🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

እምነት  የነሀሴ 20/ 2014 ቃል እምነት ከመስማት ነው  ሮሜ 10: 17   ማቴ 2: 3 'ን | Beza International Church

እምነት 
የነሀሴ 20/ 2014 ቃል

እምነት ከመስማት ነው 
ሮሜ 10: 17
 

ማቴ 2: 3 "ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላይቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች።" የአይሁድ ንጉሥ መወለዱን አስመልክተው ሰብአ ሰገል ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በተናገሩ ጊዜ ንጉሡ ሄሮድስ ታወከ ይለናል። ይህ የአይሁድ ንጉሥ መወለድ በዋነኝነት ለእስራኤል ልጆች በመቀጠልም ለሰዎች ልጆች ሁሉ መልካም ዜና የነበረ እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። “እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገር ስላዘጋጀ ያለ እኛ ፍፁማን ሊሆኑ አይችሉም። ዕብ 11፡ 40 በማለት ስለ መሲህ መምጣት የተናገሩ የእምነት አባቶችና ነቢያት የጌታ ቃል ሰምተን በጌታ ኢየሱስ ለምናምን ለእኛ የሚበልጥ ነገርን እንዳዘጋጀ በማወቅ ጆሮአችን እምነትን በውስጣችን ሊያሳድግ ለሚችለው ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ ሊሆን ይገባል።

ንጉሡ የተረበሸው እርሱ ብቻውን ሳይሆን የኢየሩሳሌም ከተማም ጭምር ነበር፤ የሄሮድስ ስጋት በይሁዳ የነበረውን ንግስናውን የሚያሳጣው እንደሆነ ቆጥሮ ሲሆን፤ ኢየሩሳሌምም አብራው እንደተረበሸች መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ማር 4፡ 24 “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ።“ ይህም ስለምንሰማው ነገር ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረግን በምንሰማው ነገር እንድንወሰድ ያደርገናል።

"መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው" ሮሜ 10፡ 17 እምነትን ሊፈጥር የሚችል መስማት በእግዚአብሔር ቃል (ሬማ) ነው፤ ሁላችንም እንደምናውቀው ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነው፤ ከዚህም የተነሳ ብዙዎች ያገኙትን ሁሉ በመስማት ለስጋት፣ ለፍርሃትና ለጭንቀት እየተዳረጉ ይታያል። እምነት በውስጣችን እንዲፈጠር መስማት ያለብን ከማህበራዊ ድህረ ገፆች ሳይሆን የጊዜውን ቃል (ሬማ) ከሆነው በእግዚአብሔር ቃል ነው። የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ አይለወጥም!

በዚህ ዘመን የምንኖር ቅዱሳን ሁኔታዎች "ሰላም ነው" ሲሉን የምንረጋጋ፤ "ሰላም አይደለም" ሲለን የምንረበሽ፤ በመረጃዎች ከፍና ዝቅ የምንል ከመሆነን ዘወትር ያልተረጋጋን እንሆናለን።

“የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል“ ምሳሌ 1፡ 33 እንደሚል ሁሉ እግዚአብሔር በቃሉና በመንፈሱ የሚያናግረንን ስንሰማ ከእኛ አልፎ በዙሪያችን ላለው ማህበረሰብ ብሎም ለከተማ መረጋጋት ምክንያት እንድንሆን ያደርገናል። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ቃል በመስማት በእምነት እንደግ።

የሕይወት ተዛምዶ
እምነታችን ከምንሰማበት ምንጭ ጋር የተያያዘ መሆኑን አውቀን ከእግዚአብሔር ቃል በመስማትና የምንሰማውን በመምረጥ በሚገኝ እርጋታ እንኑር።

ፀሎት
እግዚአብሔር ሆይ እምነትን ሊያሳድግ የሚችለውን ቃልህን እሰማሃለው፤ የምሰማውንም እመርጣለሁ። ለቃልህ ጊዜን ለመስጠት እወስናለሁ ለዚህም ፀጋህን አብዛልኝ።

ማንኛውም የፀሎት ጥያቄ ካላችሁ በ @bezaconnect ይፃፉልን።