2021-04-28 00:53:44
+++ የይሁዳ እግሮች +++
ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመሥጠት ከአይሁድ ጋር የተስማማው ረቡዕ ዕለት ነበር፡፡ ይህን ስምምነት አድርጎ እንደጨረሰ ወደ ጌታና ወደ ደቀ መዛሙርቱ ማኅበር ተመለሰ፡፡ ከረቡዕ ጀምሮ እስከ ሐሙስ ማታ ድረስም ከጌታ ፊት ምንም እንዳልተፈጠረ ሆኖ አሳለፈ፡፡ ይህ በትክክል ይሁዳ ምን ዓይነት አስመሳይና ክፉ ሰው እንደነበረ ያሳያል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁኔታዎች አስፈርተውት ጌታውን ለሦስተኛ ጊዜ አላውቀውም ብሎ ከካደ በኋላ ጌታችን ለአንድ አፍታ ቀና ብሎ ስለተመለከተው ብቻ የጌታውን ፊት በድፍረት ለመመልከት አቅም አጥቶ መራራ ልቅሶን እያለቀሰ ከአጥር ውጪ ወጥቶ ነበር፡፡ ይሁዳ ግን አሳልፎ ሊሠጠው ከተስማማባት ሰዓት ጀምሮ ድምፁን አጥፍቶ ከጌታችን ጋር እንደ ወትሮው አብሮ ሲቀመጥ አንድ ጊዜ እንኳን አልተሸማቀቀም፡፡
ልብ አድርጉ! በራሱ ሃሳብ አመንጪነት ፣ ራሱ ወደ አይሁድ ሸንጎ ሔዶ ፣ ብር ለመቀበል ተስፋ ተቀብሎ ከመጣ በኋላም የጌታችንን ዓይኑን እያየ ‹አሳልፌ የምሠጥህ እኔ እሆንን?› ብሎ ለመጠየቅም ድፍረት ነበረው! በዚያች ሰዓት እንደ ዳታንና አቤሮን መሬት ተሰንጥቃ ስላልዋጠችው ፣ ምላሱ ከጉሮሮው ጋር ስላልተጣበቀ ፣ በድፍረትና በመናቅ በእውነተኛው ጌታ ላይ የተናገሩት የሽንገላ ከንፈሮቹ ዲዳ ባለመሆናቸው የፈጣሪን ትዕግሥቱን እናደንቃለን፡፡ ሁሉን የሚያውቀው ጌታ ግን ይሁዳ ሊሸነግለው መሞከሩን ቢያውቅም ‹አንተ አስመሳይ!› ብሎ አላዋረደውም፡፡
የእግዚአብሔር ነቢይ ኤልሳዕ ሎሌው ግያዝ የማይገባውን ገንዘብ ከለምጹ ከነጻው ከሶርያዊው ንዕማን ተቀብሎ ቤቱ ወስዶ ከሸሸገ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆኖ ከፊቱ መጥቶ ሲቆም ‹ግያዝ ሆይ ከወዴት መጣህ?› ብሎ ጠይቆት ነበረ፡፡ ግያዝም ‹‹እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሔድሁም›› አለ፡፡ ኤልሳዕም ፡- ‹‹ልቤ ከአንተ ጋር አልሔደምን?›› ብሎ ያደረገውን እንዳወቀበት ከነገረው በኋላ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ ይጣበቃል ብሎ ረግሞት እንደ በረዶ ለምጻም ሆኖ ወጣ፡፡ (፪ነገሥ. ፭፥፳‐፳፯)
ሐዋርያው ጴጥሮስም ሐናንያና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስት ገንዘባቸውን ከቤታቸው ሸሽገው መንፈስ ቅዱስን ሊያታልሉና በማስመሰል በፊቱ ሊቆሙ ሲሞክሩ ‹እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሻችሁም› ብሎ በካህን ቃሉ ተናግሮ ተቀሥፈው እንዲሞቱ አድርጓቸዋል፡፡ (ሐዋ. ፭፥፩-፲)
የነቢያትና የሐዋርያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኤልሳዕና ከጴጥሮስ በላይ የልብን የሚያውቅና መቅጣት የሚቻለው ነው፡፡ ሆኖም ከአይሁድ ጋር ሊሸጠው ተዋውሎ የመጣው ይሁዳ ዓይኑን በጨው አጥቦ ‹አሳልፌ የምሠጥህ እኔ እሆንን?› እያለ ሲዘብትበት በታላቅ ትዕግሥት ዝም አለው፡፡ ነቢያትንና ሐዋርያትን ሊያታልሉ የሞከሩ ሰዎች እንዲህ ከተቀጡ የነቢያትን አምላክ ሊያታልል የሞከረ ‹‹…እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?›› (ዕብ. ፲፥፳፱)
ከሁሉም ልብ የሚሰብረው ሐሙስ ምሽት የሆነው ነገር ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ›› የእግር ሹራብ በማይደረግበትና ክፍት ጫማ በሚደረግበት በዚያ ዘመን ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ የዋሉበትን የሐዋርያቱን በአቧራ ያደፉ እግሮች ሊያጥብ ተነሣ፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፬) በእስራኤል ባህል እግር ማጠብ የሎሌዎች ሥራ ቢሆንም የሰማይና የምድር ንጉሥ ግን በትሕትና እንደ ሎሌ ሆነ፡፡ (፩ሳሙ. ፳፭፥፵፩)
