Get Mystery Box with random crypto!

ውድቅት ሌሊት ማታ ከእግዜሩ ጋር እንቆቅልሽ ጨዋታ፡፡ ለምን? እንቅልፍ የለኝም፡፡ ደንግጬ ስነቃ እ | Scribbles

ውድቅት ሌሊት
ማታ
ከእግዜሩ ጋር
እንቆቅልሽ ጨዋታ፡፡
ለምን?
እንቅልፍ የለኝም፡፡
ደንግጬ ስነቃ እንዳልጸልይ
ይቅር በለኝ እንድል፣ ይቅር ያለ ልብ የለኝም፡፡
ስለዚህ፣ በጸሎት ፋንታ
ከእግዜሩ ጋር
እንቆቅልሽ ጨዋታ፡፡

እንቆቅልሽ አልኩት
ኹሉን ለሚያውቅ ጌታ፡፡

ስለሚያውቅ ለምን እንደጀመርነው
በጸሎት ፋንታ፣ በእንቆቅልሽ ልለምነው።

ምን አውቅልሽ ብሎ፣ አላውቅም እንዲለኝ
ጠይቄው ምላሹን፣ አልኩት አትንገረኝ፡፡

ለምን?
እስቲ መልሱን ሲለኝ
እንድል ሃገር ስጠኝ።

ልለው...
ኖራ ይሆን፣ ፈጥሬያት በምናቤ
የወደድኳትን፣ ያቺን ሃገሬን
እንቆቅልሼን አላውቅም በልና
ኢትዮጵያን ስጠኝ እንደገና፡፡

ታሪክ ብማርም
ታሪክ አላምንም፡፡
ስለዚህ፣
እንዳሉት ከነበረች መልስልኝ
ካልነበረችም ፍጠርልኝ።
ብቻ ለዚህ ልቤ አንድ መፍትሔ አበጅልኝ፡፡
እንቆቅልሼን አላውቅም ብለኽ፣ ጦቢያን እንደዐዲስ ሥራልኝ፡፡


ውድቅት ሌሊት
ማታ
ከእግዜሩ ጋር
እንቆቅልሽ ጨዋታ፡፡
እያወቀ አላውቅም እንዲለኝ።
ከዚያስ?
ከዚያማ ሃገሬን ስጠኝ።


#RANDOM_THOUGHTS