Get Mystery Box with random crypto!

ሰሞንኛ (በእውቀቱ ስዩም) በቀደም ቆንጆይቱን የጠለፈውን ሰውየ አሁን አይደል እንዴ የማየው | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ሰሞንኛ

(በእውቀቱ ስዩም)

በቀደም ቆንጆይቱን የጠለፈውን ሰውየ አሁን አይደል እንዴ የማየው፤ ብርሀነመስቀል ረዳ እንኩዋ በፊሻሌ ሽጉጥ የጃንሆይን አውሮፕላን ጠልፎ እንዲህ ተጀንኖ ፎቶ አልተነሳም፤

ለማንኛው ለልጂቱ ድምጽ በመሆን ላደረግሁት አስተዋጽኦ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ጥቁር ውሀ አካባቢ፥ ሚጥጥየ ሰው ሰራሽ ደሴት ቢሸለመኝ አልጠላም፤ የወልቂጤ ህዝብ ደግሞ የክብር ጉራጌነት ቢያጎናጽፈኝ ደስ ይለኛል፤ በነገራችን ላይ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ነጻ ነህ ብሎ ቢለቀው እኔ በገባበት ገብቼ …ዠለስ የጻፍኩት ሁሉ ቀልዴን ነው! ብየ ላረጋጋው የምሞክር ይመስለኛል

በነገራችን ላይ ሰሞኑን ኑሮ የሌለ ከብዶኛል፤ አንዳንዴ ሳስበው ራሴን ከመግደል ያዘገየሁበት ብቸኛ ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር ይመስለኛል፤ በቀደም ሽህ አመት አይኖር ብየ ከባንክ አምስት ሺህ ሶስት መቶ ብር ጎልጉየ አወጣሁ፤ አምስት ሺው ያስቀመጥኩት ሲሆን ሶስት መቶ ብሩ ደግሞ ባንኩ ያስወለደልኝ ነው! የሚገርመው ነገር፥ ብዙ ብር አለኝ ብየ ለጊዜው እንኩዋ ደስ እንዳይለኝ ባንከሩ በድፍን ሁለት መቶ ብር ሸክሽኮ አቀበለኝ ፤ ደሞኮ ወጉ እንዳየቀር፥የተከተለኝ ሰው መኖሩን ለማረጋገጥ እንደ ብሄራዊ ትያትር አንበሳ ገልመጥ እያልሁ እያየሁ አዘገምኩ፤ ከዛ የሆነ ካፌ ገባሁና የመጣው ይምጣ ብየ አናቱ ላይ ግማሽ ቲማቲም ጠብ ያለበት፥ ጨጨብሳ አዝዠ በላሁ፤ አንዱ ደንበኛ ልክፈልልህ ሲለኝ ሀሳቡን ሳይቀይር አስፈምኩት! በቀደም ደሞ የቶሞካ ቡና ባሬስታ ማኪያቶየ ላይ በወተት የልብ ቅርጽ ሊሰልልኝ ሁለት ጊዜ ሞክሮ ሁለቴ ከሸፈበት፤ በመጨረሻ ኩላሊት ምስል ጣል አድርጎ አቀበለኝ! ሲፈልግ ለምን የሸኮና ምስል አይሆንም? ዋናው ፍቅሩ ነው : :

ከካፌው ስወጣ ሶስት ብላቴኖች ከበቡኝ፤

“ የዛሬ አበባዎች የነገ ሌባዎች ! እንደምን ናችሁ ልጆች? “ ብየ ቁልቁል አየሁዋቸው፤

“ ለክለባችን የኳስና የማልያ መግዣ አጥሮን ነበር! ደገፍ አረገን” አለኝ ፊት መሪው ልጅ::
ቁንጮውን እያከከ፤

አምሳ ብር ለቅቅሁባቸውና ጉዞየን ቀጠልኩ፤ ለመጭው ትውልድ የስፖርት እድገት ያበረከትኩትን ሳስብ ፈገግታየ ለግማሽ ሰአት አልበረደም::

አመሻሽ ላይ ጩጨዎቹ፥ እንደገና ከበቡኝ፤

“ ቅድምኮ የኳስ ብላችሁ ቀፍላችሁኛል!” አልኳቸው፤

ፊት መሪው ፈላ ምን አለኝ፥

“ አሁን ደሞ የስቴድየም ማሰርያ እያሰባሰብን ነው”

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19