ጌታችን አጎንብሶ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ ይሁዳም ሊታጠብ ተራውን ይጠብቅ ነበር፡፡ ጌታውን ሊሸጥ በተስማማበት ማግሥት ጌታችን አጎንብሶ እግሩን አጠበው፡፡ ‹‹ወኀፀበ እግረ ይሁዳ አስቆሮታዊ ዘያገብኦ›› ‹‹የሚያስይዘውን የአስቆሮቱ የይሁዳንም እግር አጠበ›› እንዲል (ግብረ ሕማማት ዘሐሙስ)
ከአንድ ቀን በፊት ክፋትን ለማሴር ወደ አይሁድ ካህናት ግቢ የሮጡትን የይሁዳን እግሮች ጌታችን አጎንብሶ አጠባቸው፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሊያስይዘው ወደ አይሁድ የሚሮጥባቸውን እግሮች ፣ የሚይዙትን ወታደሮች እየመራ ወደ እርሱ የሚመለስባቸውን እግሮች አጠበለት፡፡ ምንም እንኳን በነገው ዕለት እግሮቹን እንዲቸነከር አሳልፎ የሠጠው መሆኑን ቢያውቅም ሰውን ወዳጁ ክርስቶስ ግን የአስቆሮቱ ይሁዳን ለመጨረሻ ጊዜ እግሩን አጥቦ ተሰናበተው፡፡
እንደ ነቢዩ ዳዊት ‹‹አቤቱ፥ ምሕረትህን እንዴት አበዛህ!›› ከማለት በቀር በምን አንደበት ልንናገር እንችላለን? (መዝ. ፴፮፥፯) ‹‹ጠላቶቻችሁን ውደዱ›› ያለን ጌታ አሳልፎ የሚሠጠውን የይሁዳን እግር ሲያጥብ ከማየትስ በላይ በቂም በቀል ለሚቆስለው ልባችን ምን መድኃኒት ይኖር ይሆን?
ይሁዳ ሆይ እስቲ አንድ ጊዜ ንገረን ፤ ጌታ አጎንብሶ እግርህን ሲያጥብህ እንዴት አስቻለህ? ‹እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ› የሚሰገድለት አምላክ እግርህን ሲያጥብህ እንዴት ትንሽ እንኳን አልተሰማህም? አንተ እግሩን ልታጥበው እንኳን የማይገባህ ፈጣሪ እግርህን ሲያጥብህ እያየህ እንዴት ልብህ ደነደነ? መጥምቁ ዮሐንስ ‹የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም› ያለው ጌታ አጎንብሶ ሲያጥብህ እንዴት ልብህ በጸጸት አልተሰበረም? ረቡዕ አሳልፈህ ልትሠጠው ተስማምተህ መጥተህ ሐሙስ አጎንብሶ ሲያጥብህ እንዴት አልጨነቀህም? ከአይሁድ ጋር የተስማማኸው ነገር ‹ይቅርብኝ› ለማለት ጌታችን ከእግርህ በታች ዝቅ ብሎ ካጠበህ ሰዓት የተሻለ ማሰቢያ ጊዜ ከየት ይገኛል? በፍቅሩ ውስጥ ክፋትህ ፣ በትሕትናው ውስጥ ትዕቢትህ እንዴት አልታየህም? እንዴትስ እግሮችህን ሠጥተህ ያለ አሳብ ታጠብህ?
ቅዱስ ጴጥሮስ እንኳን ‹‹ጌታ ሆይ አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?› ብሎ ተጨንቆ ጠይቆ ነበር፡፡ ‹የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም› ብሎ ተከላክሎም ነበር፡፡ ልበ ደንዳናው ይሁዳ ግን ዝም ብሎ እግሮቹን ሠጠ፡፡ የከዳውን ጌታ የቁልቁል እየተመለከተ ለአፍታ እንኳን ልቡ አልተመለሰም፡፡ ሐዋርያት ጌታ ባጠበው እግራቸው ለጊዜው ፈርተው ቢሮጡም በኋላ ግን በጸጸት ተመለሱበት፡፡ በአምላክ እጅ በታጠበ እግራቸው ያለመሰልቸት ዓለምን ዞረው ወንጌሉን አስተምረው እስከሞት ድረስ ታመኑ፡፡ በእግራቸውም እንደ ስማቸው ሐዋርያት (ተጓዦች) ሆኑበት፡፡ ይሁዳ ግን በአምላክ እጅ በታጠበው እግሩ ወደ አይሁድ ገስግሶ ጌታ ለሚያንገላታው ጦር መንገድ እየመራበት ተመለሰ፡፡
‹‹ኦ እግዚኦ ዘኢትደፈር ይሁዳ ደፈረከ››
‹‹አቤቱ የማትደፈር አንተን ደፋር ይሁዳ ደፈረህ!››
(ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ ፩፥፳፩)
("ሕማማት)" (ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ )
4 views21:53