🔥 Burn Fat Fast. Discover How! 💪

5/09/13 ብትመጪ ቀላል ነበር። በጉዞዬ፣ እርምጃዬን እቆጥራለሁ። እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ይሄ | The Articulation Bureau

5/09/13

ብትመጪ ቀላል ነበር።


በጉዞዬ፣ እርምጃዬን እቆጥራለሁ። እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ይሄ መንገድም ችግር አለበት። ስንት ዘመን ሄድኩበት? ስንት ሰዎች ሄዱበት? አንድም የወደቀ ብር ኖሮ አያውቅም። አዲስ ነገር ኖሮት አያውቅም። ሰዎች እንኳን አንዳንዴ አይጋጩም? ቦክስ ነገር እንኳን? የሆነ ደብለቅለቅ ያለ ነገር? ትላንት ያልነበረ አይነት? አዲስ አዲስ ነገር?

ጠጅ ቤት እገባለሁ። ጠጅ ነበር የመጣው ግን አረቄ አረቄ ይላል። ደሞ ሻይ ሻይም ይላል።
እንቱፍ! “ኧረ ማነህ አስተናጋጅ!”

አስተናጋጅ ቀልጠፍ ቀልጠፍ እያለ ሲመጣ አውቅ ነበር። ይሄኛው እጁን ኪሱ ውስጥ ከቶ ይመጣል። ወክ ያደርጋል? ሲደርስ እበሰጫጫለሁ ቆይ። እሱ እስኪደርስ ጆሮዬን ጣልኩ። ከአንዱ ግድግዳ ጠርዝ የሚፈልቅ የአረጋኸኝ ወራሽ ዘፈን ይሰማል። ምናባቱ ይልመጠመጣል ይሄ ደሞ? ለምንድነው አረጋኸኝ ታዋቂ ዘፋኝ የሆነው? እዛ  ጋር ደሞ አንዱ ሰካራም ተነስቶ ይፀልያል። ተነስቼ በቴስታ ልንደለው?

“ጠጁን ቀይርልኝ! አንድያህን ለምን አትቀመጥም? ለምን እየመጣን አናዝም? ስራህን ስራ ወደዛ!!”

ሌላኛው ጠጅ። ይኸው ደሞ ይሄኛውም ጭራሽ ወተት ወተት የሚል። ጨጓራዬን እያስፋቀኝ እወጣለሁ። ከላይ አግኙት።

መንገድ ላይ ፖሊስ አለ። ልጣላው ይሆን?

እሄዳለሁ ወደ ትያትር ቤት። ያየሁትን ትያትር ነው የምደግመው። ይህን ትያትር እወደው ነበር። ዛሬ ግን ወይ ቀልዳቸው አያስቅ፣ ወይ ንግግራቸው አያምር፣ ወይ ትወናው አልሆነ፣ ውሃ ውሃ! “ማነው ስክሪፕቱን የለወጠው?” ማለት እፈልጋለሁ። እጄን ላውጣ ያዩኛል? ልጩኽ በመሃል “ተበላሽቷል” ልበል? ኤዲያ! ተነስቼ እወጣለሁ።

ሊስትሮው “ጫማው ኢጣረግ?” ይለኛል።

ወያላው “ጀሞ 2 ጀሞ 2” ይላል። “ትሄጃለሽ? ኧ ብራዘር?” ይላል።

ሎተሪ አዟሪው “ዛሬ የሚወጣ! ዛሬ የሚወጣ!” ይላል።

ሰው ሁሉ ነገር ነገር ይለዋል ምነው?

ከተማው ምነው ካልተጣላውህ አለ?

አየሩ ምነው ካልተጋረፍኩ አለ?

ግን ቀላል ነበር። ብትመጪ ቀላል ነበር።


@amadonart