፡፡ አላህ አጭበርባሪና ኃጢአተኛ (የሆነን ሰው) አይወድምና፡፡ ከሰዎች ይደበቃሉ፡፡ ከአላህ ግን መደበቅ አይቻላቸውም፡፡ በሌሊት እርሱ የማይወደውን ቃል በሚነጋገሩበት ወቅት አብሯቸው ነበር፡፡ አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ያካበበ÷ (ሁሉንም ዓዋቂና ተቆጣጣሪ) ነው፡፡ እነሆ ከዚህች ዓለም ላይ እናንተ ተከራከራችሁላቸው፡፡ በዕለተ ትንሳኤ ከአላህ ዘንድ ማን ይሟገትላቸዋል ማንስ ጠበቃ ይሆናቸዋል?” (ቁርኣን፥4÷107-109)

የዚህ አንቀፅ መልዕክት ለሕዝቡ ሁሉ ቢሆንም አንቀጹ በምክንያትነት ሊወቅስ የወረደው መልዕክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ ነበር፡፡ ታሪኩን ቲርሚዚ÷ ኢብኑ ጀሪር÷ ኢብኑ አቢሃቲም÷ አቡሻይ እና ሓኪም ቀታዳ ኢብኑ ኑዕማንን አጣቅሰው ዘግበዋል፡፡

ታሪኩ እንዲህ ነበር። የበኑ ኡበይረቅ ጐሣ አባላት የሆኑ ቢሽር÷ቢሽር እና ሙበሽር የተሰኙ እኩያን ግለሰቦች ነበሩ፡፡ “ቢሽር” ግን ሙናፊቅ ነበር፡፡ ግጥም በመግጠም ሰሀቦችን ያጥላላ ነበር፡፡ በዚሁም በሰዎች ዘንድ ታወቀ፡፡ የርሱን ግጥሞች የሰሙት ሰሀቦች “ይህንን ግጥም ይህ እኩይ ግለሰብ እንጂ ማንም አይገጥመውም” ይሉ ነበር፡፡ ይህንንም የሰሀቦችን ንግግር ቢሽር ሲሰማ ስንኝ በመቋጠር “አንድ ግጥም በሰሙ ቁጥር ሳያጣሩ ጆሮአቸውን ደፍነው እርሱ ነው” ይላሉን? የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አሰራጨ፡፡

ይህ በእንዲህም እያለ እነኚሁ የበኒ ኡበይሪቅ ሰዎች በሌሊት የቀታዳ ኢብኑ ኑዕማን አጐት የሆነውን የሪፋአን ሠይፍ÷ ጋሻ ፣ ጦር፣ ምግብና ሌሎች ንብረቶችን ቤት ሰብረው ወሰዱ፡፡ ይህን ጊዜም ሪፋአና ቀታዳ ጋር ሆነው ሌባውን ለማፈላለግ ተንቀሳቀሱ፡፡ በኒ ኡበይሪቆች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚያመለክት መረጃ አገኙ፡፡ ሄደውም ጠየቋቸው እነርሱም “እኛ አልሠረቅንም፡፡ የሰረቀውም ሊበድ ኢብኑ ሰህለ ይመስለናል “ሲሉ መለሱ፡፡ ይህ ግለሰብ ግን ምጡቅ ስብእና የነበረውና በዚህ በፍፁም ሊጠረጠር የማይችል ነው፡፡ በርሱ ያላከኩት ጥርጣሬን ከራሳቸው ለማስወገድ ነበር፡፡ በስርቆት የታማው ሊበድ ኢብኑ ሰህል ሰይፉን መዞ ወደ በኒ ኡበይሪቅ ሰዎች ዘንድ ሄደ፡፡ “እኔ ሌባ ነኝን? በአላህ እምላለሁ ይህንን ሰይፍ አንገታችሁ ላይ ሳላሳርፍ የሰረቀውን ግልፅ አድርጉ፡፡” አላቸው። እነርሱም “ከኛ ዞር በልልን! የሰረቅከው አንተ አይደለህም፡፡” አሉት፡፡ እርሱም ተዋቸው፡፡

ንብረቱ የተሰረቀበት ሪፋአ ያሰባሰበው መረጃ ሁሉ ጥርጣሬውን ወደበኑ ኡበይረቅ ሰዎች አነጣጠሩ፡፡ በዚህን ጊዜም ሪፋ እና ቃታዳ ተነጋግረው ጉዳዩን ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ አቀረቡ፡፡ የበኑ ኡባይሪቅ ጐሣ አባላት የሆኑትን ግለሰቦች ከሰሱ፡፡ ንብረቱን የሰረቁት የበኑ ኡበይሪቅ ሰዎችም በተራቸው «ስማችንን በስርቆት አጠፋ» በማለት ሪፋአንና ቀታዳን መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ “ያለምንም ማስረጃና ምስክርም ሰማችንን አጠፉ” ሲሉም ከሰሱ፡፡ ጉዳዩንም መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ተመለከቱ፡፡

