🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ቁልቁል እንደ ሰርዶ፥ በጀርባዋ ወርዶ፡ የተጠቀለለ፣ ጽልመት የተኳለ፣ ውብ ሀር የመሰለ፣ ቆንጆ ፀጉ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ቁልቁል እንደ ሰርዶ፥
በጀርባዋ ወርዶ፡
የተጠቀለለ፣
ጽልመት የተኳለ፣
ውብ ሀር የመሰለ፣
ቆንጆ ፀጉር ያላት ካየሁ አንዲት ጉብል
አንዲት ውብ ኮረዳ፤
ያንቺ ውብ ገጽ ነው ከዐይኔ ላይ የሚሳል
ከደሜ የሚቀዳ።

በጨዋታ መሀል ጨዋታዋን ገትታ፤
ፍቅርን የምትመግብ በጣፋጭ ፈገግታ፤
እንደ ጣዝማ ጥንቅሽ እንደ ማር ወለላ፣
ፈገግታዋ ሚጥም ሳቋ የሚበላ፤
ቀልዷ ማይሰለች፣
ሳቅ በሳቅ የሆነች፣
እንዲያው በለስ ቀንቶት፡
ከሷ ጋር የቆየ ለቅጽበት ለአንድ አፍታ፤
ሸምቶ ሚመለስ፡
የዘላለም ሀሴት የእድሜ ልኩን ደስታ።

በቃ እንደዚህ ያለች፡
ቅመም የመሰለች፡
የምድሪቱ ህመም ስቃዩ እንዳይከፋን፤
ቀኑን ልታሳምር፡
ጨው ሆና የመጣች የሳቅ የጨዋታ የፈገግታ ዙፋን፤
ካየሁ አንዲት ጉብል
አንዲት ውብ ኮረዳ፤
ያንቺ ውብ ገጽ ነው ከዐይኔ ላይ የሚሳል
ከደሜ የሚቀዳ።

ደግሞ
በሰው እጅ ያይደለ በመለኮት ጣቶች፤
ገጽ ላይ ተቀርጸው ካሉት ድንቅ ውበቶች፤
እንደ ውቅያኖስ ውሀ ኮለለ ያለ ጥራት፣
እንደ ኢትዮጵያዊ ጀነን ያለ ኩራት፣
ተላብሰው የኖሩ፡
እንደ ማለዳ ጎህ
ብርሀን እየተፉ ቀልብ እየሰረቁ፤
በደቂቀ አዳም ላይ እየተሳለቁ፤
ከሰልካካ አንፍ ጎን ተተክለው የኖሩ፤
የአልማዝ ፈርጥ ይመስል አምረው የተፈጠሩ፤
ውበት ያደላቸው፡
ፈጽመው ማይመስሉ አፈር ሚበላቸው፣
በጠራ ሰማይ ላይ እንደተሸመነ የደመና ፈትል፤
የማይጠገቡ የማይሰለቹ የውበት መዘክር፤
የጥጥ ፍልቃቂ የመሰሉ ዐይኖች፡
ያሏት ጉብል ካየሁ አንዲት ውብ ኮረዳ፤
ያንቺ ውብ ገጽ ነው ከዐይኔ ላይ የሚሳል
ከደሜ የሚቀዳ።

ሳቅ በሳቀ ቁጥር ሀሴት የሚተፋ፤
በረድ የመሰለ የወተት አረፋ፤
ድንቅ ውብ ቆንጅየ አስናን፣
እንደ ብርቱካን ሆድ ግመጡኝ ግመጡኝ፣
እንደ መቅደስ ንዋይ ሳሙኝ ሳሙኝ የሚል ውብ ቆንጆ ከናፍር፤
በወርቅ መቅረዝ ላይ የተደረደረ፡ የብርሀን ፊደል የመሰለ ጥፍር፤

እንደ ኪሊዮፓትራ የረዘመ አንገት፣
መድፈኛ ያዘለ ለጠጥ ያለ ደረት፣
አለንጋ የመሰሉ ረዣዥም ጣቶች፣
ሎሚ የመሰሉ፡
በአልቦ የተዋቡ ቆንጆ ተረከዞች...
ያሏት ጉብል ካየሁ አንዲት ውብ ኮረዳ፤
ያንቺ ውብ ገጽ ነው ከዐይኔ ላይ የሚሳል
ከደሜ የሚቀዳ።

ብቻ ምን አለፋሽ፡
ችቦ አይሞላም ወገቧ የተባለላት አይነት፣
የፈጣሪን ድንቅ ጥበብ የሚመሰክር ቅርጽ ያላት፣
የዳቪንቺ ሞናሊዛ የሸክስፔሯ ዡሊየት፣
የኦርማይዋ ፊያሜታ የበአሉ ግርማ ሉሊት፣
የሀዲስ አለማየሁ ሰብለ ወንጌል፣
የስብሐት ለአብ ሲልቪ- ኒኮል፣
የዴርቶጋዳዋ ሲጳራ የዮቶድ ቢሊየነር ፊላ፣
የውበት ደራሲያን ውብ "ካራክተሮች" በሞላ፤
የማይደርሱበት ውበት ያላት ካየሁ አንዲት ጉብል
አንዲት ውብ ኮረዳ፤
ያንቺ ውብ ገጽ ነው ከዐይኔ ላይ የሚሳል
ከደሜ የሚቀዳ።

ለምን ይሆን?


... Biruk T.

ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19