Get Mystery Box with random crypto!

የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ (ሜሪ ፈለቀ) ክፍል 29 | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........


(ሜሪ ፈለቀ)

ክፍል 29

ሰውነቴን ያጋራሁት ወንድ ሊያስገድለኝ ከመሞከሩ በላይ የተሸነፍኩለት ሰው ስልኩን ዘጋግቶ መጥፋቱ ልቤን ሊያበድነው ይገባ ነበር? ክህደት ያውም ለመግደል እስከመሞከር የደረሰ ክህደት ይበልጣል ወይስ መተው? ጭፈራ ቤቱ እስክደርስ በዳዊት ከምናደደው እኩል በጎንጥም እየተናደድኩ ነበር የምነዳው! እንደደረስኩ በሩን በረጋግጄ ስገባ ለወትሮው የሚውልበት ቢሮው ዳዊት የለም። እሱ እስኪመጣ እየጠበቅኩ ቤቱን እየተዘዋወርኩ ማየት ጀመርኩ። ገና ረፋድ ስለሆነ ከሚያፀዱት ሰዎች ውጪ ማንም የለም!! ምንድነው የማደርገው አሁን? መቼም እንደድሮው ስራ ብዬ አልቀጥልበትም! ወይም ቢያንስ የአገልግሎቱን ዝርዝር ማስተካከል ይኖርብኛል!! ከዋናው ጭፈራ ቤት ይልቅ ከሀያ እጥፍ በላይ ገቢ የሚያስገኙት ባለሀብቱ እና ባለስልጣናቱ የሚያዘወትሯቸው በድብቅ የሚከወኑት የሴቶቹ ገላ እና የሚሸጡት አደንዛዥ እፆች ናቸው!! እነዚህ አገልግሎቶች ከተቀነሱ እንደማንኛውም የከተማዋ ጭፈራ ቤቶች ሰካራም የሚራገጥበት ወለል ብቻ ነው የሚቀረው!

እዚህ ቤት ስንቷ ወጣት የሀብታም እና የባለሀብት መዝናኛ ሆናለች!! (ስንቷ ክብሯን ሸጣ ሆዷን ሞልታለች! ወይም እናቷን አሳክማለች።) እዚህ ቤት ስንቱ ወጣት የማይወጣበት ሱስ ውስጥ ተዘፍቋል! (VIP ደንበኛ የሚባሉት ኮኬይን የሚገዙት ናቸው!! ሺሻ እንዲሰራላቸው ያዛሉ ኮኬይን ተደባልቆ ያጨሱታል። ኪሳቸውም ጤናቸውም አብሮ ይጨሳል።) እዚህ ቤት ስንቱ ባለጌ በሚስቱ ላይ ማግጧል (ስንቷ ምስኪን ሚስት እቤቷ ልጆቿን አቅፋ አልቅሳለች) ፣ እዚሁ ቤት ስንቱን ብልግና ማየት ተለማምጄ እንደ ጤንነት ቆጥሬዋለሁ!

ከሙሉሰው ጋር ተጋብተን ትንሽ እንደቆየን ፣ እንግዳ ወይ ጓደኞቹ እቤቱ ሲመጡ እቤቱ ሄጄ እንደሚስት ስብር ቅንጥስ ብሉልኝ ጠጡልኝ ማለት የለመድኩ ጊዜ ፣ እኔ ጠባቂ መሆኔ ቀርቶ በጠባቂ መታጀብ የጀመርኩኝ ጊዜ (አስፈላጊ ሆኖ አልነበረም! ለምን ጠባቂ እንደሚያጅበውም አይገባኝም!! ታይታ ካልሆነ በቀር) ፣ በቴሌቭዥን እንኳን ለማየት ወራት ከምንጠብቃቸው ባለስልጣናት ጋር የተለያዩ ክስተት እና ድግሶች ላይ የባሌን እጅ ቆልፌ መታየት የለመድኩ ጊዜ ፣ አንቱ የምለው ባለስልጣን ሚስት ባሏን ስታማልኝ የለመድኩ ጊዜ ፣ ራሴን ከእነርሱ እንደአንዳቸው ስቆጥር ያልታየ ድግስ ደግሼ እቤት እንዲታደሙልኝ ማድረግ የጀመርኩ ጊዜ፣ ………. ያኔ ጭፈራ ቤቱን በእኔ ስም እንዲያዞርልኝ አስደረግኩት። (እንደ ዓረፍተነገሩ እጥረት ሂደቱ ቀላል አልነበረም!! ትልቁ የገቢ ምንጩ ነው!! ባለስልጣናቱ የሚመጡት እሱን ስለሚያምኑት ነው!! )

