Get Mystery Box with random crypto!

እምነት  የነሀሴ 25/ 2014 ቃል እምነት በተግባር   'እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደ | Beza International Church

እምነት 
የነሀሴ 25/ 2014 ቃል

እምነት በተግባር
 

"እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈፀም እርግጠኛ የምንሆንበት የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው። አባቶችም የተመሰከረላቸው በዚሁ ነው።” ዕብራውያን 11፡1-2

በ1ኛ ሳሙኤል 14 ላይ የሳኦል ልጅ ዮናታን  ከፍልስጥኤማውያን ጋር ስለገጠሙት ጦርነት ከወጣት ጋሻ ጃግሬው ጋር ሲነጋገር  እናያለን፤ ንግግራቸውም እንዲህ ነው፦

“ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፡ “ና፥ ወደ እነዚህ ሸለፈታሞች ጦር ሰፈር እንሻገር ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም በጥቂትም ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና” አለው።” ወጣቱም ጋሻ ጃግሬው “በልብህ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል እኔም በሙሉ ልብ ከአንተው ጋር ነኝ” አለው። 1ሳሙኤል 14: 6- 7 ታሪኩ  እንዲህ እያለ ሲቀጥል ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው  ባደረጉት ግዳይ አንድ ጥማድ በምታህል የእርሻ  ቦታ ላይ ሃያ  ያህል ሰዎችን ሲገድሉ እናያለን በመቀጠልም የተቀረው የእስራኤል ጦር ሲከተላቸው በመጨረሻም እስራኤላዊያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ እጅግ በመምታት ሲያሳድዷቸው እናያለን። 1ሳሙ 14: 31  ይህ በዮናታን እና ጋሻ ጃግሬው መካከል ያለው  እርስ በርስ መግባባትን ተከትሎ የሆነው  ታሪክ በዕብራዊያን 11 ላይ ለተፃፈው ተግባራዊ ምሳሌ ነው ብዬ አምናለሁ። ዕብራዊያን 11ን በጥልቀት መረዳት እንድንችል በዚህ ታሪክ ውስጥ ከተጠቀሱት ውስጥ ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ እፈልጋለሁ። 
 
1. መተማመን- አንድ ሰው በአንድ ሰው ወይም በአንድ ነገር ላይ እምነት ሊኖረው ወይም ሊተማመንበት የሚያስችል እምነት ነው። ይህ የመተማመን መሰረታዊ ትርጉም ሲሆን ዮናታን ጠላቶቹን ለመጋፈጥ ወደፊት ለመሄድ ሲወስን በጌታ ላይ የነበረውን መተማመን እናያለን። እናም ይህ እምነት በተግባር ምን እንደሚመስል፤  እራሳችንን ባገኘንበት በማንኛውም ሁኔታ  ውስጥ ሆነን በጌታ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመታመን ንቁ ውሳኔ ማድረግ ምን እንደሚመስል ያሳየናል። 

2. ማስተማመኛ/ማረጋገጫ- መተማመንን ለመፍጠር የሚደረግ  አዎንታዊ መግለጫ/ ንግግር ነው። “ምናልባትም ጌታ እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና።” ይህ ንግግር ዮናታን ስላላየው እውነት እንደሚሆን የተናገረው ማስተማመኛ/ ማረጋገጫ ንግግር ነው። 

ተግባራዊ እምነት በተግባር ስለሚገለጥ እምነት ሳስብ የማስበው ነው። እምነት መተማመንንና አስተማማኝ እርግጠኛነትን በጌታና በቃሉ ላይ ማድረግ ነው። እምነታችን ተግባራዊ መሆን ያለበት ጌታን ደስ የሚያሰኝና እንድንሰራው የቀረበለንን ስራ በእምነት በመስራት ነው።

የሕይወት ተዛምዶ
በዚህ ሳምንት እራሳችንን በምናገኘንበት በየትኛውም ነገር ሁሉ ሆነ ብለን እምነታችንን ተግባር ላይ እንድናውለው ሁላችሁንም ላበረታታችሁ እወዳለሁ።

ፀሎት
ጌታ ሆይ እምነቴን በተግባር ማሳየት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስተምረኝ!

ማንኛውም የፀሎት ጥያቄ ካላችሁ በ @bezaconnect ይፃፉልን።