Get Mystery Box with random crypto!

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጊኒ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኤቦላ በሽታ መከሰቱ በይፋ ከተረ | DW Amharic

በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጊኒ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኤቦላ በሽታ መከሰቱ በይፋ ከተረጋገጠ በኋላ ሀገራቱ ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሚገኙ አስታወቁ። የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴሮች ይፋ እንዳደረጉት ጊኒ ውስጥ ሰባት ሰዎች ላይ ተህዋሲው መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን የሶስቱ ሰዎች ህይወት ሊያልፍ ችሏል። በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ዛሬ አራተኛ ሰው ላይ ተህዋሲው ሊረጋገጥ ችሏል። ይህንን ተከትሎም ሁለቱ ሀገራት የበሽታውን ደረጃ ዝቅተኛ በሚባለው የወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዛሬ አስታውቀዋል። ተላላፊ በሽታው የተከሰተው በሰሜናዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪቩ አውራጃ ሲሆን በጊኒ ደግሞ የላይቤሪያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ጎውኬ ከተማ ነው። በዚች ከተማ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደ አንድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተሳተፉ ሰዎች « የማስመለስ፤ የተቅማጥ፣ ትኩሳት እና የመድማት የመሳሰሉ ምልዕክቶችን ማሳየት እንደጀመሩ ተገልጿል። በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ናሙና የተወሰደው ግን ዓርብ ዕለት መሆኑን የፈረንሳይ ዜና ምንጭ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። ጎረቤት ሀገር ላይቤሪያ ይፋ ከሆነው ዜና በኋላ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንደሆነች የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል። የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ፈጣን ርዳታ ለመለገስ ማቀዱን ገልጿል።
ጊኒ ውስጥ ከጎርጎሮሲያኑ 2013 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ተከስቶ በነበረው የኤቦላ በሽታ 2500 ገደማ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በጠቅላላ በአካባቢው ባሉ ሀገራት ደግሞ ከ 11, 300 በላይ ሰዎች ሞተዋል። የኤቦላ ተህዋሲ ለመጀመሪያ ጊዜ እጎአ በ 1976 ዓም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የተረጋገጠ ሲሆን መጠሪያ ስሙንም ያገኘው በሀገሪቱ በሚገኝ አንድ የወንዝ ስም ነው።