🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

የመሪ ሚና የመጋቢት 18/2013 ዕለታዊ ቃል 1ሳሙኤል 7÷1-17  ይነበብ እስራኤል በኤሊ ዘመ | Beza International Church

የመሪ ሚና

የመጋቢት 18/2013 ዕለታዊ ቃል
1ሳሙኤል 7÷1-17  ይነበብ

እስራኤል በኤሊ ዘመን በፍልስጤማውያን ተማርኮባቸው የነበረውን የቃል ኪዳን ታቦት አስመልሰው በአንድ ሰፈር ውስጥ በአሚናዳብ ቤት አስቀመጡት፡፡ በዚያም ሠፈርና በመኖሪያ ቤት ለሃያ ዓመት ቆዬ፡፡ ይህ የቃል ኪዳን ታቦት ለሕዝቡ ክብራቸው ሞገሳቸውና ኃይላቸው ነበር፡፡  እስራኤልም ያለ ቃል ኪዳን ታቦት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እንደ ተራ ሰው ሆነው እግዚአብሔርን ይከተሉት ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ወቅት ነበር ሳሙኤል እስራኤልን እንዲመራ ጥሪ ከእግዚአብሔር ዘንድ የደረሰው፡፡

በዘመናት መካከል ሀገርን ለማዳንና ለመታደግ እግዚአብሔር ሲፈልግ መሪዎችን ያስነሳል፡፡ እንዲሁም ከትንሽ ቡድን ጀምሮ ለሀገር ብሎም ለቤተ ክርስቲያን የመውደቅም ሆነ የመነሳት ትልቁን ሚና የሚጫወቱት መሪዎች ናቸው፡፡ መሪዎች በትክክለኛ ዘመን ተነስተው ሲመሩ ሃገር ካለችበት ቀና ትላለች፡፡ ይህ ማለት ሠላምን የሚያደፈርስና የሚያናጋ ይጠፋል ማለት ሳይሆን የእግዚአብሔር አብሮነት ከመሪዎች ጋር ስለሚሆን የዕረፍት ምክንያት ያደርጋቸዋል፡፡ የመሪዎች ትልቁ ፈተና የሚሆነው በአጣብቂኝ ወቅት ላይ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ሳሙኤል የተረከበው ሀገር ታቦቷ የተማረከባትና ከዚህም የተነሳ ሕዝቦቿ በሐዘን የተመቱ ነበር፡፡ ሕዝቡ በእንዲህ ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ዝቅታ ውስጥ ወርደው ሳሉ፣ ሳሙኤል ግን ከዚህ የሚወጡበትን መንገድ ተመለከተ፡፡ ከዚያም የወሰነው ውሳኔ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና እርሱን ብቻ እንዲያመልኩት ከዚያም እግዚአብሔር ከፍልስጤማውያን እጅ ያድናችኋል እኔም ስለ እናንተ እፀልያለሁ አላቸው፡፡ እነርሱም ሳሙኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፀሎትህን አታቋርጥ አሉት፡፡

እግዚአብሔርም በዚያ ቀን በፍልስጤማውያን ላይ ታላቅ ድንጋጤ በመፍጠር ድል እንዲቀዳጁ አደረገ፡፡ ከድሉም በኋላ ሳሙኤል እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል ሲል ያንን ሥፍራ አቤንኤዘር በማለት መታሰቢያን አስቀመጠ፡፡ አቤንኤዘር ማለት የሚረዳ አለት የሚል ትርጓሜ አለው፡፡

ዛሬም በግላችን ካለንበት ሁኔታና እንዲሁም ሀገራችን ከገባችበት ቀውስ መንጭቆ የሚያወጣ እውነተኛ አለት የሆነ መሪ አለን፡፡ ይህም አለት ክርስቶስ ሲሆን እስካሁን ድረስ ረድቶናል ወደፊትም በረጂነቱ ይቀጥላል፡፡/1ቆሮ.10÷4/ ስለዚህ እግዚአብሔር ሀገርንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን ከፍ የሚያደርግበትና የሚጎበኝበት  መንገድ በመሪዎች ስለሆነ ከመሪዎች ጋር እንቁም፡፡

የሕይወት ተዛምዶ
እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ቤተ ክርስቲያን በየደረጃው ካሉ መሪዎች ጋር አብሮ በትብብር መስራትን ተለማመዱ። ምክንያቱም የዕድገት መሠረት ነውና። አሁኑኑ ጀምሩት፡፡

ፀሎት
እግዚአብሔር ሆይ፣ መሪዎች ሁሌም ቀድመው በሁሉ ረገድ እንዲመሩ እርዳቸው፡፡