Get Mystery Box with random crypto!

የተሰወረ ጥበብ ይፈለጋል (በእውቀቱ ስዩም) መምህር ሰሎሞንን ድሮ ነው የማውቃቸው ፤ በሙያቸው ሂሳ | በእውቀቱ ሥዩም እና ሥነ-ፅሁፍ

የተሰወረ ጥበብ ይፈለጋል
(በእውቀቱ ስዩም)
መምህር ሰሎሞንን ድሮ ነው የማውቃቸው ፤ በሙያቸው ሂሳብ መምህር መሰሉኝ ፤ ምን እንደደረሱ ባላውቅም አንድ ሁለቴ ደራሲያን ማህበር ስብሰባ ላይ አይቻቸዋለሁ፤ በስብሰባው ላይ እጃቸውን ያወጡና አስተያየት ለመስጠት ይጠይቃሉ፤ መድረክ ላይ የሚቀመጡት ጋባዦች ብዙ ጊዜ አይተው ቸል ይሉዋቸዋል፤” በህግ አምላክ እሱን ማይክ ስጡኝ !” ብለው ይቀውጡታል ! ማይክ አቀባባዩ ትቱዋቸው ያልፋል! “ ተውታ እንግዲህ ! “ ይሉና ከካፖርታቸው ውስጥ ከቤታቸው ይዘውት የመጡትን wireless ማይክ አውጥተው ረጅም አስተያየት ይሰጣሉ ፤ (የማይኩን ጨዋታ እንኩዋ ፈጥሬው ነው)
እምገርም ነው! መምህር ሰሎሞንን ፤ ሰሞኑን ነቢይ ሆነው ዩቲውብ ላይ አየሁዋቸው፤” ከየካቲት 12 ጀምሮ ያስፈራል “ ይላል አንዱ ጥንቢታቸው! “ ከታህሳስ 12 በሁዋላ ያለው ጊዜ በጣም አስፈሪ ነው” ይላል ሌላኛው ! የምን ቁጥ ቁጥ ነው?! አመቱን ሙሉ ያስፈራል ብለው ለምን አይገላገሉም?
መምህር ሰሎሞን ከነ እስራኤል ዳንሳ ትንሽ ለየት እሚያደርጋቸው ትንቢታቸውን ከመፅሀፍ ቅዱስ በተጨማሪ በካልኩሌተር ማጀባቸው ነው፤ ትንቢታቸውን እየዘረዘሩ በመሀሉ ፤ “ ታህሳህ 13’፤ ከሱባኤው ዘመን ጋር ስንደምረው ስንት ይመጣል?” በማለት ጋዜጠኛውን ያፋጥጡታል ፡፡ ጋዜጠኛው በበኩሉ “ እኔ እንዲህ አይነት የተወሳሰበ ሂሳብ ብችል እዚህ ምን አስቀመጠኝ? ናሳ አልቀጠርም? “ በሚል አይነት መልሶ ይሾፋቸዋል፤፤
ቪድዮአቸውን ወደ ሶስት መቶ ሺህ ሰው አይቶታል፤ ጋዜጠኛው ዩቲውብ ከሚለለቅበት ክፍያ ትንሽ እሚበጥስላቸው ይመስለኛል ፤ ይብላኝ ለሰፊው ህዝብ እንጂ ለሳቸው ከታህሳስ 12 ወር ያለው ጊዜ አስፈሪ አይሆንም፤ ሌላው ቢቀር የየወር አስቤዛ ይሸምታሉ፤
ኢትዮጵያ ውስጥ ትንቢት ማለት ስለሚመጣው ዘመን ከባድነት መናገር ነው፤ ስለዚህ የሚከሽፍ ትንቢት ሊኖር አይችልም ! እኔ አሁን ተነስቼ የሚቀጥለው ሳምንት አሰቃቂ ነገር ይደርሳል ብል ትንቢቴ ሊከሽፍ ነው? ወይ ወለጋ ወይ መተከል የሆነ ሰው ይሞታል፤ ካልሞተ ደግሞ በፆምና በፀሎት ብርታት ተቀልብሱዋል ብየ አመልጣለሁ !
በድሮ ጊዜ ነቢይ ማለት የተሰወረ እውቀት የሚገልጥ ጠቢብ ማለት ነበር ፤ ዛሬ ነቢይ ማለት የሙሉጊዜ አሙዋራች ማለት ሆነ ! እስቲ የተሰወረውን እንባንናለን መጭውን እናውቃለን ብላችሁ የምታምኑ እኔም አምን ዘንድ እኒህን ጠቃሚ ጥያቄዎች መልሱልኝ
1)ሚያዝያ አንድ ( አዲሳባ የምገባበት ቀን ነው) የውጭ ምንዛሬ ስንት ይገባል?
2) ደብረፂዮን በመጫኛ ተጎትቶ ደብረዳሞ ገብቶ መነነ እሚባለው ነገር ምን ያህል እውነት ነው?
3. ኢሳያስ አፈወርቂ እንዲህ እንደ ብረት ሀውልት ቀጥ እንዳለ ስንት አመት ይቆያል?
4. ዳዊት ፅጌ ኮንሰርት መች ያቀርባል?


ከወደዱት ለወዳጆ ያጋሩ
@bewketuseyoum19
@bewketuseyoum19