Get Mystery Box with random crypto!

ቃል (እንዳለጌታ ከበደ) /እውነተኛ ታሪክ/ ቃልኪዳንን ያወቅኳት በጓ | ስለ መፅሀፍት በጥቂቱ

ቃል
(እንዳለጌታ ከበደ)
/እውነተኛ ታሪክ/
ቃልኪዳንን ያወቅኳት በጓደኛዬ በማኅደረ ታሪኩ አማካይነት ነው፡፡ ስልክ ቁጥሬን ከእሱ ከወሰደች፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ከደወለችልኝ በኋላ፣ በአካል ለመገናኘት በቃን፡፡
ቃል ኪዳን የኪነጥበብ ሰው መሆን እየፈለገች፣ መድረስ የምትፈልግበት ቦታ እንዳትደርስ ብዙ እንቅፋት በመንገዷ ተጋርዷል፡፡
ማኅደረ፣ ሊታዘንላት የሚገባና መንገድ የጠፋባት ልጅ መሆኗን ነግሮኛል፡፡ በአካል ሳገኛትም የገባኝ እውነት ይሄ ነው፡፡ ቃልኪዳን የማየት ችግር አለባት፡፡ ግን ችግር ያለባት አትመስልም፡፡ ዓይኖቿ ያሳስታሉ፡፡ የሚያዩ ይመስላሉ፡፡ መነጽር አትጠቀምም፡፡ ዘንግ አትይዝም፡፡ እጇን ይዘው የሚመሩ፣ ወደምትፈልግበት የሚያደርሱ ብዙ ወዳጆች አሏት፡፡
ንቁ ናት፤ ቀልጣፋ፤ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አብረዋት ካሉ ሰዎች ጋር የወዳጅነትን መንፈስ በቶሎ መፍጠር የምትችል፡፡ ከእኔ ጋር አራት ኪሎ፣ ማለዳ ካፌ ተቀጣጥረን በተገናኘንበት ጊዜ፣ የሰነበተ ወዳጅነት ያለን እንጂ የዕለቱን ዕለት የተዋወቅን አንመስልም ነበር፡፡ ሳቋ ሞቅ ያለ ነው፤ ፈገግታዋ የደመቀ፡፡ ጠይም ናት፤ ባለመካከለኛ ቁመትና ለጥቂት ከቅጥነት ያመለጠ ሰውነት ያላት፡፡
ማኅዲ እንደነገረኝ ቃልኪዳን የደረጃ ተማሪ ናት፡፡ አጥንታ አይደለም፡፡ ደብተር ላይ መተከል አልወድም የምትለው ነገር አላት፡፡ የሰማችውን ስለማትዘነጋ ነው የደረጃ ተማሪ የሆነችው፡፡ እኔ ሳገኛት 17 ዓመቷ ነበር- የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ…
ጮክ ብላ አታወራውም እንጂ አባቷ ስመጥር ድምጻዊ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በህይወት ዘመናችን ከምናደንቃቸው ዘፋኞች መካከል አምስቱን እንድንጠራ ብንጋበዝ፣ የእሷ አባት የመጠቀስ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ድምጻዊ ግን ‹ልጄ ናት!› አይልም፡፡ ከሚስቱ ሰርቆ ነው የወለዳት፡፡ ታደንቀው ከነበረ፣ ከአንዲት የአዲስ አበባ ልጃገረድ የወለዳት ይህቺ ሴት፣ መልኳ እሱን ነው የሚመስለው፡፡ ጓደኞቹ፣ ወዳጆቹ እና አንዳንድ የማይመለከታቸው ሰዎች ሁሉ ይህንን ምስጢር ያውቃሉ፡፡ ያቀርቧታል፤ ያጫውቷታል፤ ያበረታቷታል፡፡
እሷም ዘፈን ትወዳለች፤ የአባቷን ዘፈኖች አስመስላ ታንጎራጉራለች፡፡ መድረክ ላይ አይደለም፡፡ ደስ ሲላት፣ ደስታ የሰጣትን ሰው የምታመሰግነው፣ ከዋለላት ውለታ ጋር ተዛማጅነት ያለውን አንድ ዘፈን በመዝፈን ነው!
