Get Mystery Box with random crypto!

ሰሞንኛ! (በእውቀቱ ስዩም) በቀደም የአባቶች ቀን ሲከበር ከሰባት አመት በፊት “ ለአባቴ “ ጽፌ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

ሰሞንኛ!
(በእውቀቱ ስዩም)

በቀደም የአባቶች ቀን ሲከበር ከሰባት አመት በፊት “ ለአባቴ “ ጽፌ በማለዳ ድባብ ውስጥ የታተመ ውዳሴ ግጥም እዚህ ግድም ሲዘዋወር ዋለ፤ በረከት ገበሬዋ የተባለች የተሳካላት ሴት ግጥሙን አነብንባ ለቀቀችው፤ በረከትን በስኬትዋ የሚቀኑባት፥ ወይም በግላቸው ምክንያት የጠመዷት ሰዎች ከግጥሙ ውስጥ አንዲት ቃል መዝዘው ዘመቱባት ፤ በረከት በምትችለው አስረድታለች፤ አሁን የኔ የባለቤቱ ተራ ነው፤

ላባቴ የጻፍኩት ግጥም ላይ “ሉሲፈር “ እሚል ቃል ተጠቅሚያለሁ፤ ትርጉሙ አሻሚ ለሆን እንደሚችል በመገመት በግርጌ ማስታወሻ ላይ ቃሉን የተጠቀምኩበትን አግባብ ማስቀመጥ አልረሳሁም፤

ሉሲፈር የሚለው ቃል መሰረቱ ሮማይስጥ ወይም ላቲን ነው ፤ የንጋት ኮከብ ወይም ያጥቢያ ኮከብ “ በሚል ይተረጎማል፤ ቬነስ የተባለቸው አንጸባራቂ ፕላኔት በዚህ ስም ስትጠራ ቆይታለች፤ በዚህ ረገድ፥ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ትንቢተ ኢሳያስ የባቢሎን ንጉስ ሲናገር እንዲህ ይላል፤
“ አንተ የንጋት ልጅ ፤ አጥቢያ ኮከብ ሆይ! እንዴት ከሰማይ ወደቅህ ! አህዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ እንዴት እስከምድር ድረስ ተቆረጥህ “
እያለ ይቀጥላል፤

አማርኛው የንጋት ልጅ ወይም ያጥቢያ ኮከብ እሚለውን የላቲኑ ትርጉም ሉሲፈር ይለዋል፤ የባቢሎኑ ንጉስ በቅጽል ስሙ “ ያጥቢያ ኮኮብ ወይም የንጋት ልጅ “ ተብሎ ይጠራ ነበር ፤ ባገራችንም ነገስታት “ ጸሀዩ ንጉስ “ ተብለው ይሞገሱ ነበር ፤ ለእቴጌ ምንትዋብ በነገሱ ጊዜ “ አሁን ወጣች ጀንበር ፤ ተሸሽጋ ነበር “ ተብሎ ተዘፍኗል ፤ ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልክቱ ኢየሱስን ለመግለጽ ይሄንን ቃል ተጠቅሟል “ ምድርም እስኪጠባ ድረስ ፥ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ ፥ሰው በጨለማ የሚያበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህንን ቃል እየተጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ” (ምእራፍ 1፤ 19)

በሌላ በኩል፥ የካቶሊክ የስነመለኮት እና ባለቅኔዎች በሁዋለኛው ዘመን ኢሳያስ ስለ ባቢሎን ንጉስ የተናገረውን በመተርጎም ሉሲፈር የሰይጣን የቀድሞ ስም ነው የሚል ትረካ አስተዋውቀዋል፤ በርግጥ፥ ማርቲን ሉተርን ጨምሮ ታላላቅ የፕሮቴስታን አባቶች ይህንን ትርጓሜ አልተቀበሉትም፤ እኔ ባህላዊ እውቀቴን ባገኘሁበት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ፥ የክፋት አውራ እንደሆነ እሚታመነው ፍጡር፤ ልዩልዩ ስሞች ይሰጡታል፤ ካልተሳሳትኩ ሄዋንን ያሳታት ሰይጣን” ተመን “ ይባላል፤ መጽሀፈ ሄኖክ የልዩልዩ አጋንንትን ስሞችን ሲዘረዝር ሉሲፈር እሚል አልጠቀሰም፤ ሰይጣን፤ ሳጥናኤል፤ ቢልዘቡል፤ ጸላኤ ሰናይ፥ እሚል አውቃለሁ፤

እኔ ገጣሚ ስለሆንኩ እያንዳንዷን ቃልና ዘይቤ በጥንቃቄ ለመምረጥ እሞክራለሁ፤ “ላባቴ” በተሰኘው ግጥሜ ላይ “ሉሲፈር “እሚለው ቃል “የንጋት ኮከብ “ የሚለውን እንዲገልጽ ተጠቅሜበታለሁ፤ ባንጻሩ ስለ ክፋት (evil) መጻፍ በፈለግሁበት ጊዜ ‘ሰይጣን” እና “ዲያብሎስ “የሚሉ ቃላትን ተገልግየባቸዋለሁ ፤ ለዚህ ማሳያ እዚያው የማለዳ ድባብ ውስጥ “ አባ ይፍቱኝ “ እሚለውን ግጥሜን እጠቅሳለሁ፥

“ አባ ይፍቱኝ
ሰይጣን ብሎ ነገር ፥ የተጭበረበረ
ዋዛ ነው ቧልት ነው ፥ ብየ አስብ ነበረ
ይሄው እውነት ሆኖ ዋዛና ተረቱ
ዲያብሎስን አየሁት፤በሸሚዝ ዘንጦ
እልፍ ግዳይ ጥሎ፥ ቸብቸቦ ጨብጦ”

(የማለዳ ድባብ ፥ ገጽ 75)

ዛሬ ዛሬ፥ ሚድያ ከፍተው ከሞላ ጎደል ለአገሪቱ በጎ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን ስም በማጥፋትና ባልዋሉበት በመወንጀል የሚተዳደሩ ሰዎች አሉ፤ የግል ውድቀታቸውን ፤ ክፋታቸውን በሀየማኖት እና በሀገር ፍቅር ካባ ስለሚሸፍኑት የሚያዳምጣቸውና የሚከተላቸው አላጡም ፤ “ ዲያብሎስን አየነው በሸሚዝ ዘንጦ” እሚለው ሀረግ ደና አድርጎ ይገልጻቸዋል፤ የሚባንንባቸው ትውልድ እስኪመጣ ድረስ በቅደስና ስም ክፋትን እየነገዱ ይቆያሉ::


ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19