🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ዛሬ ነገ ነው? 'አባዬ ዛሬ ነገ ነው?' አለ አቡሽ አባቱን ከተኛበት እየቀሰቀሰ። አባት እየተበሳጨ | ህብረ ቀለማት ግጥሞች

ዛሬ ነገ ነው?
"አባዬ ዛሬ ነገ ነው?" አለ አቡሽ አባቱን ከተኛበት እየቀሰቀሰ። አባት እየተበሳጨ "ምንድን ነው የምትለኝ?" አለ። ልጅም "ዛሬ ነገ ነው ወይ?" አባት እንቅልፉ ስላለቀቀው "ሂድና እናትህን ጠየቃት በቃ ልተኛበት" አለና እየተበሳጨ ፊቱን ቨፈነ።

ልጅ ወደ እናቱ ሄዶ ያንኑ ጥያቄ ደገመላት " እማዬ ዛሬ ነገ ነው?" እናት ፈገግ አለች "ምን ማለት ነው ደግሞ ዛሬ ነገ ነው? ማለት?" አለች የልጇን የተጋለጠ ደረት እየሸፈነች "ትናንት አስተማሪያችን 'ነገ ትምህርት የለም' ብላን ነበር፣ ዛሬ ነገ ነው?" አላት። እናት "እ እ አዎ ልክ ነህ ዛሬ ነገ ነው" አለች እየሳቀች።

ይህ ለሕፃኑ የተሰጠ መልስ ለእኛም ሳያስፈልገን አይቀርም። ብዙዎቻችን የምንኖረው ለነገ ነው። ለነገ እንማራለን፣ ለነገ እንሰራለን፣ ለነገ እንገነባለን። የተፈጠርነው ለዘላለማዊነት ነውና እንደምንኖር አስበን ማቀዳችን ባልከፋ። ነገር ግን ላላየነው ነገ ስናስብ ያየናትን ዛሬ እንዘነጋታለን። ለነገ ደመና የዛሬን ፀሐይ እንገፋታለን። እንዳቀድን እንዳለምን ለመኖር ስንዘጋጅ እንሞታለን። መጽሐፍ" ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ ተመልከቱ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና" "ነገ ለራሱ ያስባልና ለነገ አትጨነቁ!" ይላል። ያዕ 4:15 / ማቴ 6:34

ሰይጣን ከሚጠቀምበት ሰውን ማጥቂያ መሳሪያም አንዱ "ነገ" በሚል ቃል ማዘናጋት ነው። ነገ እማራለሁ፣ ነገ እሔዳለሁ፣ ነገ የታመመ እጠይቃለሁ፣ ነገ ንስሐ እገባለሁ፣ ነገ ወደ እግዚአብሔር እመለሳለሁ፣ ነገ ይሄንን መልካም ነገር እሰራለሁ ነገ ነገ ነገ። ፈርኦን የሚባለው ጨካኝ ንጉስ በመቅሰፍት ጓጉንቸር ተወርሮ ነበር። በመጨረሻም እስራኤልን እለቃለሁ ሲል ሙሴ:- ጓጉንቸሮቹ ከቤትህ እንዲጠፉ መቼ ልጸልይልህ? አለው። ፈርኦንም :- ነገ አለ።

እንግዲህ ዛሬን ከጓጉንቸሮች ጋር ማደር ፈልጓል ማለት ነው። ወዳጄ በሕይወትህ ውስጥ ጓጉንቸሮች ምንድን ናቸው? ምን አይነት ክፉ አመል አለብህ፣ ምን ዕረፍት ያሳጣህ፣ ሰላም የነሳህ ነገር አለ? አልላቀቅ ያለህ ሱስ፣ አልተስተካከል ያለህ ድክመት፣ አልድን ያለህ ቁስል ምንድን ነው? እርሱን መቼ ትላቀቀዋለህ? መቼ መዳን ትሻለህ? ነገ ካልከኝ ፈርኦን መሆንህ ነው? "አቤቱ አሁን አድን" ካልክ ደግሞ እንደ ዳዊት ትሰማለህ።

ነገ ይህንን ሱስ እተዋለሁ፣ ነገ ይህን ልማድ እላቀቃለሁ፣ ነገ ይህን መልካም ነገር አደርጋለሁ የሚል ቀጠሮ ሠርቶ አያውቅም። ነገ እንላለን እንጂ የሚገርመው በማግስቱም መልሳችን ነገ ነው። "ዱቤ ዛሬ የለም ነገ ነው" እንደሚለው የብልጥ ባለሱቅ ማስታወቂያ ነገ ስንሔድ ነገ እየተባለ የምንፈልገውን ሳንሰራ የማንፈልገውን እየሰራን እንኖራለን። ወዳጄ ነገ የአንተ አይደለችም "የተወደደ ሰዓት አሁን ነው" መኖርህን ሳታውቅ ቀጠሮ አትስጥ። ኃይልህ በአሁን ላይ ብቻ ነው። ማንም ሊሰራባት የማይችላት ሌሊት ሳትመጣ አሁንን ተጠቀምባት።

አሁኑኑ ተነስ ያሰብከውን መልካም ነገር ለመስራት፣ ክፉውን ነገር ለመተው ነገ አደርገዋለሁ አትበል ትናንት ኅሊናህ ሲጠይቅ "ነገ አደርገዋለሁ" ብለህ ነበር፣ ዛሬም "ነገ" አትበል ምክንያቱም ሕፃኑ እንዳለው "ዛሬ ነገ ነው!"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም
ቪክቶሪያ አውስትራሊ