Get Mystery Box with random crypto!

#ኑሮና_ትግሉ . . . ድካም ከነልጅህ መዛልና ወዳጅህ፣ መጠማት ቁርጥማት፤ ህመም ገላዬ ሁን ሀዘን | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

#ኑሮና_ትግሉ
.
.
.
ድካም ከነልጅህ መዛልና ወዳጅህ፣
መጠማት ቁርጥማት፤
ህመም ገላዬ ሁን ሀዘን ሆይ እቀፈኝ፣
ማጣት አዝለኸኝ ዙር መታረዝ ግረፈኝ።
ወንድ ሀሞቴ ፍሰስ፣
ቀና እስክትል ድረስ።
ሲሻህ ገደል ግባ!!  "የለውም" ሁን ወኔ፣
ለማሸንፍ ሲቃን የማልቀበለው ማነኝና እኔ ?

በል ቶሎ በል ድካም፤
በል ቶሎ በል ህመም፤
በማጣት ፍላፃህ ስስ ልቤን ተርትረው፣
በሀዘን ኩታህ ስፌት አካሌን መትረው።
እንዲቆረቁረው፤
እንዲሸነቁረው ነፍሴ እክል ይግጠመው፣
ሽንፈት ያየ ሰው ነው፤
ደክሞት ያመጣውን ድል የሚያጣጥመው።

ብርታት የእናት አባት፤
ሽንፈት ውርስ አይደለም፤
ጀግና መሆን የዘር የሚያገኙት በደም፣
ወይም ወጥተው መቅረት፤
የነፍስ እጣ አይደለም ሲታገሉ መውደም።
እናም እላለሁ........
ሞት ከነወንድሙ ሊወስድ እስትንፋስህ፣
የመቃብር ደጃፍ እስኪያውክ መንፈስህ።
መናኛ በርህን፤
እስኪቆረቁረው ቆሞህ ከመጠብቅ፣
ደጁ ድረስ ሄደህ አንገቱን ነው ማነቅ።
መጋልና መብረድ፤
መውጣትና መውረድ፤
አጥንት ቢያሳሳም መንታም ቢሆን መልኩ፣
ሞት የናቀ 'ለት ነው፤
የወንድ ልጅ መብቃት ጀግና የመሆን ልኩ።

እውነት ነው፤
እርግጥ ነው፤
እንደ ጋቢ ካፖርት ሀዘን የደረበ፣
ጥም መቁረጫ ያጣ አንጀቱ የተራበ።
እንኳንና "መሆን" ለጠፋው "ምናልባት"።
የሴት ልጅ ፈገግታ ምኑም ነው ደምግባት፣
ቀይ እንጆሪ ከንፈር አያይም ዳሌ ባት።

እውነት ነው ሀቅ ነው፤
መኖር ለታከተው ቀን ለሸረከተው።
አለም ለናቀው ሰው ግራ ለተጋባ፣
ናፍቆት እንጦሮጦስ ፍቅር ገደል ይግባ።
ዘላለም ነኝ አትበይ፤
ሁሌም አለሁ አትበይ፤
ቆመሽ አታስቁሚው ሂጂ አንቺም ወዳሻሽ፣
አሁን የጨበጥሽው፤
ማለዳሽን እንጂ አታውቂውም ማምሻሽ።
      " ሰምተሻል አንቺን ነው !!!"
.
.
ሀዘን ሆይ ክፉ ነህ !
ማጣት ክፉ ጠላት፣
ማርያምን አውሬ ነህ ገዳይ ነህ መጠማት።
ከ'ኔ ራቅ መባተል!!!!
መገፋት መግተልተል።
መንዘፍዘፍ ደክሞኛል፣
እስኪያቅተኝ ድረስ እራሴን አሞኛል።
የደከመ አታውቅም ?
የከፋው አታውቅም ?
የአምና ቀኔ በቃህ ዛሬን ልኑርበት፣
አይችሉት የቻለን ጥርሴም ልሳቅበት።
ብዬ ብለምንህ፤
ብዬ ባስለምንህ፤
ክፉ አይደለህ ድካም አይተህ መች ልታልፈኝ፣
ሩቅ ተጓዥ ነኝና፤
መሸሸጊያ አላጣም ይልቅ ና እና እቀፈኝ።
.
.
.
"እኔ ትግል ላይ ነኝ እርሶም መልካም ትግል ይሁንልዎ!!"


    ዓቢይ ( @abiye12 )

ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19