Get Mystery Box with random crypto!

አፍረን ቀሎ እና የአቡበከር ሙሳ ገድል ------ ግን ዓሊ ቢራን ኮትኩቶ ያሳደገው የጥበብ መምህሩ | ancient history of oromoo and oromia

አፍረን ቀሎ እና የአቡበከር ሙሳ ገድል
------
ግን ዓሊ ቢራን ኮትኩቶ ያሳደገው የጥበብ መምህሩ ልክ የዛሬ አርባ ዓመት ሞቶ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ የዚያን የጥበብ ገበሬ ስራዎች እንቃኛለን፡፡
------
ዓሊ ቢራ በአማርኛ አንድ ዘፈን ብቻ ነው የተጫወተው፡፡ ከዘፈኑ ስንኞች መካከል እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡
ከድሬ ስመጣ ገና ትንሽ ነበርኩ
አሁን ከኢትዮ ስታር ባንድ እዩኝ ግንድግድ ነኝ፡፡
ዓሊ እንዲህ ያለው በ1970ዎቹ አጋማሽ ነው፡፡ ታዲያ ከድሬ የመጣው የያኔው ትንሽ ልጅ ዛሬ በብዙዎች ዘንድ የሚወደስ “ግድንግድ” ሆኗል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎችንም አፍርቷል፡፡ ይህ ተወዳጅ አርቲስት ከእውቅና ማማ ላይ ሊወጣ የቻለበት አስደናቂ ታሪክ አለው፡፡ ታሪኩንም ከስረ መሰረቱ ጀምረን እንመረምረዋለን፡፡
*****
በኦሮሞ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የተደራጀ የሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ” በመባል ይጠራል፡፡ የኦሮሞ ሙዚቃ የራሱን ዘውግ ፈጥሮ መስፋፋት የጀመረው ይህ ቡድን ህልውናውን ካበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ቡድኑ ለስምንት ዓመታት ብቻ የቆየ ቢሆንም በኦሮሞ ኪነ-ጥበብ ላይ ያሳረፈው ተጽእኖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚያ ቡድን ውስጥ የተሰባሰቡት ወጣቶች የተገኙት ከመላው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ ሁሉንም አንድ ላይ አገናኝታ ስለ ጥበብ እንዲፈላሰፉ ያደረገችው ግን ድሬ ዳዋ ናት፡፡
“አፍረን ቀሎ”ን የመሰረቱት ሶስት ወጣቶች ናቸው፡፡ ዘመኑም 1954 ነው፡፡ እነዚያ ወጣቶች በጊዜው በኦሮምኛ ቋንቋ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን የሚያቀርብ ቡድን አለመኖሩ ስላንገበገባቸው “ለምን በቋንቋችን የሙዚቃና ቴአትር እድገት ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀስ ቡድን አናቋቁምም?” በማለት መነጋገር ጀመሩ፡፡ ሃሳቡን ለጥቂት ሳምንታት ካንሸራሸሩ በኋላም ቡድኑን መሰረቱ፡፡ ስያሜውንም በአራቱ የምስራቅ ሀረርጌ የኦሮሞ ጎሳዎች ስም “አፍረን ቀሎ” በማለት ጠሩት፡፡
ሶስቱ ወጣቶች በመሰረቱት ቡድን ዙሪያ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች መለመሉ፡፡ በተበታተነ ሁኔታ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን የሚሞካክሩ ወጣቶችንም መሳብ ጀመሩ፡፡ በሀርሞኒካና በጊታር እየዘፋፈኑ ሰርግና የጫጉላ ሽርሽር ሲያደምቁ የነበሩትንም አሰባሰቡ፡፡ በዚህም መሰረት ዓሊ ሸቦ፣ ማሕሙድ ቦኼ፣ ሸንተም ሹቢሳ እና ሃሚዶ መሐመድ የመሳሰሉትን የዘመኑን ውብ ዜመኞች በአንድነት አጣምረው “አጃዒበኛ” ስራዎችን ወደ ህዝብ ማድረስ ጀመሩ፡፡ ህዝቡም በከፍተኛ ወኔና ሞራል ተቀበላቸው፡፡ በተለይ በአረፋና በዒድ አል ፈጥር በዓል የሚያቀርቡት የድራማና የሙዚቃ ትርዒት ከፍተኛ ዝናና ከበሬታ አስገኘላቸው፡፡ የድሬዳዋ ባለሀብቶችም በልዩ ልዩ መልክ ይደጉሟቸው ጀመር፡፡ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ከመግዛት ጀምሮ በሀረርጌ ከተሞች ውስጥ እየተዘዋወሩ ትርዒታቸውን የሚያሳዩበትን ሁኔታ እስከማመቻቸት የሚደርስ ድጋፍ አደረጉላቸው፡፡
“የአፍረን ቀሎ” ቡድን የተመሰረተው በሶስት ወጣቶች እንደሆነ ከላይ ገልጬአለሁ፡፡ ነገር ግን ከሶስቱ ወጣቶች መካከል የአንደኛው ሚና እጅግ በጣም ግዙፍ ነበር፡፡ ይህ ሰው የቡድኑ ሊቀመንበር ሆኖ ይሰራል፡፡ የቡድኑ አስተዋዋቂም ነው፡፡ የቡድኑ አባላት የሚያዜሟቸው ግጥሞችንም በብዛት የሚጽፈው እርሱ ነው፡፡ ድራማና አጫጭር ጭውውቶችንም ይደርሳል፡፡
የአፍረን ቀሎ ቡድን በህዝቡ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት እየጨመረ ሲመጣ ይህ የቡድኑ ሊቀመንበር የነበረው ሰውዬ ከአንጋፋዎቹ ከያኒያን በተጨማሪ ታዳጊዎችንም እየመለመለ ወደ ቡድኑ መቀላቀል ጀመረ፡፡ በዚህም መሰረት ሂሜ ዩሱፍ እና ኢብራሂም ሀጂ ዓሊን የመሳሰሉ ዐጃኢበኛ ከያኒዎች የቡድኑ አባላት ሆኑ፡፡
ቡድኑን በኋላ ላይ ከተቀላቀሉት ታዳጊዎች መካከል በድምጹ ቅላጼ ለየት ያለ ሆኖ የተገኘው ዓሊ መሐመድ ሙሳ የሚባል ጠይም ኮበሌ ነው፡፡ በመሆኑም የቡድኑ ሊቀመንበር የነበረው ሰው “ፉአዲ ቀልቢ” የሚባል የዘመኑን ተወዳጅ የግብጻዊያን የዐረብኛ ዜማ “ቢራዻ በሪኤ” (በአማርኛ “መስከረም ጠባ”፣ “ጸደይ ሆነ” እንደማለት ነው) በሚል ርዕስ ወደ ኦሮምኛ ቀይሮት ጻፈውና ለታዳጊው ዓሊ ሙሐመድ ሙሳ ሰጠው፡፡ ታዳጊውም ከህዝብ ፊት በመውጣት እንዲህ ዘፈነው፡፡
Birraadhaa bari’ee ililliin urgoytee
Dilii maalin qaba Rabbii khiyya yaa Goytee?
ይህ የዘፈኑ አዝማች ነበር እንግዲህ፡፡ ታዳጊው ይህንን ሲዘፍን ዕድሜው ከአስራ አምስት ዓመት የበለጠ አልነበረም፡፡ የዘፈኑ አዝማች በአማርኛ ሲተረጎም እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡
መስከረም ጠብቷል የአበቦች መዓዛ ያውዳል
“ምን ጥፋት አለብኝ አምላኬ ሆይ! ለኔ ምን ይበጃል?
