Get Mystery Box with random crypto!

ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ ኦፍታኤ ዳዊት( ካነበብኩት) ከወዳጅ ከዘመ | የኛ🔊

ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ

ኦፍታኤ ዳዊት( ካነበብኩት)

ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ
ተሸሽጎ ተገልሎ፥
ተሸማቆ ተሸምቆ
ከቤተ-ሰው ተደብቆ
መሽቶ - የማታ ማታ ነው - ሌት ነው የወንድ ልጅ ዕንባው
ብቻውን ነው የሚፈታው
ብቻውን ነው የሚረታው
ችሎ ውጦ ተጨብጦ ተማምጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተወጥሮ
እንደደመና ተቋጥሮ
ውስጥ አንጀቱ ተቀብሮ
መሽቶ ረፍዶ - ጀምበር ጠልቆ
የጨለማ ድባብ ወድቆ
በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ - በዝምታ ሲዋጥ ሀገር
ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ - ብቸኝነት ብቻ ሲቀር
የኋላ የኋላ - ማታ
ምድር አገሩ በእፎይታ
ዐይኑን በእንቅልፍ ሲያስፈታ
ሁሉ በእረፍት ዓለም ርቆ - ብቸኝነት ብቻ ሲቀርብ
ያኔ ነው - ወንድ ዐይኑ የሚረጥብ
የብቻ ዕንባ - ወዙ እሚነጥብ
ብቻውን ነው - ብቻውን ነው
የዕንባ ጨለማ ለብሶ ነው
ወንድ ልጅ - ወዙ እሚነጥበው
እጣውን ለብቻው ቆርሶ
ብቻውን ሰቀቀን ጎርሶ
ብቻውን ጨለማ ለብሶ
ገመናውን ሳግ ሸፍኖ
ክብሩን በሰቆቃ አፍኖ
ሌሊት የማታ ማታ ነው
ህቅ እንቁን እሚነጥበው
ኤሎሄውን እሚረግፈው
ከዐይኑ ብሌን ጣር ተመጦ
ከአንጀቱ ሲቃ ተቆርጦ
ደም አልሞ ፍም አምጦ
ከአፅመ-ወዙ እቶን ተፈልጦ
ከአንጀቱ ሲቃ ቆርጦ
እንደጠፍር ብራቅ እምብርት
እንደእሳተ ገሞራ ግት
ሩቅ ነው ወንድ ልጅ ዕንባው
ደም ነው ፍም ነው ዕሚያነባው
ንጥረ ህዋስ ነው ሰቆቃው
ረቂቅ ነው ምሥጢር ነው ጣሩ ብቻውን ነው የሚፈታው
ብቻውን ነው የሚረታው
ችሎ ውጦ ተጨብጦ
ሰቀቀኑን በሆዱ አጥሮ
በአንጀቱ ገመና ቀብሮ
ውሎ ጭጭ እፍን ብሎ
እንደደመና ተቋጥሮ
ጣሩን ውጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተሰትሮ
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
ከቤተ-ሰው ተደብቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ
ተሸሽጎ ተከናንቦ
ተሸማቆ ተሸምቆ
የብቻ ብቸኝነቱ
የጨለማ ልብሱ እስኪደርስ
ባይን አዋጅ ሃሞቱ እንዳይረክስ
ቅስሙ በገበያ እንዳይፈስ
ተገልሎ በእኩለ-ሌት - ወንድ ብቻውን ነው እሚያለቅስ"
ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ.አ