🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ዝም ብለሽ ጠብቂኝ እርግጥ በዚች ሀገር የተካበው ሁሉ : በፈራረሰባት ህልም ያለችው ሁሉ : ቅዠት | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ዝም ብለሽ ጠብቂኝ

እርግጥ በዚች ሀገር
የተካበው ሁሉ : በፈራረሰባት
ህልም ያለችው ሁሉ : ቅዠት በሆነባት
ሳመኝ ተው ስትለው : ጥርስ በነከሰባት
ፍቅር ስጠኝ ስትል : መርዝ በተላከባት
ያቀፈችው ሁሉ : ዞሮ በነደፋት
አለኝ ያለች ሁሉ : ባዶ በቀረባት
እርግጥ በዚች ሀገር
እርግጥ በዚች ሀገር
ወተት ስንለምናት : ደም ባዘነበችው
ገዳይ እና አራጇን : በሸላለመችው
ወዳጅ አፍቃሪዋን : ወደዳር ባለችው
እንውደድሽ ሲሏት : በማይገባት ፍቅር
ለሷ በሞቱላት : በሚላት ቅር ቅር
የአፍቃሪን ልብ እምነት : በሰባበረችው
ወዶ የቀረባትን : አንገት ባስደፋችው
እርግጥ በዚች ሀገር
መጠበቅ : ሰው መቅጠር
መጠራት : መቀጠር
ሰአት ሞልቶ : መገናኘት
የናፈቀን : ፍቅር ማግኘት
ቢከብድ እንኳን : ቢያስቸግርም
አንቺን ላገኝ
ሰአት ጠቦ : አያጥረኝም
(ብቻ አትቅሪ : አትቆይ እንጂ
በዚች ሀገር
ግድ የለውም : ብታረፍጂ...)

ግን በተራሽ : ከጠየቅሽኝ
እኔን ናፍቀሽ : ከጠበቅሽኝ
መቼ ትመጣለህ? ብለሽ ካልሽኝ

ጠብቂኝ ግራር ስር : ቁሚልኝ ከዋርካው
አልጣሽ ከዛፉ : ልይሽ ከጎዳናው
ላግኝሽ ከካፌ : በድልድዩ እለፊ
ኑሪ ሁሉም ቦታ : ከሀገሩ አትጥፊ
ዝም ብለሽ ጠብቂኝ : ድንገት እመጣለሁ
መቼስ በዚች ሀገር
እንደምን አምኜ : ነገን አቅዳለሁ?
ልክ ነበርሽ አንቺ
ዝም ብየ ምወዳት : ባልገባችኝ ነገር
እናት ሲሏት ባዳ : ባዳ ሲሏት ሀገር
በሆነች ምድር ላይ
የፊቱን ለማቀድ : ሆኖብኛል ፍርጃ
እንኳንስ ነገየን : ዛሬየን እኔእንጃ
ዝም ብለሽ ጠብቂኝ : ዝም ብየ እመጣለሁ
ምናልባትም ትናንት...
ምናልባትም ዛሬ...
ምናልባትም ነገ...
...እንጃ ምን አውቃለሁ

ብቻ ግን ጠብቂኝ...ጠብቂኝ...ጠብቂኝ


እስከመቼ???

በአቤኒ የተፃፈ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19