🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ዕለተ ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የብራና ቤተሰብ የመጽሐፍ ውይይት በጁፒተር ኢንተርናሽና | ስለ መፅሀፍት በጥቂቱ

ዕለተ ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን 2013 ዓ.ም
የብራና ቤተሰብ የመጽሐፍ ውይይት
በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ ቦሌ ቅርንጫፍ
የመጽሐፉ ርዕስ፡ እላፊ፤በዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ
የገፅ ብዛት 524 (6 ምዕራፎችና ነፃ ገፆች)
አጋፋሪ፡ መኰንን መንገሻ
መወያያ ጽሑፍ አቅራቢዎች፡ ዶ/ር አበባው ማናዬ እና ሳራ ሞገስ
ማስታወሻ ከታቢ፡ ቢኒያም ተስፋዬ
ክፍል አንድ - ዳሰሳ እላፊ
ከቀኑ 10፡01 ሲል የዕለቱ አጋፋሪ የብራናን ባህል ተከትሎ የዕለቱን መርሃ-ግብር በማስተዋወቅ መድረኩን መፅሐፉን ከስደትና ከስነልቦና አንፃር ለቃኙት ዶ/ር አበባው ሰቷል፡፡ ዶ/ር አበባው በቅድሚያ እንደ ግለሰብ በመፅሐፉ ላይ ያላቸውን አስተያየት አጋርተዋል፡፡ ሰዎችን በማየት ብቻ መፈረጅና መፍረድ በበዛበት ሀገር ፀሐፊው ባህሉን ተገንዝቦ ነገር ግን ከፍርድና ከፍረጃ ነፃ የሆነ አቀራረብ መከተሉ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት በስደትና ተያያዥ ጉዳዮች ሰርቻለሁ በብዛት የሚቀርቡ የጥናት ፅሑፎች ደረቅ ሆነው ነው ያገኘኋቸው እላፊ ግን ህይወት ህይወት እንዲሸት ተደርጎ የቀረበ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከኢኮኖሚ እስከ ማህበራዊ ህይወት፤ ከፓለቲካ እስከ መንፈሳዊ ጉዳዮች ይዳስሳል መፅሐፉ፣ አልፎ አልፎ ወጣ ያሉ ሐሳቦችን ያስነብበናል (ለምሳሌ የማህበረሰብን አምባገነንነት)፡፡ በተጨማሪም የግርጌ ማስተወሻዎቹን እንደ ምክረ ሐሳብ ነው የወሰድኳቸው ያሉት ዶ/ር አበባው ተቃርኖዎችን የወሰደበት መንገድ በህይወታችን ያሉብንን ተቃርኖዎችና ያንንም እየመረመርነው እንዳልሆነ አሳይቶናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሀገራዊ እሴቶቻችንን የቢራ ስሞች በዚህ ደረጃ እንደተቆጣጠሯቸው አላስተዋልኩም ነበር መፅሐፉ ያንን እንዳይ አድርጎኛል ብለዋል፡፡