እነሪፋእና ቀታዳ የተጨበጠ ማስረጃና ምስክር እንዲያቀርቡ ተጠየቁ፡፡ እነርሱ ያላቸው ማስረጃ ቀጥተኛ ሳይሆን የአከባቢ ማስረጃ ነበር፡፡ መልዕክተኛውም (ሰ.ዐ.ወ) ለበኒ ኡበይሪቆች በመወሰን እነቀታዳን ወቀሱ፡፡ ምስክርና ቀጥተኛ ምስክር ሳይይዙ የግለሰቦችን ስም ማጥፋታቸው በመጥቀስ ተከራከሯቸው፡፡ በድርጊታቸውም ወቀሷቸው፡፡ እነ ቢሽር ጨለማን ተገን አድርገው መስረቃቸው ሳያንስ የተሰረቀባቸውን ሰዎች በስም ማጥፋት ከሰው አስወቀሱ፡፡ እነ ሪፋእና ቀታዳ ግን ንብረታቸውም ተሰርቆም ዳግም ስም በማጥፋትም ተወቀሱ፡፡

ይህን ሁሉ ነገር ይመለከት የነበረው አላህ (ሱወ) የእኩያንና መናፍቃኑን ጥፋተኝነት አረጋገጠ፡፡ መልዕክተኛውም ምስክርና ግልፅ ማስረጃ ባለመኖሩ ለእኩያኑ በመከራከራቸው ተወቀሱ፡፡ እንዲህም አለ፡-

“እኛ ሰዎችን አላህ ባመላከተህ (ፍትህ) ትዳኝ ዘንድ መጽሐፉን በአንተ ላይ በእውነት አወረድን፡፡ (ስለሆነም) ለከዳተኞች ተሟጋች (ጠበቃ) አትሁን፡፡ አላህን ምህረት ጠይቅ፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡ ለነዚያ ነፍሶቻቸውን ለሚያታልሉት (ጥብቅና በመቆም) አትሟገት፡፡ አላህ አጭበርባሪና ሃጢአተኛ (የሆነን ሰው) አይወድምና፡፡ ከሰዎች ይደበቃሉ፡፡ ከአላህ ግን መደበቅ አይቻላቸውም፡፡ በሌሊት እርሱ የማይወደውን ቃል በሚነጋገሩበት ወቅት አብሯቸው ነበር፡፡ አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ያካበበ÷ (ሁሉንም ዐዋቂና ተቆጣጣሪ) ነው፡፡ እነሆ ከዚህች ዓለም ላይ እናንተ ተከራከራችሁላቸው፡፡ በዕለተ ትንሳኤ ከአላህ ዘንድ ማን ይሟገትላቸዋል? ማንስ ጠበቃ ይሆናቸዋል?” (ቁርኣን።4÷105-109)

ይህ የቁርኣን አንቀፅ ለመናፍቃን መሟገትን አስመልክቶ ጠንከር ያለችን መልዕክትን ያዘለ ነው፡፡ አንቀፁ የወረደበት ምክንያት ደግሞ መናፍቃኑን ይታገሉ በነበሩት የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መሆናቸው ጉዳዩን ይበልጥ ጥብቅ ያደርገዋል፡፡ በስርቆቱ ጉዳይ ምስክርና ቀጥተኛ ማስረጃ በሌለበት ነገር ግን ግለሰቦቹ ቀደም ብለው በእኩይነታቸው የታወቁ ነበር፡፡ ቢሽር ደግሞ ሙናፊቅ ከመሆኑም በተጨማሪ የሰሀቦችን ስም ያጠፋ የነበረ ግለሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ምስክርና ቀጥተኛ ማስረጃ ቢጠፋም መልዕክተኛው ለእኩያኑ ወግነው በመከራከራቸው ተወቀሱ፡፡

ከዚህ ታሪክ እኩያን ራሳቸው በደል ፈጽመው ንጹሓንን መልሰው ሊከሱ እንደሚችሉ፥ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ሌሎችን መወንጀልና መፍረድ፥እንዲሁም ለእኩያን ጥብቅና ቆመን መሟገት እንደማይገባን እንረዳለን።

በመጨረሻም በጥላቻ፥ለፖለቲካ ትርፍና ሴራም ሆነ ሌላ በምክንያት መስጂዶቻችንና ንጹሓንን ላይ ጥቃት የፈጸመና የሚፈጽም፥ ራሱ ጥቃት ፈጽሞ በሌላው ያላከከና የሚያላክክ፥ እንዲሁም እውነቱን እያወቀ ለመሸፋፈን የሚተጋም ጭምር ማንም ይሁን ማን አላህ የክፉ ሥራውን ዋጋ ይስጠው።