🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

【ይድረስ ለእቃቃ ሚስቴ...】 መልክሽ ጠፍቶብኛል። ስምሽም ትዝ አይለኝም። አንቺነትሽ ግን ፈፅ | Scribbles

ይድረስ ለእቃቃ ሚስቴ...

መልክሽ ጠፍቶብኛል። ስምሽም ትዝ አይለኝም። አንቺነትሽ ግን ፈፅሞ አልተረሳኝም፡፡ እስቲ ልጠይቅሽ...

ትዝ ይልሻል እንዴ?
የኔም ያንቺም እናት "ደጉ ጊዜ'' 'ሚሉት
ያ ልጅነታችን?
ተጋብተን፣ ተፋተን፣ ቤት ሰርተን አፍርሰን
ህይወትን ስንኖራት በንፁህ ልባችን?
ሙከራ 1 2 3፣ 1 2 3 4
የኔና የአንቺ ህይወት
ያ ቀላሉ ጊዜ
የተጫወትንባት፣ የተሞሸርንባት
ጊዜን አርገን ሚዜ
ትዝ ይልሻል ያኔ?

አልዋሽሽም። እኔ እምብዛም ትዝ አይለኝም። አንዳንዴ እንቅልፍ አጥቼ እንዲህ በሌሊት ስቀመጥ ግን ሳቅሽ ትዝ ይለኛል፡፡ ጥርሶችሽ ምን ይመስሉ እንደነበረ ፈፅሞ ተረስቶኛል፡፡በደንብ አስቅሽ እንደነበረ ግን አስታውሳለሁ። ፀጉርሽን እየጎተትኩ አስለቅስሽ እንደነበረም ትዝ ይለኛል፡፡ አዎ። ፀጉርሽ ረጅም እንደነበረ በደንብ አስታውሳለሁ። አሁን ተቆርጠሽው ይሆን?

የእቃቃ ሚስቴ፣ ይህ የፍቅር ደብዳቤ አይደለም፡፡ የምፅፍልሽ ስላልረሳሁሽ አይደለም፡፡ ረስቼሻለሁ፡፡ ብዙም ትዝ አትይኝም። ቆም ብዬ ያለፉትን ጊዜያት ሳስታውስ ግን ይገርመኛል፡፡ ስለዚህ ልጠይቅሽ...

ትዝ ይልሻል ያኔ?
ጀምበር አዘቅዝቃ፣ መሄጃችን ሲደርስ
ምን ነበር የምንል? አስታውሺኝ በሞቴ፡፡
የራት ሰአት ደርሶ ስትሄጂ ቤትሽ
እኔም ስሄድ ቤቴ።
ዛሬ ባዜምልሽ እንደው ትዝ ይልሻል?
ወይስ ልክ እንደኔ ያን ደጉን ልብሽን አውጥተሽ ጥለሻል?
አንቺ የልጅነቴ፣ የእቃቃ ሚስቴ
ትዝ ይልሽ ከሆነ አስታውሺኝ በሞቴ
ያን መልካሙን ልብሽ፣ ያን ደጉ አንደበቴ
ሰጥተን የበዛልን ያን መልካሙ ጊዜ፡፡

የምፅፍልሽ ለዚህ ነው። እኔ ትዝ አይለኝም፡፡ በእርግጥ አስታውሰዋለሁ፡፡ የማስታውሰውን ንፁህ ሰው ስሆን ግን ትዝ አይለኝም:: ልክ ከአመታት በፊት እንዳየሁት ፊልም ግን ያ ጊዜ በእርግጥ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ አንቺ ንገሪኝ...

ትዝ ይልሻል እንዴ?
የኔም ያንቺም እናት ሁሌ የሚያነሱት
ያ መልካሙ ጊዜ?
የተጫወትንባት፣ የተሞሸርንባት
ጊዜን አርገን ሚዜ
ትዝ ይልሻል ያኔ?

አንቺ ትዝ አትይኝም። ያን ጊዜ የነበርኩትን እኔንም እምብዛም አላስታውስም፡፡ ከፍቅር የተመሰረተ እኛነታችን ግን ትዝ ይለኛል። የእቃቃ ሚስቴ፣ ድንገት ዛሬ ብንገናኝ እጅሽ በፍቅር አቅፎ ይቀበለኛል? ወይስ በጊዜው የማናቀውን ጥያቄ፣ ዛሬ አፍሽ ስለማንነቴ ደፍሮ ይጠይቀኛል?

ተቀይረሻል? እኔ ተቀይሬያለሁ፡፡
አቡክተን ቤት በሰራንበት አፈር
ብዙ ሰዎችን ቀብሬያለሁ።
በሳቅንበት መንደር
ብዙ እንባ አፍስሻለሁ።
እንዲያም ሆኖ ግን ትዝ ይለኛል
ያ የምንዘምረው መዝሙር በህብረት
መሸቶ ጨረቃ ስትወጣ፣ ሁላችንም ስንሄድ ወደ ቤት
.
.
.
"ወደ ቤት፣ ወደ ሀገር ቤት
አንድ እንጀራ ለኛ፣ ሌላዉ ለጎረቤት
"
.
.
.
ታዲያ ትዝ ይልሻል?
መቋጫችን ሀገር፣ መስጠት ልማዳችን
የነበረበትን ያ መልካሙ ጊዜ?
ያ ጣፋጩ ልብሽ፣ ያ ደጉ አንደበቴ፡፡
ይድረስ ላንቺ ውዴ
ለእቃቃ ሚስቴ፤
ማነህ፣ ማነሽ ሳንል የተዋደድንበት
የኔና ያንቺ ጊዜ
ያ ነበር፣ ያ ድሮ፣ ወዴት ጠፍቶ ይሆን
አስታውሺኝ እስቲ አንዴ፡፡


#RANDOM_THOUGHTS