Get Mystery Box with random crypto!

ሀሳብ አልባ ወንበሮች --------------------------- በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ብል | @እንደኔ እይታ.....

ሀሳብ አልባ ወንበሮች
---------------------------

በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ብልጽግና ከሀሳብ ክርክር ሲሸሽ የመጀመሪያው አይደለም። "እመጣለሁ" ብሎ ይቀራል። "ቀኑ ይቀየርልኝ" ብሎ ቀኑ ተቀይሮለት ይቀራል። ታዛቢዎች እና ባለሙያዎች በሚታደሙበት "አልከራከርም" ይላል፣ በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ ክርክር ለመሳተፍ አሻፈረኝ ይላል። ለእኔ ከሌሎቹ ተጨማሪ ሰአት ይጨመርልኝ፣ ሌሎቹ አንድ አንድ አባል ሲወክሉ እኔ ብቻ ሁለት ተከራካሪ ይፈቀድልኝ ብሎ ችክ ይላል... ሰበቡ ማለቂያ የለውም።

ዛሬ ኢቲቪ (EBC) አምስት ፓርቲዎችን በመጋበዝ በባህል እና ቱሪዝም ላይ የምርጫ ክርክር ለማድረግ ቀጠሮ ነበረን። አራት ፓርቲዎች (ኢዜማ፣ እናት፣ አብን፣ ነጻነት እና እኩልነት) በቀጠሮአችን ሰአት ኢቲቪ ስቱዲዮ ተገኝተን ነበር። እኔ እና ዶ/ር ሙሉዓለም ኤዜማን ወክለን ቀድመን ተገኘን። ሀሳብ አልባው ብልጽግና ፓርቲ ግን ቢጠበቅ ቢጠበቅ የውኃ ሽታ ሆነ።

የአራቱ ፓርቲዎች ተወካዮች ይህ የብልጽግና ተደጋጋሚ ነውር ተቀባይነት እንደሌለው እና ብልጽግና ቀረ ተብሎ ክርክሩ ከሚሰረዝ የመጣነው ፓርቲዎች ክርክራችንን መቀጠል አለብን የሚል አቋም ያዝን። ኢቲቪ ግን ጌቶቹን በመፍራት "ክርክሩ አይካሄድም" አለ።

ከአንድ ሰአት በላይ ተጨቃጭቀን ኢቲቪ ሀሳቡን እንደማይቀይር ስንረዳ ከኢዜማ የተወከልነው እኔ እና ዶ/ር ሙሉዓለም ለመጡት ፓርቲዎች አንድ ሀሳብ አቀረብን። "ስቱዲዮ ውስጥ ገብተን በየቦታችን እንቀመጥ የብልጽግና ወንበሮች ለታሪክ ባዶ ሆነው ፎቶ እንነሳ" አልን። ፓርቲዎቹ ተስማሙ። እነሆ ይህንን ፎቶ በስልካችን ካሜራ ለታሪክ አስቀረን።

ደራሲ በዓሉ ግርማ "ከአድር ባይ ብዕር ይልቅ ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል" እንዲል እኔ ደግሞ "ከሆድ አደር ካድሬ ይልቅ ባዶ ወንበሮች ሀሳብ አላቸው" እላለሁ።