Get Mystery Box with random crypto!

ቱ! ደሞ ከማን ሰማ ናፍቆት በስልጣኑ ሆዴን እንዳባሰው ይሄ ሰፊ ሰማይ በደረቀ ሌሊት እንዲህ የሚ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ቱ!

ደሞ ከማን ሰማ
ናፍቆት በስልጣኑ ሆዴን እንዳባሰው
ይሄ ሰፊ ሰማይ
በደረቀ ሌሊት እንዲህ የሚያለቅሰው

እኔው ሂጂ ብየ
ሸኝቼሽ ነበረ ጠርጌ መንገዱን
አሁን ምን አመጣው
መልሳት እያሉ ከእግዜር መማለዱን

ያኔ
ከዳተኛ ብሎ አምቶሻል ምላሴ
ዛሬ
አንቺን አምጣ ይለኛል የተራበሽ ነፍሴ

ማን በገዘተልኝ
ናፍቆት ይሉት በትር ሲያሳየኝ አበሳ
ሲጎነታትለኝ
አንቺን አምጣ እያለ ልረሳሽ ስነሳ

እግዜሩም አይወደው
ለትንሽ ፍጥረቱ ማነስ ማደግደጌን
እንዲ ስሰባበር
ስንገዳገድልሽ እስክጥል ማዕረጌን

የምችለው መስሎኝ
እንዳላባረርኩሽ ከኑሮ ደጃፌ
አሁን ላይ ሳስበው
ያበሻቀጥኩበት ቆመጠጠኝ አፌ

ምንድን ነበር ያልኩሽ?
እንደበላተኛ ቆጥሬው ልብሽን
ደሞ አቅም እንዳለው
እንደጀግና አድርጎኝ ሰብሬው ቅስምሽን

ምን አልኩሽ እንደውም

(ችጋር ቢያንፏቅቅሽ
ቢያስቧጥጥሽ ምድር ቢያስግጥሽ ሰማይ
ካልጠፋ የ'ህል ዘር ቃል ይበላል ወይ

እስኪ ልጠይቅሽ
ቢያስተዛዝበንም አምቄው በደሌን
ጣፍጦሽ ነው? እርቦሽ ነው? የበላሽው ቃሌን?)

ይሄን ነበር ያልኩሽ አቤት ማስጠላቱ
አሁን ዘገነነኝ የቃሌ ክፋቱ
                                      ቱ!

ምነው ባስላኩብሽ
ስቆ እያባበለ ሲያንገላታኝ ናፍቆት
ልብ መች ይሰክናል
ከጉያው ከጎኑ አፍቃሪው 'ርቆት

ናፍቃኛለች እያልኩ
ላገኘሁት ሁሉ ስናዘዝ የሰሙኝ
ለሴት እንዲ ሆነ
አቅም አጥቶ ተነነ ተረታ እያሉ አሙኝ

እኔ አንገቴን ልስበር
ልሸነፍ ልቻለው ከደጄ ድረሺ
ግዴለም ልታማ
አይንሽን አሳይኝ ናፍቆቴን አስታግሺ

እየጠበቅኩሽ ነው
ከናፍቆትሽ ጋራ ነይልኝ በሞቴ
ያኔ ያልኩሽ የለም
ስትሄጅ የከፈትኩት አልተዘጋም ቤቴ!


         በአቤኒ የተጻፈ


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19