ቃልኪዳን ቆንጆ የምትባል ዓይነት ሴት አይደለችም፡፡ ዐይኗን ያጣችው ካደገች በኋላ ነው፡፡ በርግጥ ዐይኗን፣ አባቷንና የጀርባ አጥንቷን (ስፓይናል ኮርዷን) ያጣችው በለጋ ዕድሜዋ ነው፡፡ ከባድ የሆነ ራስ ምታት ነበራትና፣ ሀኪም ቤት ሄደች፡፡ ሐኪሙም ‹ያደረባት በሽታ ከኔ ችሎታ በላይ ነው፤ መታከሚያ መሣርያውም ያለው አንድ ቦታ ብቻ ነው፤ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል! እዚያ ሂዱ!› ብሎ ሰደዳቸው፡፡
ሄደች፡፡ እናቷና የእንጀራ አባቷ እያዋከቡ ወሰዷት፡፡ ተደናግጠው፡፡ ቃልኪዳን አልጋ ትያዝ ተባለ፡፡ ያዘች፡፡
አንድ ቀን ማታ፣ ጤንነቷን ይከታተል የነበረው ነርስ፣ ሌሊት ቀስቅሶ፣ አስታማሚዋንም አስነስቶ ‹ክኒን አላት!› አለ፡፡ ቃልኪዳን ክኒን መዋጥ አትወድም፡፡ እንደማትወድ ነርሱ ያውቃል፡፡ ‹በመርፌ ይቀየርልኝ!› ብላ ወትውታውም አልሠማትም ነበር፡፡ ያን ሌሊት መጣና፣ ሁለት ክኒን ፍሬ መዳፏ ላይ ሲያኖር ግን አልተሳቀቀችም፡፡ አልተነጫነጨችም፡፡ ‹ክኒኑን ቀየራችሁት እንዴ?› አለች፤ ‹ሰሞኑን በተከታታይ ሌሊት ተነስቼ የዋጥኩት ክኒን በቀለሙም በመጠኑም ይህን አይመስልም!› አለችው በዝግታ፡፡ ነርሱ ተቆጣ፡፡ ‹የማደርገውን አውቃለሁ› አለ፡፡ ‹አሞሽ ስለነበር፣ የክኒን ጥላቻም ስላለብሽ ነው እንጂ ሰሞኑን የዋጥሽው ክኒን ይሄ ነው!› አላት፡፡ አስታማሚ ዘመድም፣ ‹ቃልዬ! ላንቺ ብሎኮ ነው፡፡ ለመዳን መታከም አለብሽ!› አለቻት፡፡
ቃልኪዳን ክኒኖቹን ዋጠቻቸው፡፡
ሌሊቱን በሙሉ ስትሰቃይ አደረች፡፡ አጠገቧ አንድ ጎልማሣ ሰው አለ፤ በጀርባ ህመም ክፉኛ የተሰቃየ፡፡ ልክ እሱ ያቃጥለኛል እንደሚለው ስትቃጠል አደረች፡፡ መተኛት ከበዳት፡፡ ኧረ ምን ሆኛለሁ? አለች፡፡ መድኃኒቱ እየሠራ ቢሆን ነው አለቻት አስታማሚዋ - ከእንቅልፏ ጋር እየታገለች፡፡ ቃልኪዳን አልቻለችም፤ ሕመሙ አልተዋት አለ፤ አቁነጥንጦ፣ አቅበጥብጦ፣ አቃጥሎና አሰቃይቶ ብቻ አልተዋት አለ፡፡ ነርሱን ካልጠራሽልኝ! አለቻት አስታማሚዋን፡፡ አስታማሚዋ አመንትታ ነበር፡፡ ሌሎች ታማሚዎችና አስታማሚዎች ግን ይህ ስቃይ ካልተገታ እረፍት አጥታ እረፍት እንደምታሳጣቸው በማመን ነርሱ ይጠራ አሉ፤ አስታማሚዋን ላኳት…
መጣ፤ ነርሱ መጣ፤ መጣና ማስታገሻ ሰጣት፡፡
ቃልኪዳን በአዲስ በሽታ ተጠቃች፡፡ ለመነሳት ሞክራ ነበር - ሽንት ቤት ለመሄድ፡፡ ግን አልቻለችም፡፡ ተንገዳግዳ ወደቀች፡፡ ወገብዋ ለሁለት የተከፈለ መሰላት፡፡ ራስ ምታቷ ከደቂቃ ወደ ደቂቃ ከፍ እያለ መጣ፡፡ አሁን እሷ ብቻ ሳትሆን መላ ቤተሰቧ በድንጋጤ ተመታ፡፡ ምን እየሆነችብን ነው አሉ፡፡ ለዶክተሮቹ ነገሯቸው፡፡