ሌላው ጭንቅላቱን የምዘውርበት ጉድፉ ጭፈራ ቤቱ ነው! <ሌላውን ነውርህን ተወውና በወጣት ሴቶች ገላ እንደምትነግድ ፣ እፅ እንደምትነግድ ቢያውቅ እንደቅዱስ መልዓክ የሚያይህ ህዝብ ይቅር የሚልህ ይመስልሃል? > ራስምታት የሚቀሰቅስበት ርዕስ ነው።) ስራውን ለመልመድ ትንሽ ወራት ፈጀብኝ ግን ስለምደው ከእርሱ በተሻለ ያዝኩት ምክንያቱም እኔ ሙሉ ሀይሌን ተጠቅሜ እንጂ እንደእሱ ድብብቆሽ እየተጫወትኩ እና በትርፍ ጊዜዬ አልነበረም የምሰራው። ወደአካውንቴ ከሚያስገባልኝ ጠርቀም ያለ ገንዘብ በተጨማሪ ቁጭ ብዬ ራሴን የምሰማበት ጊዜ ስለማይሰጠኝ ወደድኩት።

እቅዴ በምፈልገው መንገድ እየሄደ ያልሞላልኝ ያን እናቴ ስትሞት መሳሪያ ዘቅዝቆ ይዞባት ተራ ሲጠብቅ የነበረ ደመኛዬን መድፋት ነበር። የሚኖረው አዲስአበባ ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ማዕረግም ሀብትም ያለው ሰው አልነበረም!! ከሙሉሰው ጋር ግን በየእለቱ የሚገናኙ ሰዎች ባይሆኑም ቢያንስ የአንዳቸውን ፌስቡክ ፖስት አንዳቸው ሼር የሚደራረጉ ወዳጃሞች ናቸው!! እቅዴ ግልፅ ነበር ለሁለታችንም!! አንድ ቅዳሜ <ኸረ ተጠፋፋን ለምን ምሳ አንበላም?> ብሎ ሙሉሰው እንዲቀጥረው፣ ከዛ ሲገናኙ እኔ ባለሁበት ምሳ ልንበላ! (የመጨረሻዋን ምሳ) ስንጨርስ መኪናውን እኔ ልሾፍር ፣ ከዛማ ከከተማ አርቄ ወስጃቸው ትክክለኛ ማንነቴን ነግሬው ሬሳውን ለጅብ ጥዬ መምጣት ነበር እቅዴ!! ይሄን ከ10 ጊዜ በላይ ለሙሉሰው ነግሬዋለሁ!!

