Get Mystery Box with random crypto!

ሱላማጢስ ሆይ... ስወድሽ፣ ምንም አላጣሁም፡ ምንም አልተጎዳሁ፤ እንዲያውም፡ ራሴን አወቅሁት፣ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ሱላማጢስ ሆይ...
ስወድሽ፣
ምንም አላጣሁም፡
ምንም አልተጎዳሁ፤
እንዲያውም፡
ራሴን አወቅሁት፣
ሰው የሚያፈቅር ልብ
እንዳለኝ ተረዳሁ።

ፍቅር፡
ረቂቅ መንፈስ ነው፣
ኃያል ጦረኛ ነው፣
ተዋግተው ተዋግተው የማያሸንፉት፤
ተማረክን ብለው የማይጠየፉት፤
በዕንባ የሚጽፉት፤
የወደቁ ለታ፣
የተረቱ ለታ አሜን ብለው ሚያልፉት።

ፍቅር፡
ረቂቅ ህመም ነው፣
ደስ የሚል ስቃይ ነው የነፍስ ላይ አደስ፤
በዐይን የማይታይ፣
በእጅ የማይዳሰስ፤
አውልያ ማያውቀው፣
ወጌሻ ማያሸው የልብ ላይ ቁስል፤
በዐይን ሰሌዳ፣
በህሊና አድማስ ላይ ወዳጅን የሚስል።
ረቂቅ ጥበብ ነው።

ፍቅር ሕብረ ቃል ነው፡
ሰም ወርቅ ያነገተ፣
ጠቢባን ያልፈቱት የልብ ላይ ቅኔ፤
እንደ ክረምት መንገድ፣
እንዳምሌ እንደ ሰኔ፤
ወንዙ ጎድሏል ብለው፡
ደርሰው ሲሻገሩ ደራሽ ሆኖ ሚወስድ፤
በወሰነው አሰር፣
በመረጠው ፍኖት አንጠልጥሎ ሚነጉድ።

ምንም ሳያዘጋጅ፣
ምንም ሳያሳስብ፣
በመጎንጢስ ኃይል ወደ ራሱ ሚስብ፤
ስቦ ሚያንጠለጥል፣
ከሰፊ ውቅያኖስ አስምጦ የሚጥል፤
አቁስሎ አቁስሎ መልሶ የሚያክም፤
ፍቅር ማግኔት ነው፣
ስበቱ የሚጣፍጥ: ግፊቱ ሚያደክም።

ታዲያ...
እኔ የምወድሽ፡
እንደ ጽርሐ አርያም፣
እንደ ሰማይ ርቀት፤
ደግሞም እንደ ሲኦል፣
እንደ ገሀነም ጥልቀት፤
ወሰን እንደሌለው እንደ ጠፈር ስፋት፤
ስፍር እንደሌለው እንደ አሸዋ ብዛት...
እንዲያ ነው ምወድሽ።

ዘንድሮ፡
 እኔ እኔን አይደለሁም፣
በሀሳብ ማዕበል ሁሌ ነው ምዋኘው፤
እኩለ ሌሊት ላይ፡
ከእንቅልፌ ስባንን፣
ስላንቺ ሲያስብ ነው ራሴን የማገኘው።
ቀንም እንደዚያው ነው።
ብቀመጥ ብነሳ፣
ብራመድ ብላወስ፤
የልቤ ትርታ
እስካልቆመ ድረስ፡
አንቺን ነው ማስበው።

እውነት ከህልም ዓለም እየተምታታብኝ፤
ከትናንት ዛሬ ፍቅርሽ በረታብኝ።

ፍጹም አድርጋ ነው እንደ ሰባት ቁጥር፤
ነፍሴ በመቅረዟ ልትስልሽ የምትጥር።

ጸሐፊ Biruk T.