ዶክተሮቹ መቸ እንደጀመራት ጠየቁ፤ ክኒኑን ከወሰደች በኋላ እንደሆነ ተነገራቸው፡፡ ምን ዓይነት ክኒን እንደወሰደች አጥብቀው ሲጠይቁ፣ የክኒኑ ዓይነትና ክኒን ለመውሰድ ቃልኪዳን እንዴት አንገራግራ እንደነበር ተነገራቸው፡፡ የክኒኑን ዓይነት ካወቁ በኋላ ዶክተሮቹ ስሜታቸውን መደበቅ አልሆነላቸውም፡፡ ሀዘንም አረበባቸው፡፡ ነርሱ ስህተት እንደሰራና ያልተገባ መድኃኒት እንዳስወሰዳት ተናገሩ፡፡ መድኃኒቱ የታዘዘው ለእሷ ሳይሆን እሷ አጠገብ ታሞ ለተኛው፣ በጀርባ ህመም ለተሰቃየው ሰው ተሰናድቶ የነበረ ነው፡፡
ቃልኪዳን የማየት ሃይሏ እየደከመ መጣ፡፡ ሁሉም ነገር ብዥ፣ ጭልም ይልባት ገባ፡፡ እየታወረች መሆኑንም ታወቃት፡፡ ማየት አለመቻሏ ብቻ ሳይሆን፣ ዓይኗ ተከፍቶ ቀለም የማይለይና እንቅስቃሴ የማይረዳ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ በከባድ ራስ ምታት ተጠቃች፡፡ ሞቷን መመኘት ጀመረች፡፡
ቤተሰቦቿ፣ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በምን እንደሆነ ያውቃሉና፣ ሆስፒታሉን ካልከሰስነው፣ ነርሱን ፍርድ ቤት ካላቆምነው በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ፡፡
ዶክተሮቹና ነርሶቹ ግን፣ እናቷንና የእንጀራ አባቷን ደጅ ጠንተው፣ የሚያጋጥምና በቀላሉ ወደነበረበት የሚመለስ ነው የህክምና ጉድለት አሉ፡፡ በህይወት ዘመናቸው ቆጥረው የማያውቁትን ብር ሰጧቸው፡፡ ማየቷ ከህመሟም መፈወሷ አይቀርም አሉና ወደ ክስ እንዳይሄዱ ለመኗቸው፡፡
የቃልኪዳን ቤተሰቦችም፣ ከሀኪሞቹ በላይ አናውቅም አሉና በዚያ ብር ለቃልኪዳን ማባበያ ይሆናት ዘንድ ልብሶች፣ ጫማዎች ገዙላት፡፡ በዚህ ገንዘብ የሕይወታቸው አቅጣጫ ለጥቂት ወራትም ቢሆን ተቀየረ፡፡ በቀን ሶስት ጊዜ በልተው እንደሚያድሩ ሰፈርተኛው እንዲያውቅ አደረጉ፡፡
ይህ ሁሉ ከሆነ፣ ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ አንድ ቀን፣ ቤት ውስጥ ከቤተዘመድ ጋር ሞቅ ያለ ጨዋታ እየተደረገ ሳለ፣ ‹አንድ ጊዜ ዝም በሉ!› አለቻቸው፡፡ ምን ሰማች ብለው ፊታቸውንና ጆሯቸውን ወደሷ ሲመልሱ፣ ‹የቲቪውን ድምጽ ጨምሩት፤ ቶሎ በሉ፤ ቶሎ፤ ቶሎ!› አለቻቸው አጣደፋ፡፡