🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ሰማርያ የሰኔ  10/ 2014 ቃል “በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት።” ዮሐንስ 4፥ 4 በዮሐን | Beza International Church

ሰማርያ

የሰኔ  10/ 2014 ቃል

“በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት።”
ዮሐንስ 4፥ 4

በዮሐንስ 4፡ 9 ላይ እንደምናነበው አይሁድ ከሳምራዊያን ጋር በፍፁም አይተባበሩም ነበር። ታዲያ ጌታ አንድ ቀን ለደቀመዛሙርቱ ሊያስተምር ፈልጎ "በሰማሪያ ማለፍ ግድ ሆነበት።"

ደቀመዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ሲሄዱ ጌታ ደክሞት በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሳምራዊት ሴት በቀትር ውሀ ልትቀዳ መጣች፤ ጌታም ውሀ አጠጭኝ ሲላት ተገርማ ጥያቄ ጠየቀችው። አንተ አይሁዳዊ ሆነህ እንዴት ከእኔ ከሳምራዊቷ ውሀ ትጠይቃለህ? እኔ ሳምራዊት ሴት ነኝ፤ እንዲሁም ይህንን እንዳታደርግ የሚያግድህ ህግ አለ፤አለችው። ኢየሱስም በመገረም ማን እንደሆንኩ ብታውቂ ደግሞም ይህንን ሁሉ ግርግዳ ላፈርስ እንደመጣሁ ብታውቂ እኔን ትለምኝኝ ነበር፤ ዳግም እንዳትጠሚ የህይወትን ውሀም እሰጥሽ ነበር አላት። 

ዳግም ስለብልጫ ስትጠይቀው፤ ብልጫማ ካልሽ ከዚህ የሚጠጣ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው የሚጠጣ ግን ለዘላለም አይጠማም አላት። ከእሷ ጋር ሲነጋገር ደቀመዛሙርቱም አዩት፤ ከሴት ጋር ለዛውም ከሳምራዊት ሴት ጋር በመነጋገሩ ተገረሙ። ጌታ ግን ስለ ባህል፣ ወግ፣ ሀይማኖት እና ፆታ ሳይሆን ስለ አንድ ሰው ህይወት ግድ ይለዋል "በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት" እንደሚል ቃሉ።

ለኛ ሰማርያ የሆነብን በፍፁም በዛ ማለፍ የማንፈልግበት ጌታ ግን ሄዶ ያሳየን ክልል አበጅተን የተቀመጥንበት፣ እርስ በርሳችን የተሟሟቅንበት፣ ያ ክልክል ወደሚመስለን መንደር ጌታ ግን ሂዱ ያለን ለመዳን የኛን ምስክርነት የሚጠባበቁ ብዙዎች ስላሉ ነው። ስለዚህ ከሰራነው ክልል ውጭ በሰማርያ ወዳሉት ብልጫ ወዳለው ከዘላለም ጥማት የሚያሳርፈውን ጌታን ይዘን እንድንሄድ፤ ጥሰን እንድንወጣ ይፈልጋል። እናም በይሁዳ ብቻ ሳይሆን በሰማርያም ምስክሮቹ እንድንሆን ተጠርተናልና እንሂድ እንመስክር ቃሉን በእውነትና በፍቅር እንናገር።

የሕይወት ተዛምዶ
ከባህል፣ ከወግ፣ ከህግና ስርአት አልፈን ጌታ "ግድ ሆነበት" እንደሚል ቃሉ ከጌታ እርቀው ላሉት የሚበልጠውንና የሚያረካውን ጌታ እንድንመሠክር ግድ ይበለን ወደ እነሱ እንሂድ የያዝነውን እውነት በፍቅር እናሰረዳ።

ፀሎት
ጌታሆይ የያዝነው እውነትና የተቀበልነው ፀጋ ይዘን ከክልላችን እንድንወጣ እና ከምንም ነገር የምትበልጥ መሆንህን እንዳንተ የሚያሳርፍና የሚያረካ እንደሌለ እንድንናገር ነውና የተሰጠን ፀጋ እንድንጠቀምበት እርዳን። አሜን!

ማንኛውም የፀሎት ጥያቄ ካላችሁ በ @bezaconnect ይፃፉልን።