Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች አሰባሰብኩ ባለው መረጃ መሰረት | DW Amharic

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች አሰባሰብኩ ባለው መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 108 የአስገድዶ መድፈር ጥቃት መድረሱን አመልክቷል። ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫው እንዳስታወቀው በትግራይ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመከላከል የመሰረተ ልማት ፣ የማህበራዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ሊመለስ ይገባል ብሏል። በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ከሶስት ወራት ላለፈ ጊዜ ወደነበረበት ያልተመለሰው የማህበራዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የመሰረተ ልማቶች የአካባቢውን ነዋሪዎች እና ተፈናቃዮች ለተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት አጋልጧቸዋል ብሏል። ኮሚሽኑ በአካል ተገኝቶ ክትትል ማድረግ ባልቻለባቸው በርካታ የክልሉ አካባቢዎች «የሰው ሕይወት አልፏል፣የአካል እና የስነልቦና ጉዳት ደርሷል፣ እንዲሁም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና ዘረፋም ተፈጽሟል» ብሏል። ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኙ አራት ሆስፒታሎች ከመቀሌ፣አይደር ፣ አዲግራት እና ውቅሮ ሆስፒታሎች አገኘሁ ባለው መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብሏል። ኮሚሽኑ አያይዞም በመቀሌ እና በሌሎች ተዘዋውሮ በተመለከታቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት መልካም መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል። ነገር ግን የአስቸኳይ እርዳታ ፍላጎቱ ገና እንዳልተሟላ ነው በመግለጫው የተመለከተው። በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት ተቀብረው የነበሩ እና በየሜዳው ተጥለው የነበሩ ፈንጂዎች በተለይ በሕጻናት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ኮሚሽኑ አያይዞ ገልጿል።‹‹እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጾታዊ ጥቃትና በሕጻናት ላይ የደረሰው ጥቃትና ጉዳቱ ከዚህ የበለጠ እንዳይስፋፋ ልዩ ትኩረትና ጥረት ይሻል›› ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል።