Get Mystery Box with random crypto!

ሂጂልኝ በክረምት ሂጂልኝ በክረምት ንፋስ ሲያንገላታኝ ሲያሰቃየኝ ብርዱ ልቤን ሲያሸብረው መብረቅ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ሂጂልኝ በክረምት

ሂጂልኝ በክረምት
ንፋስ ሲያንገላታኝ ሲያሰቃየኝ ብርዱ
ልቤን ሲያሸብረው መብረቅ ነጎድጓዱ
እንዳታይኝ ከቶ ራቂኝ ግድ የለም
ወትሮም በጨለማ
መንገዳገድ እንጂ መውደቅ ብርቅ አይደለም

ሂጂልኝ በክረምት
ብቻየን ልጋፈጥ ልቻለው ጭጋጉን
ሰማዩ ሲዳምን ልሩጥ ጥጋጥጉን

ይሄ ገራም አይንሽ
ደግሞ ምን በወጣው ይታዘብ ማጣቴን?
ሂጂልኝ በክረምት
ፍርዱን እኔ ልቻል ልቀበል ቅጣቴን

ይሄ ልስልስ ቆዳሽ
ምን በፈረደበት አብሮኝ ቁር ይሸከም
ግድ የለም ራቂ
ናፍቆት አይገለኝም በትዝታሽ ልክረም

ይሄ ሕያው ጥርስሽ
በየትኛው ዕዳ በርዶት ይንቀጫቀጭ
መንዘፍዘፍ ርቆት
ደራርበሽ ይሙቅሽ እኔ ላንቺ ልቀጭ

ሂጂልኝ በክረምት
ሂጂልኝ በክረምት ባይሆን ነይ በበጋ
እንድትከልይኝ
ክፉ አይን ይበዛል ክፉ ቀን ሲነጋ!

ክረምቱን ብቻየን እጋፈጠዋለሁ
ቁሩን ለብቻየ እንዘፈዘፋለሁ

ሂጂልኝ በክረምት ስለ'ኔ አታስቢ
ይልቅስ በበጋው
ከመስከረም ጋራ ነይ አብረሻት ጥቢ

እድሜ ለጨለማ
እድሜ ለዝናቡ ይሸፋፍኑኛል
ብወድቅም ባለቅስም በጉም ያፍኑኛል

ሂጂልኝ በክረምት
ማንም አይወቅሰኝም ብቸኛ ነው ብሎ
ባይሆን በበጋው ነይ
ጉዴ ሲዘረገፍ
እርቃኔን ሲያቆመኝ ቀኔ ወገግ ብሎ

ሂጂልኝ በክረምት
ሂጂልኝ በክረምት ነይልኝ በበጋ
አፍቃሪ ይበርደዋል
ጀምበር ለብቻዋ ሌትን ስታነጋ

    
          በአቤኒ የተጻፈ

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19