ህዝቡ ዘፈኑን ሲሰማ በከፍተኛ ጭብጨባ ነው የተቀበለው፡፡ “ቢስ…ቢስ…” እያለ ደጋግሞ እንዲዘፍን አደረገው፡፡ በሌሎች መድረኮችም ተመሳሳይ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ በሰርግ ቤትም ሆነ በበዓላት ዝግጅት “ቢራዻ በሪኤ” እጅግ ተመራጭ ዜማ ሆነ፡፡ ህዝቡ እርሱ ያልተዘፈነበትን ዝግጅት ለመታደም እምቢ ማለት ጀመረ፡፡ “ቢራዻ በሪኤ” እያለ የሚደንሰው ወጣት የሌለበትንም ዝግጅት ከማየት አፈገፈገ፡፡ ምን ይሄ ብቻ? የድሬ ዳዋ ህዝብ በስልጣኑ የታዳጊውንም ስም “ከዓሊ መሐመድ ሙሳ” ወደ “ዓሊ ቢራ” ቀየረው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ “ዓሊ ቢራ” የታዳጊው መጠሪያ ሆነ፡፡
*****
“ዓሊ ቢራ” የሚለው ስም የተከሰተው ከላይ በተገለጸው ሁናቴ ነው፡፡ ለዚያ ቀጫጫ ልጅ መታወቅ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያደረገው የመጀመሪያ ዘፈኑን ጽፎ የሰጠው ደራሲ ነው፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታትም ይኸው ደራሲ እጅግ ውብ የሆኑ ግጥሞችን እየጻፈ በዓሊ ቢራ በኩል ለህዝብ ጆሮ አድርሷል፡፡ ዝንተ-ዓለም የማይረሱ ሆነው ከኛ ጋር ያሉትን እንደ “ኮቱ ያ ቢፍቱ ቲያ”፣ “ጉያን ጉያዻ ኢኒኑ”፣ “ኮጳ ኮ ነዺፍቴ”፣ “ነጃለቴ ገመ ኬቲን”፣ “ነቲ ሂንጀባቲን ገራ”፣ “ሲንበርባዳ”፣ “ሲጃሌ ጃለላ ዴይማ”፣ “ወል አርጉ ዋ ሂንኦሉ”፣ “ያደ ኬቲን ሾረርካዌ”፣ “ያ ሂሬ ሂሪያ”፣ “ሂንያዲን ሂንያዲኒ”፣ “አማሌሌ” የመሳሰሉ ምርጥ ዜማዎችን የጻፈው እርሱ ነው፡፡
ያ ከዓሊ ቢራ ጀርባ የነበረው ታላቅ የጥበብ ሰው “አቡበከር ሙሳ” ይባላል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በኦሮሞ ህዝብ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ታላቅ ስፍራ የሚሰጠው ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ ጸሓፌ-ተውኔትና የታሪክ ምሁር ነው፡፡ አቡበከር ሙሳ በ1935 በሀረርጌ ክፍለ ሀገር በኦቦራ (ወበራ) አውራጃ ከደደር ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው “ሌሌ ገባ” በተሰኘች ትንሽዬ የገጠር መንደር ነው የተወለደው፡፡ በልጅነቱ እስላማዊውንና የዐረብኛ ቋንቋ ትምህርቶችን አጥንቷል፡፡ ከዚያም ለተሻለ ትምህርትና ለስራ ፍለጋ ሲል የገጠሩን ህይወት ትቶ ወደ ድሬ ዳዋ ከተማ ተሰደደ፡፡ እጅግ በጣም ፈጣን አዕምሮ የነበረው ታዳጊ በመሆኑ በድሬዳዋ ከተማ በሚገኝ አንድ መድረሳ በዐረብኛ ቋንቋ አስተማሪነት ተቀጠረ፡፡
እንግዲህ አቡበከር ሙሳ የመድረሳውን ስራ እየሰራ ነው ከሁለት ጓደኞቹ ጋር የ“አፍረን ቀሎ”ን ቡድን የመሰረተው፡፡ ይህ ሰው ለስምንት ዓመታት ቡድኑን በሊቀመንበርነት በመምራት በኦሮምኛ ኪነ-ጥበብ እድገት ላይ ከፍተኛ አሻራ ጥለው ያለፉ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
(ይቀጥላል)
----
ማስታወሻ፡ ይህ ታሪክ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ዳዋ” ከተሰኘው የኔ መጽሐፍ የተቀዳ ነው