🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

ኢንተርን ማለት ሲልኩት እንቢ ማለት የማይችል ፥ ግዴታ እንጂ መብት የሌለው ፥ ለእርድ የተዘጋጀ በ | Medical School 🇪🇹

ኢንተርን ማለት ሲልኩት እንቢ ማለት የማይችል ፥ ግዴታ እንጂ መብት የሌለው ፥ ለእርድ የተዘጋጀ በግ ነው፡፡
.
አንዳንዶች ኢንተርንሺፕ (Internship) የሚለውን "Internsheep" ብለው ይፅፉታል። ለመሆኑ ይህ በየሆስፒታል ኮሪደሮች ፥ በየላቦራቶሪዎች ፥ በየመኝታ ክፍሉ የማታጡት ፍጥረት ማነው? አንድ ጊዜ ታካሚው ሌላ ጊዜ አስታማሚው ከፍ ዝቅ የሚያደርገው ፥ ሰርቶ ለፍቶ ያለ ምስጋና ወደ ቤቱ የሚገባው ትሁት ግለሰብ የስራ ድርሻው ምንድነው?
.
በነገራችን ላይ ኢንተርን ማለት የመጨረሻ አመት ተመራቂ ሀኪም ነው፡፡ ይህ ሰው "ሀኪም" የሚለውን ትልቅ ስም ተሸክሞ ነገር ግን በተጣለበት ከባድ ኀላፊነትና በሚደርስበት በደል ቀኑን ሙሉ ሲታትር ይውላል።
.
ኢንተርን ከስራ በኃላ እንዳይዝናና የሚረባ ደሞዝ እንኳን የለውም ፣ የሚጋብዘው ሰው ቢገኝ እንኳን ከድካሙ የተነሳ ለመዝናናት የሚበቃ ሀይል የለውም ፤ ብቻ ከሳምንት እስከ ሳምንት የሲኔርና የረዝደንት ምች እየመታው ፊቱ ላይ እብጠትና ቁስለት ሳይታይበት የሚኖር ፍጥረት ኢንተር (ተለማማጅ ሀኪም) ነው፡፡
.
አንዳንዱ ረዝደንት (የእስፔሻሊቲ ተማሪ ሀኪም) የሰፈር ጎሮምሳ ይመስል ይህን ምስኪን ፍጥረት ሲያሸማቅቀውና ሲያሳቅቀው ይውላል ፤ በቀኑ መጨረሻ ኢንተርኑ በሰራው ስራ ይመሰገናል፡፡
.
ይህ ሁሉ በደል ቢደርስበት እንኳን ኢንተርን ከሌሎች ሀኪሞች ጥሩ ልብ ያለው ልዩ ፍጥረት ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ቀን እስኪያልፍ ድረስ አንድ ፀሀፊ እንዳሉት አንድም ከፊደል "ሀ" ብሎ ሁለትም ከአሳር "ዋ" ብሎ በትዕግስት ይማራል፡፡ ያቺን ቆብ እስኪደፋ አንገቱን ደፍቶ ይኖራል፡፡
.
አንድ ኢንተርን ስራ መቅረት የሚችለው ለራሱ ቀብሩ ብቻ ነው ይባላል፡፡ በማግስቱ ቀኑን ሙሉ የለፋበትን ሳይሆን እንዲያቀርብ የታዘዘውን ብቻ ያቀርባል፡፡ ተስፋውም ነገ ተመርቆ ያለ ማንም ጫና ህሊናውንና አምላኩን ሳያሳዝን ለመስራት ይናፍቃል፡፡ ይህ ኢንተርን 365 ቀን ቆጥሮ ይመረቃል፡፡ ለዛች ቀን ለመድረስ ግን የእርሱ ጥረት ብቻ ሳይሆን የወላጆቹም ፀሎት ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ምስኪን ፍጥረት የሚከራከር አካል አንድ ቀን ይፈጠር ይሆን?
.
ዶ/ር ያሬድ አግደው ፤ የቀዶ ህክምና ሐኪም