የዚህን ወቅት ከእኔ የሚያመልጥበት መንገድ መሞከሩን ተስፋ አልቆረጠበትም ነበር። በእቅዱ መሰረት መጥተን ከምሳ ወጥተን ወደመኪናችን ስንሄድ ሙሉሰው ለሰውየው እኔ ያልሰማሁትን ግን ሲመስለኝ እራሱን እንዲከላከል ወይ ልገድለው እንደሆነ አልያም ማን እንደሆንኩ ብቻ አላውቅም የነገረው መልዕክት አደባባይ ላይ ሽጉጥ አስመዝዞታል!! (ሙሉሰው አስቦበት ያደረገው ነገር መሆኑ በሚያቃጥርበት መልኩ ሰውየው መሳሪያ ስላልታጠቀ የሱን ሽጉጥ መውሰድ የሚችልበት አቋቋም ላይ ኮቱን ገልጦለት ነበር የቆመው) ሀሳቡ እሱ ማድረግ ያልቻለውን ሰውየው እኔን እንዲገድልለት ነበር። ተቀደመ እና ሰውየው እዛው ሞተ። በሰውየው ሞት ከማዘን በእኔ አለመሞት ሲበሳጭ ላየው ግራ ያጋባ ነበር። አደባባይ ላይ ስለነበር የሆነው ሁሉ የሆነው ታሰርኩ!! የዚህን ጊዜ ነው እስር ቤት ከእሙጋ የተዋወቅነው። ነገር የማትፋታ ጋዜጠኛ ነበረች። ያልሆነ ነገር እያነፈነፈች አላፈናፍን ስትላቸው ነው እረፍት እንድታደርግ ያስገቧት!! እሷ እስር ቤቱን ለምዳዋለች። ሲፈቷት ደግሞ ሲያስሯት፣ ደግሞ የሆነ ነገር ትቆፍራለች ደግሞ ይከቷታል። ለመጀመሪያ ጊዜ በህይወቴ ሳይከብደኝ ያወራኋት ፣ ሳልደብቅ ያጫወትኳት ፣ ሳትፈርድብኝ የሰማችኝ ፣ ውርደት እና ክፋቴን እንኳን የተረዳችኝ የመጀመሪያ ጓደኛዬ ሆነች። ከሶስት ወር በኋላ ምርጫ ስላልነበረው ሙሉሰው በሚኬደው ሄዶ እራሱ አስፈታኝ። እሙም ከወራት በኋላ ተፈትታ ከእስር ቤት ውጪ ጓደኝነታችን ቀጥሎ ነበር።
ወጥቼ ብዙም ሳይቆይ አንድ ባንክ ውስጥ በራሱ ፣ በእህቱ ፣ በአንድ የሩቅ ዘመዱ …… ደማምሮ የያዘውን 48% አክሲዮን ተቀበልኩት። እኔም በራሴ ፣ በኪዳን እና በእሙ ስም አደረግኩት!! የዚህን ጊዜ <እንደውም መልቀቂያ አስገብቼ ስልጣኔን እለቃለሁ!! ከዛ ምን ይመጣል?> ብሎ ፎክሮ ነበር። እንደባለስልጣን ሳይሆን እንደተራ መናኛ ሰው ራሱ የሚጠብቀው ነገር ቅሌት መሆኑን እየደጋገምኩ ማስታወስ ነበረብኝ። ይፎክራል እንጂ እንደማያደርገው አውቃለሁ። የስልጣን ፍቅሩ ነፍሱን እስከመገበር የሚያደርሰው ነው። ቀስ በቀስ ሀብቱን ስቀበለው። <አይኔ እያየ አትበያትም! ገድዬሽ ከሀገር እጠፋለሁ!> የሚልበት ቀን ብዙ ነበር!!

ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ሲኖረኝ ፣ ከህፃንነቴ ጀምሮ የኖርኩለትን ጠላቶቼን የመግደል ህልም ሳሳካ ፣ ካሰብኩት በላይ ገንዘብ እና አቅም ሲኖረኝ ………. ሁሉም ቀስ በቀስ ጣዕሙን እያጣብኝ መጣ!!! የምኖርበት ህልም አጣሁ!! ለራሴ ስል የምለው ምንም ነገር ጠፋኝ!! ለካንስ በበቀል ስካሬ ውስጥ ወጣትነቴን ሰውቼዋለሁ፣ ሴትነቴን ሰውቼዋለሁ፣ እናት የመሆን እድሌን ቀርጥፌዋለሁ ፣ ሚስት የመሆን መንገዴን ዘግቼዋለሁ ፣ ከሁሉ በላይ ግን ሰው መሆንን ገብሬ ከሰውነት ወርጃለሁ!! ………… ከዛማ በህይወቴ ከኪዳን እና በጥቂቱ ከእሙ ውጪ ምንም ነገር ፈገግ የማያስብለኝ ፣ ልኩን ከስህተቱ ያደበላለቅኩ ፣ ባህልን ከዘመናዊነት ያቀላቀልኩ ፣ ብልግናን ከጨዋነት ያጣረስኩ ፣ ምን ለምን እንደማደርግ የተወናበደብኝ ሆንኩ!! ሲረጥቡ መበስበስ ለምጄ የለ? ተበሳበስኩት!!