በመቀጠል ምሁራዊ አስተያየታቸውን ያካፈሉት ዶ/ር አበባው የስደትን ምንነት በማስረዳት ጀምረዋል፡፡ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ መኖሪያቸውን ለቀው ከአንድ ሀገር ወደሌላ ሀገር ወይም በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ/ሲሄዱ ተሰደዱ እንላለን ካሉ በኋላ በማያያዝም ከአንድ ቢሊየን በላይ ስደተኛ በዓለማችን የተመዘገበ ሲሆን ከ273ሚሊየን በላይም ሀገሩን ትቶ የተሰደደ ነው ብለዋል፡፡ ስደት የምናጣጥለው አሊያም የምናንቆለጳጵሰው ጉዳይ አይደለም ነገር ግን የዓለምን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ስነ-ሕዛባዊ እና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ የቀረፀ ነው፡፡ ስደት ብሔርተኛ የሁኖ ኃይሎች አገንግነው እንዲወጡ ምክንያት ነው፣ ስደት አሜሪካን የመሰሉ ሀገሮች የተገነቡበትም ሂደት ነው ብለዋል ዶ/ር አበባው፡፡ እላፊ የደቡቡ የስደት መስመር ላይ ተመርኩዞ የተዘጋጀ ሲሆን የኔ የስራ ልምድ ደግሞ የሰሜን ምስራቁ ላይ ያተኮረ ነው ይሉና ስደት የባህልና የክህሎት ሽግግር ያመጣል በአንፃሩ ደግሞ ዜጎች ይጎዱበታል ይህንንም መፀሐፉ ቁልጭ አድርጎ አቅርቧል ሲሉ ሀሳባቸውን ከሰዓት ገደብ ጋር አጠናቀዋል፡፡
በመቀጠል የመፅሐፉን አጭር ዳሰሳና ወመያያ ሐሳብ ያቀረበችው ሳራ ሞገስ ከሽፋን ገፁ የተነሳች ሲሆን ጀንበርን፣ ድንበርን፣ ባህርን፣ በራሪ ወፎችን ቀረብ ሲሉት ግን የሽቦ አጥርን ያቀፈውን የመፅሐፉን ሽፋንና አቀራረብ ሳቢ ብላዋለች አያይዛም ፀሐፊው መሰል የሽፋን ስዕሎችን ጎላ የማድረግ ሁኔታ በመጀመሪያ መፅሐፉም መጠቀሙን አውስታለች፡፡ ሳራ ዳሰሳዋን ስትቀጥል የብዙ ሰዎችን ኑሮ ቀለል፣ ለዘብ ባለ አማርኛ ለማስረዳት ሞክሯል መፅሐፉ ትልና በስነ-ቃል፣ ዘፈን እና ቀልዶች ታጅቦ መቅረቡ ለማንበብ ሳቢ አድርጎታል ብላለች፡፡
በመቀጠል የመፅሐፉ ፋይዳ በሚል፤ መሰል ጥናታዊ ጽሁፎች ድርቅ ያሉ ጽሑፎችን የሚያቀርቡ ሲሆን እላፊ ግን በተዋዛ አቀራረቡ ስነ-ጽሑፋዊ አበርክቶው የጎላ ነው፣ ማጠቃለያ በሚለው ክፍል የቀረቡት ሐሳቦች ለፖሊሲ አውጪዎች እንደ ግብዐት የሚያገለግሉ ናቸው፣ መፅሐፉ አንባቢ የራሱን ድምዳሜ እንዲወስድ ዕድል ይሰጣል እንዲሁም እንደ ሀገር የወደቁ ስርዐቶቻችንን (ትምህርት፣ ጤና፣ የአገልግሎት ዘርፍ) ያወሳል በማለት የመፅሐፉ ፋይዳዎች ያለቻቸውን በአጭሩ ለታዳሚው አቅርባለች፡፡
በማጠቃለያዋም ለውይይት ቢሆኑን በማለት የመሚከተለሉትን ነጥቦችን ሰንዝራለች፡-
 መፅሐፉ Neo-classical የኢኮኖሚ ንድፈ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ይመስለኛል፤ ስለዚህም ሌሎች የስደትን መግፍኤ ምክንያቶችን ወደ ጎን በመተው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖችን ብቻ በሰፊው ያወሳል፤
 በስደት ላይ ያሉ ጋሬጣዎችን/ ችግሮችን በሰፊው አላነሳም፤
 መጽሐፉ ሴቶች ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ሰጪነታቸው ይጨምራል ቢልም ፆታ ተኮር ጥቃትን ግን በደደብዛዛው አልፎታል፤
 የተለያዩ ጽሑፎች መንግስት ስደትን የማመቻመች ሚና እንዳለው ያወሳሉ በእላፊ መጽሐፍ ግን ይህ ጉዳይ ሳይነሳ ታልፏል፤
 በመጽሐፉ የተገለፁ ገጸ-ብህርያት የጸሐፊውን ማንነት ባወቁበት ሁኔታ ተዐማኒነት ያለው መረጃ ይሰጡታል ብሎ ማሰብ ይቻላል ወይ ስትል ታጠይቃለች፡፡
ክፍል ሁለት - ውይይት በእላፊ
መድረኩ ለተሳታፊዎች ክፍት መሆኑን ተከትሎ በሁለት ዙር ከተሳታፊዎችና ከመድረክ ሀሳቦች እየተሰነዘሩ ውይይት በእላፊ መፅሐፍ ላይ ተደርጓል፤ በአጭሩ በምናብ ቦታው ላይ እንመለስማ፡-
መፅሀፉ ትልቅ ስራ ነው፣ ዘርፍ ብዙ ነው፣ አቀራረቡ ማራኪና ተነባቢ ነው የሚሉ ሐሳቦች በተደጋጋሚ ከተወያዮች የተሰጡ ሲሆን መፅሐፉን በሁለት መልኩ ከፍዬ አየዋለሁ ያለች ተሳታፊ ስነ-ጥበባዊና ጥናታዊ ያለቻቸውን ነጥቦች አውስታለች፡፡ በእላፊ ውስጥ ያሉ ስነ-ቃሎች፣ ግጥሞች፣ ተረኮች፣ ወጎች እና አስቂኝ ገጠመኞች ስነ-ጥበባዊ ጎናቸው የጎላ እኛንም ከዛኛው ዘመንና ከገጠሩ ህዝብ ጋር ያስተዋወቁን ናቸው ሰትል እንደ ጥናትም መጽሐፉ በገጸ-ባህሪያቱ ውስጥ ሀገሬን እንዳይ አስችሎኛል በማለት አጠቃላለች፡፡
በውይይቱ ወቅት ጎልተው ከተሰሙ የመጽሐፉ ጭብጦች መካከል ‹‹መፈናፈኛ› እና ‹‹ መባከን›› ዕለቱን ተቆጣጥረውት ውለዋል፡፡ እንደ ማህበረሰብ ልጆችን መፈናፈኛ ማሳጣት በብዙ አውድ የታየ ሲሆን ለፀሐፊውም እንዲያብራራው ጥያቄ ቀርቦበታል፤ በሌላ በኩልም የጠበቁትን አለማግኘትና ከሀገር ከወጡ በኋላ ባክኖ መቅረት ላይም ሀሳብ እንዲሰጥበት በተወያዮች ተጠይቋል፡፡
እላፊ ጆሀንስ በርግን ከአዲስ አበባ ጋር በማነፃፀር ያቀረበበት መንገድ ጥሩ ቢሆንም አሁን ላይ እየታዩ ካሉ ሁኔታዎች አንፃር (ለምሳሌ የዘረፈ ወንጀል መስፋፋት) እኛስ ወደዛ እየሄድን አይደለም ወይ በማለት ተወያዮቹ አጠይቀዋል፡፡ ስደት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ያቀፈ፤ ትልቅ ዓለምአቀፍ መነጋገሪያም ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ጠላት›› ብለን የፈረጅናቸው ሀገራት ስደተኞችን ሊጠቀሙ አይችሉም ወይ ያለ ውይይቱ ተሳታፊ አያይዞም ለሀገር ደህንነትም ስጋት ስለሆነ የህግ ማዕቀፍ ሊበጅለት ይገባል ብሏል፡፡ ሌላ ተሳታፊ በበኩላቸው የውይይት አቅራቢው በሰሜን ምስራቁ ስደት ላይ ልምድ ያላቸው እንደ መሆኑ መጠን በመጽሐፉ ከተወሳው የደቡብ ስደት ጋር በማነፃፀር ቢያቀርቡልን ብለው ጠይቀዋል፡፡